የሲዳማ ሕዝብ ጩኸት ‘ሞግዚት’ ፍለጋ አይደለም!!

0
595

የሲዳማ በክልል ደረጃ ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄን ጠልፎ የራስ ፍላጎትን ለማስፈጸም የኦሮሞ ልኂቃን በኦነግና በኦዲፒ በኩል እንዲሁም የትግራይ ልኂቃን በሕወሓት በኩል እያሴሩ ነው ሲሉ ግዛቸው አበበ ይከሳሉ፤ እንደማሳያ የሚያነሷቸውን ነጥቦችም አካተዋል።

 

2011 አዲስ ዓመት ከገባበት ጊዜ ጀምሮ በሲዳማ ውስጥ የሚስተጋባ አንድ ስጋት አለ። ይህን ስጋት የወለደው ‘ኤጀቶዎች ነን’ በሚሉ አንዳንድ ወገኖች የሚያስተጋባ ወሬ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ስጋት የገባቸውም ሌሎች ‘ኤጀቶዎች ነን’ የሚሉ ወገኖች ናቸው። ይሁንና አንደኛው ወገን ሌላኛውን አበክሮ ሲቃወምና ሲኮንን ይሰማል። ኤጀቶዎች በሕጋዊ መንገድ ተደራጅተው፣ የታወቁ መሪዎችና አባላት ኖሯቸው፣ ጽሕፈት ቤት ከፍተው፣ ደንብና መመሪያ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ ባለመሆናቸው የሲዳማ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄም ግራ መጋባት ውስጥ ሲገባ ይታያል።

በሲዳማ ዞን ለሚካሔዱ ዘመቻዎች ኤጀቶዎችን ማመስገን በሚሰማበት በዚህ ጊዜ በተቃራኒው ለሚደርሱ ዝርፊያዎች፣ ዘረኛነት ያጠላባቸው የጥላቻ ድርጊቶችና ሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራት ኤጀቶዎች ተጠያቂ ሲደረጉ መስማት የተለመደ ጉዳይ ነው። ተጠሪውና መሪው እኔ ነኝ ብሎ በይፋ የሚቀርብ ቡድንም ሆነ ግለሰብ ስለሌለ የዚህ አካባቢ ሕዝብ እውነተኛ መንግሥት እንደሌለና ብዙ ስውር መንግሥታት እንደተጫኑበት ሆኖ እየተሰማው ነው።

መጠነ ሰፊ ዘመቻ የሚያካሔዱና ብዙ ተከታዮች ያሏቸው የኤጀቶዎች፣ የሲዳማ ሕዝብ፣ የሐዋሳ ከተማ ወዘተ ድምጽ ነን የሚሉ በርካታ ማኅበራዊ ሚዲያዎችና የማኅበረሰብ ትስስር ገጾች አሉ። ሐዋሳ ፍቅር፣ ሲዳማ፣ ሲዳማ ፔጅ፣ ሐዋሳ የኛ፣ ኤጀቶ ወዘተ የሚባሉ ግለሰቦች ወይም ቡድኖች የሚዘውሯቸው ብዙ መቀስቀሻ ገጾች አሉ። እነዚህ መቀስቀሻ መድረኮች በየጊዜው ከሚያስተላልፏቸው መልዕክቶች በመነሳት በሲዳማ ሕዝብ እና በኤጀቶዎች ሥም ከሚንቀሳቀሱት ግለሰቦችና ቡድኖች መካከል ዲጂታል ወያኔና አፍቃሪ ኦነግ እንደሚገኙባቸው መረዳ ይቻላል።

ዲጂታል ወያኔ ሆነው በኤጀቶ ወይም በሲዳማ ሥም የሚንቀሳቀሱት ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ኤጀቶ ወይም የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ለውጡን የሚቃወምና ዘመነ ሕወሓትን ናፋቂ እንደሆነ አድርገው ለማሳየት ሲሞክሩ አፍቃሪ ኦነግ የሆኑት ደግሞ የኤጀቶና የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ኢትዮጵያዊ አይደለንም የሚል መንፈስ ያለበት ንቅናቄ መስሎ ይታይ ዘንድ ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ናቸው። የሲዳማ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ኤጀቶ ነን የሚሉ ሌሎች ወገኖች እነዚህን ኹለት ዓይነት አካሔዶች በስጋት ዓይን እየተመለከቷቸው የቆዩ ሲሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ የኦሮሞ አክቲቪስቶች፣ በአክራሪ ኦነጎችና በኦዴፓ ሰዎች በኩል በአደባባይና በየሚዲያው ላይ የሚሠሩ ድራማዎች ስጋታቸው ከልክ አልፎ እንዲንር አድርጎባቸው ‘ጥያቄአችን ሞግዚት እንፈልጋለን የሚል አይደለም’ እስከ መመካከርና ሐሳብ እስከ መለዋወጥ አድርሷቸዋል።

