መሪዎች አርዓያነታቸውን ያሳዩ!

0
855

በቅርቡ በመላው የሙስሊም ማኅበረሰብ የተከበረውን ኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቀደም ብለው ባቀረቡት ጥሪ መነሻነት ከክርስቲያኖች ጋር በመሆን ሕዝብ ሙስሊሙ በዐሉን በሚያከብርበትና በሚሰግድበትን አዲስ አበባ ስታዲየም ውስጥና ዙሪያውን በኅብረት ጽዳት አካሒደዋል።

ይሔ የጽዳት ክንውን ወትሮ ይደረግ እንደነበረው በቀላሉ መታየት የለበትም፤ ምክንያቱም ተምሳሌታዊ ፋይዳው ዘርፈ ብዙ በመሆኑ።

ክርስቲያኖች የሙስሊሙ ማኅበረሰቡ የሚያከብረው በዐል አስታኮ ጽዳቱ ላይ መሳተፉ በልዩነት መካከል መቻቻልና መከባበር እንዲሁም የአብሮነት ምስክርነት መገለጫ ነው። ከዚህም አለፍ ሲል ሁሉም ሃይማኖቶች ለፍቅር የሚሰጡትን አስተምኅሮ በተግባር ያሳየ ሆኖ አልፏል።

በተመሳሳይም በቅርቡ በደማቅ ሁኔታ የተከበረውንና በተባበሩት መንግሥታት በትምህርት፣ ሳይንስና ባሕል በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው የሲዳማዎች ዘመን መለወጫ ፊቼ ጫምበላላ በዐል በዋናነት በሲዳማዎች ይከበር እንጂ ከመላው ኢትዮጵያ በዐሉን ለመታደም ሰዎች መሰባሰባቸው ተዘግቧል። ፊቼ ጨምበላላ ከዘመን መለወጫ በዐልነቱ ጎን ለጎን የፍቅር፣ የአንድነት እና የመቻቻል ተምሳሌታዊ ፋይዳው ጎልቶ ታይቷል፤ ይህም የአገር ሰላምና ደኅንነት ከማስጠበቅ አንጻር የሚያበረክተው ሚና አዎንታዊ ነው።

ኢድ አልፈጥርና ፊቼ ጫምባላላን የመሳሰሉ ማኅበረሰቡን በሰፊው የሚሳተፍባቸውን በዐላት በደንብ መጠቀም እስከተቻለ ድረስ ለአገር መረጋጋትና ደኅንነት እንዲሁም ለዘላቂ ሰላም መስፈን ወሳኝ ሚና ይጫወታሉ ብላ አዲስ ማለዳ ታምናለች። በተለይ በፖለቲካ፣ በሃይማኖትና ሌሎች ተቋማት መሪዎች ፊታውራሪነት የሚደረገው እንደዚህ ዓይነት ተግባራት ተምሳሌታዊ ፍይዳቸው ሰፊ፣ የማኅበረሰቡን አመለካከት ላይ የሚኖራቸው በጎ ተጽዕኖ ከፍተኛ እንደሚሆን ይታመናል። በመሆኑም የመሪዎቻችን አርዓያነት ያለው ተግባር የማኅበረሰቡን አመለካከት በጥሩ መንገድ ለመቅረፅ የሚያበረክተው ፋይዳ ብዙ በመሆኑ ሊበረታታ ይገባል።

በሌላ በኩል ደግሞ እሁድ፣ ግንቦት 18/2011 በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ በደቦ ፍርድ የአንድ ተማሪ ሕይወት መነጠቁ ተሰምቷል፤ ሌሎች ሦስት ተማሪዎች ላይም ጉዳት ደርሷል። የግድያውና የጥቃቱ መንስኤም ከብሔር ጋር የተያያዘ መሆኑ ተዘግቧል። ይህንን ፀያፍ ድረጊት ለመበቀል በሚመስል መልኩ ደግሞ በያዝነው ሳምንት ማክሰኞ፣ ግንቦት 27/2011 አክሱም ዩኒቨርሲቲ ውሰጥ በተነሳ ብጥብጥ የአንድ ተማሪ ሕይወት ለህልፈት ሲዳረግ ሌሎች ዐሥር መቁሰላቸው ተዘግቧል። በተጨማሪ ረቡዕ፣ ግንቦት 28 ሌሊት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ በተነሳ ግጭት ከዐሥር በላይ ተማሪዎች መጎዳታቸው ተሰምቷል።

