ለውጥንቅጡ ፖለቲካችን መፍትሔ

0
693

የኢትዮጵያ የኅልውና ሥጋትና የሕዝብ ሰላም ማጣት ችግር ዋና መንስኤ ዘርና ፖለቲካ መቀላቀላቸው ነው የሚሉት መላኩ አዳል, ከዚህ ችግር መውጫ መንገዱ ሕገ መንግሥትን በማሻሻል ርዕዮትን መሰረት ያደረገ ፖለቲካን ማካሔድና ፌደራላዊውን አወቃቀር ማስተካከል ነው ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውን አቅርበዋል።

 

ዘርና ፖለቲካ ወይም ሃይማኖትና ፖለቲካ ከተቀላቀሉ ውጤቱ አገር ማፍረስና የሕዝብ ሰላም ማጣት ነው። በአገራችንም ዘርና ፖለቲካ ተቀላቅለው የአገር ኅልውና የሕዝብ ሰላም አደጋ ላይ ወድቋል። የዘር ፖለቲካ ያመጣብን አንዱ ችግር፣ ሁሉም ቡድን የየራሱ “እውነት” እንዲኖረው ማድረጉ ነው፤ እውነት ስለአንድ ነገር አንድ ብትሆንም። ይህም በቡድኖች መካከል መግባባት እንዳይኖር አድርጓል፤ የሕዝቦች ጠላትነት ብሎ ነገር ባይኖርም። ችግሩ የልኂቃን የፍላጎት ተቃርኖና ሕዝብን የድክመታቸው መከለያ ማድረጋቸው ነው። ስለዚህ በሕዝቦች መካከል የጠላትነት ስሜት እንዳለ መተረኩ ሊታረም ይገባል።

የሕዝባችን ጀግንነት፣ ሃይማኖተኝነትና መከባበር፣ በዘውጌነት ብሎም ዘረኝነት ሥነ ልቦና መተካቱ አፍራሽነቱን በተግባር እያየን ነው። ኢትዮጵያዊነት ለሁሉም ዜጎች ያለአድሎ፣ ለአገር ኅልውናና ደኅንነት ያለ ራስ ወዳድነት ለማገልገል እራስን ማብቃትና፣ እሱንም በተግባር ማሳየት እንጂ ማስመሰል አይደለም። ነገር ግን የምናየው ለዓይን የማይመች፣ የምንሰማው ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ነው። የወቅቱ ዋናው ችግራችን የሞራል እሴታችንን ማጣታችን ነው። የሌብነቱ፣ የራስ ወዳድነቱ፣ የዘረኝነቱ መንስኤ ይኸው ነው። ይህች አገር ደሃ ግን ውብነች፣ ውበቷ ሕዝቧ ነው። የድኅነቷ ምንጭም የአስተሳሰብ ችግር ያለባቸው እንደ ኦነግና ሕወሓት ዓይነት ዘረኛ ድርጅቶች ናቸው። በፖለቲከኞች፣ ፓስተርና ነብይ ነን ባዮች በአገሬ ሕዝብ ላይ እየተደረገ ያለው የሥነ ልቦና ጦርነት ለሕዝብ ፍርሃትን፣ ለአገር የደኅንነት ስጋትን አስከትሏል። ከወጣቱ ያየሁት የዕውቀት ድኅነቱን፣ በዚህም ምክንያት ተጠራጣሪነቱን ነው። እንወቅ፣ እናስብ፣ እንደማመጥ፤ ውሳኔያችን በአመክንዮ እንጂ በዘር አይሁን እላለሁ። ለዚህ የሞራል መላሸቅ መንስኤው ድኅነት፣ ድንቁርና፣ ኋላቀርነት፣ ደካማ ባሕል፣ ብሎም እሱን ተከትሎ የመጣው የልኂቁ ጠባብ የሆነ የዘር ፖለቲካና የዘር ፌዴራሊዝም ነው።