ምክትል ከንቲባ ታከለ ዑማ የፊቼ ጫምበላላን በአዲስ አበባ ለማክበር ያደረጉት እንቅስቃሴ፣ የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዘደንት በዐሉ ላይ የክብር እንግዳ መሆን፣ የጃዋር ሞሐመድ በከፍተኛ የታጣቂወች አጀብ በዐሉን መታደም እና የመሳሰሉት ፍጻሜዎች ብዙም ትርጉም የሌላቸው ቢመስሉም, በማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲዘፈኑ ከቆዩት ኦነጋጋሪያዊ መዝሙሮች አንጻር ሲቃኙ የኦሮሞ ቡድኖች ሲዳማን ወደ ኦሮሚያ ለመጠቅለል ወይም ሲዳማ በኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ሞግዚት ሥር ሆኖ ይተዳደር ዘንድ ዳር ዳር እየተባ እንደሆነ ተደርጎ ለመታየት በቅቷል። ይህ ደግሞ ወያኔ ‘ታንኩንና ባንኩን’ ተቆጣጥሮ በነበረበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን አሁን ዳር በተገፋበት ጊዜም አፋርን ለመጠቅለልና የአፋር ሞግዚት ለመሆን ከሚደርገው ሩጫ ጋር ተመሳሳይ ነው።

ከአስመሳይ ኤጀቶ ማኅበራዊ ሚዲያዎች አንዱ በኢትዮ-ሶማሊያው ጦርነት የኦሮሞና የሲዳማ ቡድኖች ከዚያድ ባሬ ጎን ተሰልፈው ኢትዮጵያን ለማውደም ተባብረው የሠሩበትን አጋጣሚ አውስቶ ይህ ወቅት ያንን ለመሰለ ጸረ-ኢትዮጵያ ትብብር ትንሳኤ በመስጠት ከኢትዮጵያ ቅኝ ግዛት ነጻ የምንወጣበት ጥሩ አጋጣሚ ነው ብሎ ሲሰብክ ተስተውሏል። እርግጥ ነው በቅጥረኛነት ተሰልፈው ከወራሪ ጠላት በተጓዳኝ አንዳንድ የሲዳማና የኦሮሞ ተወላጆች የነበሩ ቢሆንም እነዚያ ቅጥረኞች በኢትየጵያውያን ክንድ፣ ሲዳማዎችንና ኦሮሞዎችን ባካተተ ጀግንነት ከነሶማሊያዊ ጌቶቻቸው ሽንፈት ተከናንበዋል።

የሲዳማዎች ጥያቄ የኦሮሞ ሕዝብ ያገኘውን ዓይነት መብት ምንም ሳይሸራረፍ ለማግኘት እንጅ ትግራይ ውስጥ የሚገኙ የኢሮብና የኩናማ ሕዝቦች የሚደርስባቸውን ዓይነት ልዩ ድፍጠጣ እንዲደርስባቸው አይደለም። የሲዳማዎች ጥያቄ ለመጠምዘዝ የሚመኙ ግለሰቦችና ቡድኖች ሕወሓት ትግራይ ውስጥ ሊያራምደው የሞከረውን ጉዳይ የሚያስታውስ ነው። ሕወሓት በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ አማራ ያልሆኑ ሕዝቦች ልዩ ዞን ወይም ልዩ ወረዳ እየሆኑ እንዲተዳደሩ አድርጓል።

ሕወሓት ይህን ያደረገው ለሕዝቦች አሳቢ ሆኖ አይደለም። አማራ ክልልን የማዳክምና የአማራን ሕዝብ ለመጉዳት በተለይም የአማራ ወጣቶችን ሥራ የማግኘት ዕድል ለማጥበብ ስላሰበ ነው።

ይህ የሕወሓት ሴራ ግን በክልሉ የሚገኙ ሌሎች ብሔረሰቦችን ከመጥቀሙ በተጨማሪ ከአማራው ሕዝብ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖራቸውና ቀድሞ ክፍል ሃገር በሚባል አከላል ጊዜ የነበረው ዓይነት አብሮነት፣ በጋብቻ መዋሐድ፣ በመልካም ጉርብትና ተሳስቦ መኖርን የመሣሰሉ ጥሩ ነገሮችን አስገኝቷል። እነዚህ መልካም ነገሮች አማራውን ጨምሮ በእነዚህ ብሔረሰቦች ውስጥ የተሰገሰጉ የሕወሐት ቅጥረኞችና አድር ባዮች ችግር ፈጥረው መለስተኛ ግጭቶች ከተከሰቱበት ውጭ ባለው ጊዜ ሁሉ በጥሩ ሁኔታ ቀጥለዋል።