በንጽጽርና በተሻሻለ ሁኔታ ልዩነትን በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመደማመጥ መፍታት ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የችግሩ ዋነኛ ተዋናይ መሆናቸው ያሳዝናል። የትምህርት ከፍተኛ በጎ ተጽዕኖ ፈጣሪነትና የባሕሪይ ለውጥ አምጪነት የተዛነፈ ለመሆኑ ከእነዚህ ድርጊቶች በላይ ምስክር ከየትም ሊመጣ አይችልም።

የበለጠ አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ የፖለቲካ ልኂቁ ወይም በልኂቁ ተጽዕኖ ሥር የወደቁትና በስሜት የሚነዱ ወጣቶች የተፈጸመውን ድርጊት መነሻ ምክንያት ምን እንደሆነና እንዴት እንደዚህ ዓይነት አስነዋሪ ድርጊት ሊፈጸም ቻለ የሚለውን ከመመርመር ይልቅ እንዴት አድርገን የአፀፋ ምላሽ እንስጥ የሚለው አሳስቧቸው በየማኅበራዊ ትስስር መድረኮች ላይ የክተት አዋጅ ሲያውጁና የበቀል ሰይፍ ሲስሉ ከርመዋል። “(እከሌ) የተባለው ብሔር ሬሳ አይቀበልም” እስከሚል ማስፈራሪያ አይሉት ማሳሰቢያ ሲለቁ ከርመዋል። ይህ ጉዳይ ከማሳዙኑም በላይ የሞራል ልዕልናችንን በዚህ ደረጃ መንኮታኮቱንና ጠርዝ የረገጠ ብሔርተኝነት መንሰራፋቱን ማሳያ መስታወት ሆኗል።

በሞራል ልሽቀቱ፣ በጠርዝ ረገጥ ብሔርተኝነቱ እና በደቦ ፍርዱ በፍፁም ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንዳይገባ ደግሞ በሌላ በኩል የሚታየው በጎነት፣ መተሳሰብ፣ መቻቻልን ብርታት ይሰጣል። ኢትዮጵያ አሁን ያለችበትን ሁኔታ ልክ በተለያየ ጽንፍ በቆሙ ገመድ በሚጓተቱ ኀይሎች ቅዠት ሊመሰል ይቻላል፤ ቅዠትነቱ ገመዱ የተበጠሰ ጊዜ ሁሉንም ገደል ይዞ መግባቱ መሆኑ ነው።

መሰረታዊ የሆነ የኅብረተሰቡን ችግሮች በሰከነ መንፈስ፣ በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመነጋገር መፍታት በኅበብረተሰቡ ውስጥ ሰርፆ እንዲገባ መሠራት ይኖርበታል። በተለይ መንግሥት፣ ትምህርት ተቋማት፣ ሲቪክ ማኅበራትና መገናኛ ብዙኀን በመረጃ የጎለበተ፣ በውይይት የሚያምን፣ በአመክንዮ የሚከራከር፣ በማስረጃ የሚያምንና የሚያሳምን ማኅበረሰብ ለመፍጠር መበርታት ይጠበቅባቸዋል። እነዚህ የአመለካካትና የባሕሪይ ለውጦች የሚመጡት በአንድ ሰሞን በሚሠራ ሆይ ሆይታና ዘመቻ ሳይሆን በዕቅድና በዘላቂነት ሲሠሩ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። የሕይወት ልምምድም ይጠይቃሉ።

በተጨማሪም የሃይማኖት ተቋማት በተለይ የኅብረተሰቡን የሞራል ዕሴቶች በመጠበቅ ረገድ ወገባቸውን ታጥቀው መሥራት ይገባቸዋል፤ የሃይማኖት መሪዎችም ለምእመኖቻቸው አርዓያ መሆን ይገባቸዋል ስትል አዲስ ማለዳ መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here