ዐቃቢ ሕግ በሐሰት ለሜቴክ መስክረዋል ያላቸው ግለሰቦች ላይ የመሠረተውን ክስ አቋረጠ

0
306

ለታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ውሃ የሚያርፍበትን ቦታ የደን ምንጣሮ ሥራ ለመሥራት ከኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ጋር በ2006 ውል ገብተው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ማኅበራት የሥራ ክፍያ እንዳይከፈል የሐሰት ምስክርነት ሰጥተዋል በተባሉ ባለሞያዎች ላይ ተመስርቶ ነበረው ክስ እንዲቋረጥ ተወሰነ።

የወንጀል ክሱ ምክንያት የሆነው ቅሬታ በአመልካቾች እና በሜቴክ መካከል በነበረው የፍትሐ ብሔር ክርክር ጉዳይ ላይ የባለሞያ ምስክርነት ለፍርድ ቤት ማስረጃ ያቀረቡት ግለሰቦች የሐሰት ማስረጃ አቅርበዋል የሚል አቤቱታ ነው። ለግድቡ የምንጣሮ ሥራ የሠሩት ስምንቱ ከሳሽ ድርጅቶች ጠቅላላ ብር ብር 56,948,033.76 ሜቴክ እንዳይከፍላቸው እና ባለሙያዎቹ በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት የልኬትና የክፍያ መጠን ማዘጋጀትና ማቅረብ ሲገባቸው የሐሰተኛ ማስረጃ አዘጋጅተው ለፍርድ ቤቱ በማቅረባቸው ክስ እንደተመሰረተባቸው መዝገቡ ያስረዳል።

ፖሊስ በቀረበለት ማስረጃ መሠረት ምርመራውን ጨርሶ ለዐቃቢ ሕግ በማቅረብ እና ዐቃቢ ሕግም ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት 14ኛ ወንጀል ችሎት በባለሙያዎቹ ላይ ክስ መስረቶ ነበር። ተከሳሾች ያለበቂ ምክንያት ቀጠሮ እንዲራዘም ከመጠየቃቸው በተጨማሪ፣ ዐቃቢ ሕግ በእያንዳንዱ ቀጠሮ አዳዲስ ጠበቆችን እየመደበ በጉዳዩ ላይ አስፈላጊውን ትኩረትና ዝግጅት ባለማድረጉ ምክንያት ክሱ ሳይሰማ ከአንድ ዓመት በላይ እንዲጓተት ተደርጎ በመጨረሻም ተቋርጧል ሲሉ ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የልደታ ምድብ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታቸው ሞረዳ፣ ክሱ በሒደት ላይ መሆኑን አስታውቀው፣ ነገር ግን ከዳይሬክተሯ ክሱ ይቋረጥ የሚል ደብዳቤ እንደደረሳቸው ገልጸዋል። ይሁን እንጂ አሁንም ክሱ የሚቋረጥበትን ምክንያት እንጠይቃለን ሲሉ ስለ ክሱ መቋረጥ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው ተናግረዋል።

በፍትሐ ብሔር ክርክር ወቅት ፍርድ ቤቱ ለባለሙያዎቹ በሰጠው ትዕዛዝ፣ ሥራው በተሠራበት ቦታ ላይ በመገኘት ግራ ቀኙ የሚያሳዩትን ቦታ በሜትር እንዲለኩና ከቦታው ተፈጥሮዋዊ አቀማመጥ አኳያ በሜትር መለካት የማይቻለውን ዲኢኤም በተባለ ዘዴ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሙያዊ እገዛ በመጠየቅ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ነገር ግን ባለሙያዎቹ ለሜቴክ በመወገን የተሳሳተ መረጃ በማቅረባቸው ምክንያት የተዛባ ፍርድ እንዲሠጥ ምክንያት ሆኗል ሲሉ የማኅበራቱ ተወካዮች ተናግረዋል።

የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወሰንየለሽ አድማሱ በበኩላቸው፣ አለአግባብና ያለበቂ ማስረጃ የቀረበ ክስ በመሆኑ ጉዳዩ ተምርምሮ ተገቢው ውሳኔ ይሰጥልን በሚል በአመልካቾች የቀረበ አቤቱታን መሰረት በማድረግ፣ በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የመዝገብ ማቋረጥና አዘጋግ መመሪያ እና ደንብ መሰረት የተሰጠ ውሳኔ ነው ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 31 ሰኔ 1 ቀን 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here