በአማራ ክልል ላይ የተጣሉት ለየት ያሉ ነገሮች ወደ መልካም አጋጣሚ ቢለወጡም ሕወሐት በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሌሎች ብሔረሰቦች አሁን ባሉበት ሁኔታ ውስጥ እንዲገኙ ያደረገው ለአማራ ሕዝብ ካለው ዕድሜ ጠገብ የጠላትነት መንፈስ ተነድቶ ብቻ መሆኑን የሚያጋልጡ ኹለት ፍጻሜዎች አሉ። እነሱም፡-
(1ኛ) ይህን መሰሉን አደረጃጀት ለታላቁ የሲዳማ ሕዝብ ተግብሮት (ሲዳማን ክልል አድርጎ) በዙሪያውና በውስጡ ያሉ ትንንሽ ብሔረሰቦችን በልዩ ዞን፣ በልዩ ወረዳ ወዘተ በማካተት ትልቁ የሲዳማ ሕዝብ የክልል ባለቤት እንዲሆን ባለመፈለጉ፣

(2ኛ) ሕወሓት ትግራይን ክልል አድርጎ የክልሉን የሥራ ቋንቋ ትግርኛ ካደረገ በኋላ ከራሱ ጋር የጠቀለላቸውን የኢሮብ (ሳሆ) እና የኩናማ ሕዝቦችን ማንነታቸውንና ቋንቋቸውን ትተው ትግሬ እንዲሆኑ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን በመሥራቱ ሕወሓት ለሕዝቦች መብት ተቆርቋሪ መስሎ የሚታየው ከአንገት በላይ መሆኑን ከማሳየቱም በላይ ሕወሓት ይህን አሰራር የዘረጋው ለኢትዮጵያዊም ለትንንሾቹ ብሔረሰቦች ከሚሰጠው ጥቅም ይልቅ የሚያደርሰው ጉዳት ትልቅ መሆኑን ከግምት ውስጥ በመክተት መሆኑን ያጋልጣል።

ለብሔረሰቦች አሳቢ መስሎ የሚታየው [ሕወሓት] ከፋፋይ ሴራውን ለማራመድ እንጅ ለሕዝብ በማሰብ አይደለም። ወደ ትግራይ ጉዳይ እንደገና እንመለስ፤ የሕወሓት አንደበት የሆነው ድምጺ ወያኔ በኢሮብና በኩናማ ቋንቋዎች የአንድም ደቂቃ ፕሮግራም ሳይኖረው እንደ ቅኝ ግዛቱና እንደ አማራጭ የሀብት ምንጩ እየተጠቀመበት ላለው ለአፋር ክልል የሚሠራጭ የአፋርኛ ፕሮግራም ማዘጋጀቱ የኹለቱን (የኢሮብንና የኩናማን) ሕዝቦች እያበሳጨና እያሳዘነ የቆየ ጉዳይ ነው።

የኢሮብና የኩናማ ሕዝቦች በልበ ቅን የትግራይ ተወላጆች በተለይም መቀሌ ዩንቨርሲቲ ውስጥ በሚሠሩ ጥቂት ተጋሩ ምሁራን ታግዘው ማንነታቸው እንዲከር ያረጉት መጠነ ሰፊ ሰላማዊ ተጋድሎ እስክ ምርጫ 1997 ውጤት አልባ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ጥረት ውጤት ማምጣት የጀመረው ምርጫ 1997 ላይ የኢሮብ ሕዝብ ምርጫውን በጥብቅ ክትትል ከመጭበርበር ታድጎ፣ ለምርጫ የቀረበውን የሕወሓትን ተወካይ ችላ ብሎ ድምጹን ለአካባቢው ተወላጅ ሰጥቶ አሸናፊ ካደረገው በኋላ ነው። በእርግጥ በኢሮብ የተደረገው ምርጫ በአባዱላ ገመዳ፣ በጁኔዲን ሳዶ፣ በበረከት ስምዖን ወዘተ… የተፈጸመው ዓይነት ጥቃት ደርሶበት ሕዝብ የመረጠው በጠላትነት ተፈርጆ የሕወሓት ተወካይ የአካባቢውን ሕዝብ ወከለ ተብሎ የምርጫው ሩጫ ተደምድሟል። ነገር ግን የኢሮብ ሕዝብ ማንነቱንና ቋንቋውን የማስከበር ትግሉ ቀጥሎ አሁን ትግሬ አለመሆኑ ታምኖለት ትግርኛ ተናጋሪ እንዲሆን የሚያበረታቱ የሕወሓት ካድሬዎችና የድምጺ ወያኔ ጋዜጠኞች አርፈው እንዲቀመጡ አድርጓል። የኩናማ ሕዝብ ትግል ግን ገና በመቀጠል ላይ ነው።