የግል ባንኮች ባለቤትነትና ስያሜ፣ እንዲሁም የፓርቲዎች ንብረት የሆኑ የንግድ ተቋማት ዋናው መነሻቸው ብሔርን ብቻ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ፣ ውጤቱም ዘረኝነትንም ማስፋፋት ነው። ቋንቋን መሠረት ያደረገው ዘውጌ ፌዴራሊዝም ውጤቱ አንድነትንና እኩልነትን በማኮስመን ዘረኝነትንና የቡድን የበላይነትን ማንገስ ነው። ዘርን መሠረት ያደረገ፣ ብቃትን ወደ ጎን የተወ የሹመትና የቅጥር ሁኔታ ይህን ሁኔታ አባብሶታል። በጠቅላላው ከአገራችን ክስተቶች ምን ተማርክ ብትሉኝ፣ አንድ ርዕዮት አውንታዊና አሉታዊ ጎኑ በደንብ ተጠንቶ ወደ ሕዝብ ካልወረደ፣ ሰውን ወደ እንሰሳነት የመቀየር አቅም እንዳለው ነው።

የአገር ገንጣዩ ሻዕብያ፣ የተባባሪዎቹ ሕወሓትና ኦነግ፣ የአዲሱ ምትካቸው አብን ፖለቲካ፣ ለአገር ኅልውናና ለሕዝብ ሰላም ፀር ነው። እደግመዋለሁ፣ የትግሬው ሕወሓት፣ የኦሮሞው ኦነግና የአማራው አብን እየፈጠሩ ያለው ችግር ለአገር አንድነትና ኅልውና አደጋ ነው። ሻዕብያ የኢትዮጵያ አንድነት ፀር፣ የሕወሓትና ኦነግ የዘውግ ፖለቲካ አስተማሪ እሱ ነበረ፣ ነውም። ኦነግጎች የውሸት ታሪክ ፈጣሪዎች፣ በሱም የተጠመቁና የአኖሌን የውሸት ጡት ተቆረጠ ሐውልት ከሕወሓት ጋር በትብብር ያቆሙ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብዛት 7 ሚሊዮን በነበረበት ዘመን፣ 5 ሚሊዮን ኦሮሞ ተጨፈጨፈ ያሉ የውሸት አርበኞች ናቸው። የብሔር ፌዴራሊዝም፣ የዘር ፖለቲካ የሚያራምድና የአኖሌ ሐውልትን ያቆመ ድርጅት የጥላቻ ሕግ አወጣ ሲባል ስንሰማ፣ ፓርቲውንና ሐውልቱን ያፈርስ ይሆን ማለታችን አይቅርም? ኹለቱም መሰረታቸው ጥላቻ ነውና። ይኸው ብሔር ፖለቲካና ፌዴራሊዝም የሚያካሒደው ጠባብ ብሔርተኛ ከአካባቢ ጽዳት ሲያካሒድ ስናይ፣ ከዚህ አስቅድሞ አዕምሮውንና አስተሳሰቡን ቢያፀዳ እንላለን። የአብዛኛው ችግራችን መንስኤ ይህ የአስተሳሰብ መቆሸሽ ነውና። በጠቅላላው የኦነግ አስተሳሰብ ከኦሮሞው፣ የሕወሓት አስተሳሰብ ከትግሬው፣ የአብን አስተሳሰብ ከአማራው፣ ተጠራርጎ መጥፋት ለተሻለች ኢትዮጵያ አስፈላጊ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል። ለመሆኑ ኦነጋውያንና ሕወሓታውያን፣ ግን ስንተርክላችሁ የከረምነው የታሪክ ትርክት በሙሉ የኦነግና ሕወሓት ፈጠራ ነው ሲሏችሁ ምን ተሰማችሁ፣ ሀፍረት ወይስ ኩራት?

