የሕፃናት ማቆያ ጉዳይ

0
1191

የሕፃናት ማቆያ ለሴት ሠራተኞች የሥራ ላይ ውጤታማነት የሚጫወተውን ሚና ከፍተኛነት የጠቀሱት ቤተልሔም ነጋሽ, በአንዳንድ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የተጀመረው የሕፃናት ማቆያ ስፍራዎች ማዘጋጀት የሚበረታታና ተጠናክሮ መቀጠል የሚገባ መሆኑን ገልጸው ብዙ ርቀት መጓዝ እንደሚቀር ግን የአገራት ልምዶችን በማጣቀሻነት አቅርበዋል።

 

አዲስ ዓመት ሲመጣ፣ አንዱ የትምህርት ዓመት አልፎ የሚቀጥለው መወራት የሚጀምርበት ግንቦትና ሰኔ ወቅት ሲመጣ ከትምህርት ቤት ክፍያ መጨመር ጋር በተያያዘ የወላጆች ሮሮ መሰማት ይጀምራል። አንዳንድ መገናኛ ብዙኀንም የወላጆችን ድምጽ ያስተጋባሉ። የግል ትምህርት ቤቶችንና የወላጅን የዋጋ ልጨምር አትጨምርም ግብግብ በሌላ ቀን እመለስበታለሁ።

የዛሬ ርዕስ ልጆች ለመደበኛው ትምህርት፣ በመንግሥት መመዘኛ መሠረት አራት ዓመት ሞልቷቸው መዋዕለ ሕፃናት ትምህርት ቤት ከመጀመራቸው በፊት ያሉት ጊዜያት የሚያስፈልጋቸው የሕፃናት ማቆያ ሥፍራን የሚመለከት፣ በእነኝህ ጊዜያት በሠራተኛ ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጫናና በዚህ ረገድ የሚያስፈልገውን ሥራ ለመጠቆም የታለመ ነው።

በተሻለ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ በሚገኙ የዓለም አገራት ሳይቀር ሴቶች ከወንዶች ይልቅ የቤተሰብና የሥራ ሕይወትን አመጣጥኖ በመሔድ ረገድ ችግር እንደሚገጥማቸውና ከፍተኛውን ጫና እንደሚሸከሙ ጥናቶች አረጋግጠዋል። በየትኛውም የመደበኛ ቅጥር ሥራና የፕሮፌሽናል ደረጃ ያሉ ሴቶች፣ በከፍተኛ አመራር ላይ ያሉት ሳይቀር፣ ከሥራ በተጨማሪ የሥራ ውጤታማነታቸው ላይ ተጽእኖ እስከሚኖረው ድረስ ቤትንና ልጆችን የማስተዳደር ኀላፊነትን ለብቻቸው ይይዛሉ። ደርግ “ድርብ ጭቆና” ይለው እንደነበረው በሥራና ቤተሰብ በማስተዳደር መካከል ይወጠራሉ። ማስታወቂያዎቻችን ሳይቀር የሚነግሩን ባልና ሚስት እኩል ከሥራ ገብተው ልጆቻቸውን ካገኙ በኋላ ሚስት ልብስ ቀይራ ወደ ጓዳ ስትገባ ባል ሶፋ ላይ ጋደም ብሎ፣ ሪሞት ኮንትሮሉን ይዞ ቴሌቪዥኑን ሲያይ ነው። ማስታወቂያው መሆን የሌለበትን በማሳየቱ ብንወቀሰውም በአብዛኛው እየደገመልን ያለው የምንኖረውን ነው። ሴት ባለሥልጣናትን ስለስኬታማነታቸው ሲወራ በየሚዲያው ሳይቀር “ከልጆች ከቤተሰብ ጋር እንዴት ቻልሽው?” ተብለው ይጠየቃሉ። ለወንድ ኀላፊዎች ይህ ጥያቄ አይቀርብም፣ ቤተሰብ ይኑራቸው አይኑራቸው ከግምት ገምቶ መረጃ አይጠየቁበትም፤ ስለ አባትነት እንዲያወሩ ሲበረታቱም ሆነ ወንዶች የተሻለ የቤት ውስጥ ኀላፊነት ተሳትፎ እንዲኖራቸው ሲነገርም አይሰማም። ጠቅላይ ሚኒስትራችን ሳይቀር ሴቶች ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን በአጠቃላይ አገርን በትከሻቸው መሸከማቸውን ሲያሞካሹ እንጂ ረ ከትከሻቸው እንውረድ/ውረዱ ሲሉ አይሰማም።