ይህን ሁሉ ታሪክ ለማየት የተገደድነው የሕወሓትን የግዛት አከላለልና አደረጃጀት ራሱ በቀየሰው መንገድ ብቻ እየተመለከትን የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ችላ እየተባለ የሲዳማ ሕዝብ ያረጀና ያፈጀውን የሕወሓት ቁማር ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ የተጣለበትን ‘ግዳጅ’ ተሸክሞ ይኑር ብለን ከመከራከር እንድንቆጠብ ብቻ ሳይሆን ሕወሓት የሞከረውን ሲዳማን የማሳነስ ሙከራ የኦሮሞ ብሔርተኞች በአዲስ መልክ ሊተገብሩት ከመሯሯጥ ይቆጠቡም ጭምር ለማሳሰብ ነው። ኦነጋውያን ‘ስትፋቁ ኦነግ ትሆናላችሁ’ የተባሉትን ኦሕዴዳውን ጨምሮ የሲዳማ ሕዝብ ጥያቄ ራስን በራሱ የሚያስተዳድር የሲዳማ ክልልን ዕውን ማድረግ እንጅ የማንም ተለጣፊ መሆን አለመሆኑን መረዳትና ሳይወዱም ቢሆን ሊቀበሉት ይገባቸዋል። ኮሶ ለመድኀኒትነት እየመረረ እንደሚጠጣው ሁሉ ለአካባቢው ጤናማ ሰላም ሲባል የሲዳማ ሕዝብ ቅቤ አንጓች መስለው የሚታዩ ግለሰቦችና ቡድኖች ሁሉ መራሩን የሲዳማውያን የክልልነት ሀቅ ሊቀበሉት ይገባል። ኦሮሞ ለሲዳማ ጥሩ ወንድምና ጎረቤት እንጅ ሞግዚት ወይም ገዥ ሊሆን አይችልም።

የኦሮሞ ብሔርተኞች የሕወሓትን ፈለግ ተከትለው ጣሊያኖች የጀመሩትን አገር የማካለል ዘመቻ ለማስቀጠል ሕልም ያላቸው ይመስላል። ጣሊያን ምሥራቅ አፍሪካን በጉልበት ወርሮ በያዘባቸው ዓመታት ይህን የአፍሪካ ክፍል በኮሚሳሪያቱ ሥር በሚተዳደሩ ክልሎች ሲከፋፈለው ከክልሎቹ አንዱ ሲዳማ-ኦሮሞ ሲል የከለለው ክልል እንደነበረ ይታወቃል። ይህ የጣሊያን አከላለል ለአንዳንድ ኦሮሞዎች ሕልም ሆነ ማለት የሲዳማ ሕዝብ የክልለ ጥያቄ በሞሶሎኒያዊ ዘዴ ቅዥት ይሆናል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሊታሰብ የማይገባው ነው። የሲዳማዎች ሕልም ዕውን መሆን አለበት። የሲዳማን ሕዝብ ሕልም ለራሳቸው ጥቅም ሊጠመዝዙ የሚፈልጉ ሰዎች ምኞት ደግሞ መምከን ይገባዋል።

ሁሉም ራሱን ይቻል። ያኔ ባለ ጊዜ የነበረው ሕወሓት ኩናማንና ኢሮብን በጨፈለቀበት አካሔድ ባለ ተራ ነን ባዮች ሲዳማን የመጨፍለቅ አካሔዳቸውን በጊዜ ሊያቆሙት ይገባል። አንተ ባለ ክልል እንደሆንከው እነሱም የራሳቸው ክልል እንዲኖራቸው ነው የሚፈልጉት። ባለ ተራ ነን ባዮች በጣም ብዙ ቅዠታቸውን በየቦታው ሊተገብሩት ዳር ዳር ሲሉ እየታዩ ነው። ታንኩንና መድፉን እየተጠቀሙበት የሚያውቁት ያልተሳካላቸው እምቡ-እምቡር ባይነትና የአፍሪካ አርዓያንነት ታንኩንና መድፉን በፎቶ ለሚያውቁት ጭራሽ ባይሞከር ይሻላል። ልብ ያለው ልብ ይበል! ሲዳማዎች ‘እኛ ሞግዚት አስፈልገንም አንተም ራስክን ቻል’ እያሉ ነውና አዳሜ ሆይ ራስህን ቻል!

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here