ኦነግና ሕወሓት ከማነው ኦሮሞውንና ትግሬውን ነፃ የሚያወጡት? በዚህ ሥማቸውስ እየተጠሩ አገር መምራትና ለመምራት መወዳደር፣ ሕጋዊነቱ እስከምን ድረስ ነው? ኦሕዴድ/ኦነግ በላቲን መፃፍን የትምህርት ፖሊሲ አካል ያደረገው፣ በኢትዮፒክ ኦሮምኛን መፃፍ ስለማይችል ሳይሆን፣ ጥላቻቸውንና የመገንጠል ዓላማውን ይደግፍልኛል ብሎ በማመኑ ነው። ስለዚህ አንድነት እንዴት? እንግሊዝ በቀኝ ግዛት ያስፋፋችውን እንግሊዝኛ እየተናገረና እየጻፈ፣ ኢትዮፒክን ትቶ በላቲን እየጻፈ፣ ከአገሩ በር የቆመ ቡድንን የሚወክል ሰው የጠራ ኦሮሞ እንፍጠር ጥሪ ሊያስደንቀንም አይገባምም ነበር። አሁን ደግሞ 34 በመቶ የተወካዮች ምክር ቤት ውክልና አለኝ የሚለው የኦሮሞ ልኂቅ ከቀኝ ግዛት ተገዝተናል የሐሰት ትርክት ወደ ተራው የእኛ ነውና እንግዛችሁ እያለና ለዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ምስረታ አንቅፋትም እየሆነም ነው። ድሮ ሕወሓቶች፣ አሁን ደግሞ ኦነጎች እያደረጉት ያለው የታሪክ ሽሚያ፣ ታጋዩና መሬቱ የእኛ፣ የገዥ መደብነት ስሜትና ሥልጣንን እንደሀብት ምንጭነት ለመጠቀም መሞከር ውጤቱ የዴሞክራሲ መኮስመንና ውድቀት ነው። ኦንግና ሕወሓት ኢትዮጵያ እንደአገረ መንግሥት ብትሠራም፣ ያልተገነባው አገረ ብሔርና ኢትዮጵያዊነት በእኛ አምሳል ይወለዳል ይላሉ። የሚያድጉት በአቃፊነትና በአንድነት መዕቀፍ ውስጥ መሆኑን ግን ይክዳሉ። ሁኔታው ቅቡልነቱን በአንድ ዓመት እንዲያጣ አድርጎታል። ኦዴፓ/ኦነግ ድጋፉን በአንድ ዓመት ያጣው፣ የደካሞችና የሁሉን አማረን ስብስብ ስለሆነ እንጂ፣ ኦሮሞ ስለሆነ አይደለም። አገር መምራት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ተረድቷል፣ ዋናው ምክንያትም መንግሥት ማለት የሁሉንም ደኅንነት የሚጠብቅ፣ ጥቅሙን የሚያስከብር እንጂ፣ በኬኛ የሚመራ አይደለም። እንዴት ነው ደግሞ “ኦሮሞ መምራት አይችልም ለማስባል” የምትል ሐረግ በኦሮሞ ሊኂቃን በዛችሳ!!!? እነሱ ብቻ ሥልጣኑን እንደወረሩት እየነገሩን ይሆን?