በአሜሪካ በሠራተኛ ወንዶችና ሴቶች ላይ በተደረገ ጥናት የቤት አስተዳደር፣ በተለይም ልጆች ከተወለዱ በኋላ የሚኖረው የመንከባከብ ኀላፊነት፣ በሥራቸው ገፍተው የተሻለ ደረጃ ላይ እንዳይደርሱ አድርጓቸው እንደሆነ በቀረበላቸው ጥያቄ አዎን የሚል መልስ የሰጡት ወንዶች በጥናቱ ከተሳተፉት 16 በመቶው ሲሆኑ ሴቶች 51 በመቶው ነበሩ።

ለተመሳሳይ ሥራና ደረጃ እኩል ክፍያ ማግኘትን አስመልክቶም ወንዶችና ሴቶች ጀማሪ ሠራተኞች ሆነው ሲቀጠሩ ያለው ልዩነት አነስተኛና የተቀራረበ የሚባል ሲሆን በሥራ ልምድ እየጨመሩ ወደ ላይ ከፍ ማለት ሲጀመር ቤተሰብ የመሠረቱ ሴቶች ቤተሰብና ሥራን እኩል የማስኬድ ትግል ውስጥ ሲገቡ፣ ከወንዶች እኩል ለመሔድ ይቸገራሉ።

በግሌ በሥራ ዓለም የገጠመኝ ተግዳሮት ከሥራ ጋር የሚገናኝ ሳይሆን፣ በየትኛውም መመዘኛ የተሻለ ሁኔታ ላይ መሆኔ እንዳለ ሆኖ፣ ቤት ውስጥ ከሥራ በተጨማሪ የቤት ውስጥ አስተዳደርን ማከናወን የሚጠበቅብኝ መሆኑ ያመጣው ጫናና ሥነ ልቦናዊ ጉዳት ነው። ልጆቼ በጨቅላነታቸው ቤት መቆየት በሚገባቸው ዕድሜ የሕፃናት ማቆያ ገብተዋል። በከተማችን አዲስ አበባ በየትኛውም የመኖሪያ አካባቢ የተሻሉ የሚባሉትን ብንተው መሠረታዊ ነገሮችን ያሟሉ ማቆያዎች ሳይቀር የሚጠይቁት ዋጋ መካከለኛ ደረጃ ላይ ላለ ደሞዝተኛ ጨርሶ የሚቀመስ አይደለም። ለብዙ ሠራተኛና ቤተሰብ ያንን ገንዘብ ከፍሎ፣ ትራንስፖርት አመቻችቶ በዚያ ላይ ጠዋትና ማታ ማመላለስ የሚያስከትለው ወጪ ከደመወዝ በላይ ይሆናል። የተሻለ ገቢ ላለው ቤተሰብ ሳይቀር ከሥራ ሰዓት ጋር ካልተስማማ ልጆች ሕፃናት ሆነው ለአፀደ ሕፃናት ያለ ዕድሜ ላይ እስኪደርሱ ድረስ ያለው የመጀመሪያው ሦስት ዓመት ሥራ ለምትሠራና የቤተሰቧ ድጋፍ ለሌላት ሴት እጅግ ፈታኝ ነው። ስለሆነም በየትኛውም ሁኔታ የተሻለ የሚከፈለው ሠራተኛ ቀጥሮ ልጆችን ቤት ለማቆየትና ሥራ ለመቀጠል ውሳኔ ይደረስና በዚህ መካከል ሴቶች ላይ ሥነ ልቦናዊ ጫና፣ ቤተሰቡ ላይ ደግሞ የፋይናንስ ጉዳት ይደርሳል።

በለጋ ዕድሜ ላይ ያሉ ሕፃናትን፣ እንደ አዲስ አበባ ባለው መካከል ላይ ብቅ ብሎ የማየት ዕድል ጨርሶ በሌለበት፣ ተገቢው ሥልጠና ለሌላቸው የቤት ውስጥ ረዳቶች ትቶ ሥራ ላይ ሙሉ ትኩረትን አሳርፎ ውጤታማ ለመሆን መሞከር በራሴ እንዳየሁት ከባድ ነው። የቤት ሠራተኞች ድንገት እንሒድ ሲሉ ከሥራ መቅረት በአብዛኛው የእናት ኀላፊነት ነው። ሥራ ቦታ መከናወን ያለበት አስቸኳይ ሥራ ካለ ወይ መስክ መውጣት ሲኖር ጉዳዩ የበለጠ ውስብስብ ይሆናል። ተጨማሪ የሥራ ጫና ባለበት፣ ሥራ ላይ ሙሉ ትኩረትን ማሳረፍ በማይቻልበት፣ ሴቶች ሥራ እንዲቀጠሩ ማድረግ ወይም የሥራ ዕድል ማመቻቸት ብቻውን በቂ አይደለም።

