የሥነ ምግባር ትምህርትና የሐብት ምዝገባ አስገዳጅ ሕግ ሊወጣ ነው

0
578

የፌደራል የሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን የሥነ ምግባር ትምህርትና የሀብት ምዝገባን በተመለከተ አስገዳጅ አንቀፆቸን ለማካተት አዋጁን ሊያሻሽል ነው። የመንግሥት ባለሥልጣናት ሥራ ከመጀመራቸው በፊት የሥነ ምግባር ትምህርት ሥልጠና መውሰድ እንዳለባቸው ማሻሻያው ያስገድዳል ተብሎ ይጠበቃል።

የመንግሥት ባለሥልጣናት ሀብታቸውን የማስመዝገብ አስገዳጅ ሕግ እስከዛሬ አለመኖሩን ያሳወቀው ኮሚሽኑ፣ ሕጉ በአገሪቱ እየተንሰራፋ የመጣውን ሙስናና ምዝበራ በሚፈለገው ደረጃ መቆጣጠር እንዳይቻል በማድረጉ፣ በቀጣይ ጠንከር ያሉ ቁጥጥሮችን ለማድረግ ሕጉ አስገዳጅ ሆኖ መውጣት እንዳለበት መወሰኑን ገልጿል።

ሕጉን ማሻሻል ያስፈለገው ለሥራ እንቅፋት የሆኑ አንቀጾች በመኖራቸው እንደሆነ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት በኮሚሽኑ ውስጥ ዳይሬክተር የሆኑት ተስፋዬ ሻሜቦ፣ አስፈላጊ የሆኑ ግን ደግሞ በአዋጁ ያልተካተቱ አንቀጾችን መጨመር ስላስፈለገ አዋጁ ለሦስተኛ ጊዜ መሻሻል አስፈልጎታል ብለዋል። ከተቋቋመ 18 ዓመት የሞላው ኮሚሽኑ ከተዋቀረ በኋላ የሕግ ማሻሻያ ሲያደርግ ይሔ ሦስተኛው ነው።

ሌላው የሥነ ምግባር መከታተያ ክፍሎች በየተቋሙ ያሉ ቢሆንም፣ ከተቋሙ ኀላፊዎች የሚሰጣቸው ድጋፍና ክትትል በቂ ባለመሆኑና አንዳንድ ቦታ ጥቃት የደረሰባቸው ሁሉ በመኖራቸው ያንን ለማሻሻል በየተቋሙ ውስጥ ያሉ የሥነ ምግባር ማሻሻያ ክፍሎች ተጠሪነታቸው ለኮሚሽኑና ለተቋሙ የበላይ ኀላፊ ሆኖ የኹለትዮሽ ተጠሪነት እንዲኖራቸው ለማድረግ በረቂቅ አዋጁ ውስጥ መካተቱን ተስፋዬ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። በሥራ ሒደት ላይ ላፈጻጸም ምቹ ያልሆኑ ነገሮች አሉ፣ እነሱንም ማስተካለከል አስፈላጊ ሆኗል ሲሉም ያክላሉ።

በአዋጁ ከተቀየሩት ነገሮች መካከል፣ የጸረ ሙስና ፖሊሲና ስትራቴጂን የማዘጋጀት ሥልጣን አንዱ ነው። ከዚህ በፊት በነበረው አዋጅ ኮሚሽኑ ፖሊሲና ስትራቴጂ የማዘጋጀት ሥልጣን ያልነበረው በመሆኑ፣ አሁን በሕጉ ውስጥ እንዲካተት መደረጉም ታውቋል። ሌላው፣ በመንግሥት ተቋማት ውስጥ የሚሠራው ሙስናን የመከላከል ሥራ በሕግ የተደገፈ እንዳልነበር የሚያወሱት ተስፋዬ፤ አሁን ተቋማት በራሳቸው ሙስናን መከላከል እንዲችሉ፣ ኮሚሽኑም የመከታተልና የመደገፍ ሥራ እንዲሠራ የሚያስችል ስርዓት መዘርጋት አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ ያንን በተጠና መልኩ ለማከናወን አቅጣጫ አስቀምጠናል ብለዋል።

ኮሚሽኑ ከማስተማር ባሻገር ጸረ ሙስና አካዳሚ እንዲቋቋም ታሰበ ሲሆን የሀብት ምዝገባ ሥራ ላይ አዋጁ ሰዎች ያስመዘገቡት ሀብትና ያላቸውን የሀብት መጠን ከፍተኛ ልዩነት ካለው ጥቆማ እንዲያቀርቡ የሚያስችል የጥቆማ ስርዓት መዘጋጀቱንም ነው የጠቆመው።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here