ጠባብ ብሔርተኞች የሆኑት ሕወሓትና ኦነግ ያሉበትን አገር አረጋግቶ፣ ሰላሙንና ደኅንነቱን ጠብቆ፣ ወደ ዲሞክራሲ ማሻገር በጣም ፈታኝ እየሆነ ነው። ሕወሓትን ገፍቶ ከብዙኀኑ ለማስወጣት እየተሞከረ ቢሆንም የሚሞሉት ግን የኦነግ ፅንፈኞች ናቸው፣ አልሸሹም ዞር አሉ፣ ከድጡ ወደ ማጡ እየሔድን ነው። አሁንም በኦሮምያ፣ በአማራና በትግራይ የሚታዩ የተጋነኑ የጎሰኝነት ስሜቶች ለአገር አንድነትና ዕድገት ተግዳሮት ናቸውና የሚመለከታቸው አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች ከአደገኛ ድርጊታቸው ሊይታቀቡ ይገባል። የሚካሔደው አክቲቪዝም የአማራ፣ የኦሮሞና የትግሬ ብቻና በጉልበት የታገዘ ነው። የቀሩት ብዙኀን ጎሳዎች ጥያቄ ወደ ጎን የተገፋ ይመስላልና ይታሰብበት። ፖለቲካ ወይም ምንም ነገር ከመጠን በላይ ከጦዘ፣ መጀመሪያ ራሱን፣ ከዚያም በዙሪያው የተሰባሰቡትን ይበላል፣ ያስበላል፤ እናም፣ እናንተ አብኖች፣ ኦነጎችና ሕወሓቶች ከድርጊታችሁ ታቀቡ እላልሁ። የማንኛውም ጎሳ መደራጀት አቃፊና ችግሮችን በውይይት የሚፈታ፣ ለኢትዮጵያ ፖለቲካ የሚያደርገውን አስተዋፅኦ ታሳቢ ያደረገና ከሰፈር ፖለቲካ ቡድነኝነት የወጣ መሆን አለበት።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስተር መለስ ዜናዊ ኹለት ታሪካዊና መዘዛቸው ለዛሬም ለነገም የሚተርፍ ስህተቶች ሰርተዋል:- የዘውጌ ፌዴራሊዝምና ወደብን አሳልፎ መስጠት። ለመሆኑ እነዚህን ስህተቶች ለማረም እንደአገር ምን እየሠራን ነው? መቼና እንዴት የሚለው ጥያቄ ካልሆነ በቀር ሕገ መንግሥቱ መሻሻል፣ በዘር ፖለቲካ ፓርቲ መመስረትን መከልከልና የፌዴራሉን አወቃቀር ማስተካከል ያስፈልጋል። ሕገ መንግሥት፣ መንግሥትና ሕጎች ያስፈለጉበት ምክንያት የሰው ራስ ወዳድነት ነው። እናም የታቀደላቸውን ዓላማ እንዲያሳኩ ማስተካከልንና በትክክል መተግባርም እንወቅ። የዘር ፖለቲካና የዘውጌ ፌዴሬሽኑ በኢትዮጵያ ኅልውናና በዜጎች የትም የመኖር መብት ላይ ችግር አስከትሏል ይስተካከል እንጂ፣ ብሔርተኞች እንደሚሉት የፌዴራል መንግሥት አወቃቀር ይፍረስ ያለ የለም። አንድ፣ ኹለት፣ ሦስት ተብሎ የሚቆጠር የጋራ ርዕዮት እስከሌለን ድረስ በ108 ፓርቲ በጎጥ ተደራጅተን መባላታችን የማይቀር ነው። ዐቢይ ጠባብ ብሔርተኞችን ከመንግሥቱ በማራቅ፣ ብሔራዊ ፓርቲ መመስረት፣ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻልና የፌዴራል አወቃቀር ማስተካከል ይኖርበታል። በዘርና በቋንቋ ላይ መሰረት ያላደረጉ፣ የርዕዮት መሰረት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎችና ከዘርና ቋንቋ በተጨማሪ የሕዝብ ብዛትና የቆዳ ስፋት ተመጣጣኝነት፣ የመልከዓ ምድር አቀማመጥና አሰፋፈርን፣ የንግድና የኢኮኖሚ ትስስርን፣ የአስተዳደርና የልማት አመችነትን፣ የአኗኗር ዘይቤን፣ የታሪክ፣ ሃይማኖት፣ ሥነ ልቦናና የባሕል ትስስርን ያካተተ የፌዴራል አወቃቀር እውን መሆን የችግሮቻችን መፍትሔ ነው። በፖለቲካችን የትግሬ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ ወይም የሌላ የበላይነት የነገሠበት ስርዓት ማየት አንፈልግም፤ የምንፈልገው ሁሉም ኢትዮጵያዊ የተወከለበት ጠንካራና ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ነው። የኦሮሞ ልኂቃን ማወቅ ያለባቸው፣ 34 በመቶ ሆኖ majority የሚባል የሌለ መሆኑን ነው። ስለዚህ ከተረኝነት ወጥቶ፣ ‘ኬኛ’ን ታክሞ ለዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያ ግንባታ መታተር ነው። ሕዝብን የሚወጋና የሚያፈናቅል፣ ባንክን የሚዘርፍ፣ ሠራተኞችን ገድሎ የሚያቃጥል፣ ሴቶችን የሚደፍር፣ ሕፃናትን ያላሳዳጊ የሚያስቀር እና ቤተክርስቲያን የሚዘርፍና የሚያቃጥል የኦነግ ኀይል በሕግ መታገድና በወንጀል መጠየቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም ሕወሓት ለሚሠራው የዘመነ መሳፍንት ዓይነት እንቅስቃሴ፣ የሕገ መንግሥት ጥሰት፣ ከፌዴራል መንግሥት ጋር ያለመሥራትና፣ ለሚታዩ ሰላም መደፍረሶች ተጠያቂ የሚሆንበትን መንገድ ሕዝቡ ሊወያይበት ይገባል።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው።
በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here