ሴቶች በሥራቸው ከወንዶች እኩል ውጤታማ ብቻ ሳይሆን፣ ቦታ እንዲሠጣቸውና ዕድገት እንዲያገኙ የተሻለ መሥራት ይጠበቅባቸዋል። የቤት ውስጥ ኀላፊነቱ ወደ ኋላ እንደሚጎትታቸው ማንም አያስበውም፤ ትውልድ የመተካት ኀላፊነታቸውም እንደጉድለት ይታያል። በሠራተኛ ሴቶች ወደ ሥራ ዓለም ለመግባት የሚደረግባቸው ልዩነት ወጣት ሴቶች ሲቀጠሩ ገና ለገና ያገባሉ፣ ይወልዳሉ በሚል ልዩነትና አድልዎ ይደረግባቸዋል። የመቀጠር ዕድልም ካገኙ በኋላም ቢሆን ከጥቂት ዓለም ዐቀፍ ተቋማት በስተቀር በተለይ ልጆቻቸው ሕፃናትና የእነሱን በቅርብ መኖር የሚፈልጉ በሚሆኑበት ወቅት ሥራና እናትነትን አመጣጥነው እንዲሔዱ ድጋፍ አያደርጉላቸውም።

አንዳንዶች ልጆችና ሥራ መካከል ከመወጠራቸው የተነሳ መሥራታቸው ከመጥቀም ይልቅ ጫና ሲሆንባቸው ሥራቸውን ትተው ቤት ይውላሉ። በአሜሪካ ከላይ በጠቀስኩት ጥናት ከተካተቱ ሴት ሠራተኞች መካከል ለምሳሌ 42 በመቶው በሥራ ሕይወታቸው የሆነ ወቅት ልጆች መንከባከብ ስለነበረባቸው የሥራ ሰዓታቸውን ለመቀነስ ወይም ለሆነ ጊዜ ለማቆም ተገደዋል። ጭራሽ ሥራ ለመተው ተገደው የነበሩት ደግሞ 27 በመቶ ናቸው። የወንዶቹን ስናይ ሥራ ትተው ቤት ልጅ የሚያሳድጉ አባቶች ቢኖሩም ቁጥራቸው ከ10 በመቶ አይበልጥም። ወደ አገራችን ስናመጣው በተለይ የዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ላሉት አንዳንዴ አለመሥራት የማይቻልበት ሁኔታ ይኖራል፤ ልጆችን ለአያቶቻቸው ከመስጠት አንስቶ ሰፈር ውስጥ እንዲውሉ ሆነው ለጥቃት እንዲጋለጡ እስከማድረግ፣ በተመጣጣኝ ዋጋ የልጆች ማቆያ አለመኖር ያመጣቸው ጣጣዎች ናቸው። ሥራ ትቶ ለመቀመጥም በቂ ሌላ ገቢ ያስፈልጋል፤ ያም ለብዙው ሰው ቅንጦት ነው።

የአንዲት አገር ዕድገት ጉዞ ቢያንስ ከአጠቃላይ ሕዝቧ ግማሽና ለዚያ የቀረበ የሚሆኑት ሴቶችን ወደ ኋላ ትቶ የማይታሰብ መሆኑ ያስማማናል ብንል በመደበኛም ይሁን ኢ-መደበኛ የሥራ መስክ ላይ የተሠማሩ ሴቶች ውጤታማ እንዲሆኑ፣ የሚጠበቅባቸውንም አስተዋጽዖ እንዲያበረክቱ ለማድረግ እንደ የቤት ውስጥ የሥራ ጫናና ድርብ ኀላፊነትን ልናቃልላቸው የግድ ነው። በፖለቲካ ተሳታፊ እንዲሆኑ፣ በግሉ ሴክተርም ወደ ኀላፊነት እንዲመጡ የተሻለ ስኬታማ እንዲሆኑ ሥራቸው ላይ የሚያሳልፉት ሰዓት ሊጨምር፣ ራሳቸውን በትምህርትና በሥልጠና ለመደገፍም ከሥራ ሰዓት ውጪ በሥራና በትምህርት ተጨማሪ ሰዓታት እንዲያሳልፉ ግድ ይላል። ይህን ለማድረግ ደግሞ በመደበኛው ሁኔታ የሚጠበቅባቸው የቤት ውስጥ ሥራ ለእነሱ ብቻ መተው ማብቃት ይኖርበታል። አባቶች ልጆችን ማሳደግ ሥራ ውስጥ እንዲሳተፉ ማድረግ ብቻ ሳይሆን በተመጣጣኝ ዋጋ፣ ቢቻል በነፃ የልጆች ማቆያ ሊዘጋጅ የግድ ይላል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሴቶችን ለሥልጣን አላበቃችሁም ሲባሉ ጫካ አብረው የታገሉትን ሴቶች ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ በትነው ወንዶቹን ብቻ እንዳላቆዩ፣ ወደ ሥልጣንም እንዳላመጡ ሁሉ “የሉም ከየት እናምጣ?” ሲሉ፣ እንደ መንግሥት አካል የፆታ እኩልነትን እናሰፍናለን ተብሎ ፖሊሲ ቢወጣም ተግባር ላይ ሳይሠራ ሲቆይ፣ በተለይ ሴቶች ላይ ያለውን ድርብ ጫና ቸል ማለታቸው ውጤታማ እንዳይሆኑ ስለሚያደርግ የተሻሉ ሴቶች እንዳይመጡ አስተዋጽዖ እያደረጉ እንደነበር ረስተውታል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ከዚህ በፊት እንደገለጽኩት፣ ሌሎችም እንዳሉት የሴቶችን ጫና እንደ በጎ ነገር ሲያሽሞነሙኑ ምናልባት የሴቶችን የሥራ ጫና ለመቀነስና ውጤታማነታቸውን ለማሳደግ በመንግሥት ተሠሩ ከሚባሉት ተግባራት መካከል በፐብሊክ ሰርቪስ ውስጥ ተቀጣሪ ለሆኑ ሴት ሠራተኞች የሕፃናት ማቆያ እንዲዘጋጅ ከኹለት ዓመት በፊት ገደማ መመሪያ ማውጣት አንዱ ይመስለኛል። ሁሉም መሥሪያ ቤቶች ተግባራዊ አለማድረጋቸው እንዳለ ሆኖ (ትንሽ ቆየት ባለ መረጃ መሠረት 56 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕፃናት ማቆያ ሥፍራዎችን አዘጋጅተዋል) የፐብሊክ ሠርቪስ አውቶብሶችን ለልጆቻቸውም ጭምር እንዲጠቀሙ መፈቀዱ (ምንም እንኳን መጀመሪውኑ ይህ አለመታሰቡ የሚያስገርም ቢሆንም) ተጨማሪ መሥሪያ ቤቶችም ሕፃናት ማቆያዎችን እያዘጋጁ መሆናቸው ጥሩ ለውጥ ነው።

ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የሴቶች ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴርና የፐብሊክ ሰርቪስ ሚኒስቴርም አዋጁን መተግበር ባልጀመሩ መሥሪያ ቤቶች ላይ ክትትልና ጥናት ካስፈለገም ድጋፍና ልምድ ልውውጥ በማዘጋጀት ወደ ተግባር እንዲገቡ ሊያደርግ ይገባል። የግል ተቋማትም ቀስ በቀስ ወደዚህ በጎ ተግባር እንዲገቡ በታክስ እፎይታና በተጠኑ ሌሎች እርምጃዎች ማበረታታት ተገቢ ነው።

እዚህ ላይ መመሪያው ማካተት አለበት ብዬ የማስበው ሌላው ነገር የሕፃናት ማቆያው ለሴት ሠራተኞች ብቻ ሳይሆን ወንድ ሠራተኞች ልጆቻቸውን እንዲያመጡ ማበረታታት ማካተት ነው። ጡት የሚጠቡበትን ዕድሜ እንኳን ባይቻል ከዚያ አለፍ ብሎ ትምህርት ቤት እስኪገቡ ባለው አንድ ወይም ከኹለት እስከ ሦስት ዓመታት ልጆቻቸውን በማቆያው እንዲያስቀምጡ ማድረግ ቢቻል በተዘዋዋሪ ባለቤቶቻቸው ምርታማ እንዲሆኑ ይረዳል፤ ልጅ ማሳደግ ለሴቶች ብቻ የተተወ ነው የሚለውን አመለካከትም ለመቀየር ያግዛል።

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here