ከፕላስቲክ የተሰሩ ለስላሰ ብርድ ልብሶች

0
1501

ሙሉ ሸዋ ተፈራ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። ለሥራ ጉዳይ ወደ ተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች በሚንቀሳቀሱበት ጊዜ የታሸገ ዉሃን በመግዛት ይጠቀማሉ። “ከከተማ ሲወጣ ንጹሕ የመጠጥ ውሃ እንደ ልብ ላይገኝ ይችላል። ስለዚህ የታሸገ ውሃን በመግዛት እጠቅማለው” የሚሉት ሙሉ ሸዋ ውሃን ጠጥተው ከጨረሱ በኋላ የፕላስቲክ ጠርሙሱን አንዳንዴ ወደ ቤታቸው ይዘውት እንደሚሔዱ ሌላ ጊዜ ደግሞ ያገኙበት ቦታ እንደሚጥሉት ይናገራሉ። “ከተማ ከሆንኩ ለሚቀጥሉት ቀናት ከቤቴ ይዤ ለመሔድ እንዲያመቸኝ የውሃውን መያዣ የፕላሰቲክ ጠርሙስ በመጣል ፈንታ ወደ ቤቴ ይዤው እሔዳለው። ከዛ ጥቂት ቀን ከተጠቀምኩበት በኋላ ከሌሎች ቆሻሻዎች ጋር አብሬ እጥለዋለው” ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ሙሉ ሸዋ የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫት በአቅራቢያቸው ካላገኙ ጠርሙሶቹን መንገድ ላይ እንደሚጥሉ እንዲሁም ቆሻሻ አወጋገዳቸው ላይም የሚበሰብስና የማይበሰብስ ብለው ለመለየት እምብዛም እንደማይጨነቁ አልሸሸጉም። ይህ ግን ሙሉሸዋ የሚያደርጉት ብቻ ሳይሆን የአብዛኞቻችን የዕለት ተዕለት ተግባር ነው ቢባል ብዙም ከእዉነቱ አይርቅም።

ጠዋት እና ማታ ረጅም የታክሲ ወይንም የአውቶቢስ ሰልፍ ይዘው ግራና ቀኝ የሚያማትሩ፣ የከረሜላና የማስቲካ ልጣጭ መሬት ላይ የሚጥሉ፣ የተጠቀሙበትን ሶፍት በመኪና መስኮት የሚወረውሩ፣ ከየሰው ቤት የሰበሰቡትን ቆሻሻ በጋሪ የሚገፉ ወጣቶች፣ አስፋልት የሚያጸዱ እህቶችን እንዲሁም የታሸገ ውሃ የፕላስቲክ ጠርሙሶችን ከቆሻሻ ማጠራቀሚያው አጠገብ መሬት ላይ የሚወረውሩ ሰዎችን ማየት አዲስ አበባ ለሚኖር ሰው ብርቅ አይደለም። ምንም እንኳን የቆሻሻ ማጠራቀሚያ ቅርጫቶች በአቅራቢያችን ቢኖሩም ቆሻሻን በአግባቡ ከማስወገድ ይልቅ ያገኘንበት መወርወር ልማድ ያደረግን ሰዎች ቁጥራችን ቀላል የሚባል አይደለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከከተማ የግርግር ሕይወት ወጥቶ በልምላሜያቸው ወደሚታወቁ የአገራችን ክፍሎች በተለያየ አጋጣሚ ለሔደ ሰው በተፈጥሮ ውበት መደነቁ አይቀሬ ነው። ለዚህም ይመስላል ከእነዚህ የተፈጥሮ ሀብቶች አቅራቢያ የተለያዩ የሆቴል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ግንባታ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ የመጣው። በዛው ልክም ወደ እነዚህ መዝናኛዎች የሚመጡት ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የምናያቸው የማስፋፊያ ግንባታዎች ምስክር ናቸው። ይህ በእንዲህ እንዳለ በሐይቆች ዳር የተገነቡት ሪዞርቶች በዙሪያቸው ላለው የተፈጥሮ ሀብት የሚሰጡት እንክብካቤ አጥጋቢ አይደለም። አንዳንዶቹን ሐይቆች ቀረብ ብለን ካየናቸው መቆሸሻቸው ያስታውቃል። ሌሎቹ ደግሞ በፕላስቲክ የውሃ ጠርሙሶች ተከበው ይታያሉ። የዚህ አካባቢን በንጽሕናና በእንክብካቤ ያለመያዝ ድርጊታችን ውጤቱ ራሳችንን በተለያየ መንገድ እየጎዳን ይገኛል። ይሁንና ጉዳቱ እኛ ላይ ብቻ በማብቃት ፈንታ ከእኛም አልፎ ችግሩ በባሰ መልኩ ወደሚቀጥለው ትውልድ የሚተላለፍበትም አጋጣሚ ሰፊ ነው።

የፕላስቲክ ምርቶች በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ጥፋት ከፍተኛ የሚሆንበት ምክንያት የሚመነጨው ፕላስቲክ ከአፈር ጋር በሚቀላቀልበት ጊዜ በተፈጥሮ ሒደት በባክቴሪያና በፈንገስ ፈርሶ ወደ ጠቃሚ ንጥረ ነገር ስለማይቀየር ነው። ወደ ትናንሽ ፕላስቲክነት ለመቀየር አንድ ሺሕ ዓመት ያህል የሚፈጅበት ፕላስቲክ የአፈርን ለምነት በማጥፋት የተፈጥሮ ልምላሜን ያጠፋል። በጸሐይና በዝናብ ፕላስቲኮቹ በሚቆራረጡበት ሒደት ደግሞ አካባቢን የሚበክሉ ኬሚካሎች ወደ አካባቢ ይለቀቃሉ።

ከዚህም አልፎ ፕላስቲኮቹ ወደ ጠቃሚ ንጥረ ነገር ስለማይቀየር ተቆራርጠው መጠናቸው አንሶ በአፈር ውስጥ ሁሌ ስለሚኖሩ በውሃ አካላትም ሆነ በየብስ ላይ የሚኖሩ እንስሳትን ይጎዳል።

ሌላዉ ደግሞ የፕላስቲክ የውሃ ጠርሙሶችን ለማምረት የምንጠቀመው ፎሲል ፊውል ታዳሽ ኀይል ካለመሆኑ በተጨማሪ ከማምረት ጀምሮ እስከማስወገድ ባለው ሒደት ውስጥ ብዙ ኀይል እንጠቀማለን። በ2012 የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ በዓለም ላይ በአንድ ዓመት ውስጥ ብቻ 450 ሚሊዮን በርሜል ነዳጅ የውሃ ፕላስቲክ ጠርሙሶችን ለማምረት፣ ለማጓጓዝና ለማስወገድ ይውላል። ይህም ከ25.5 ሚሊዮን መኪኖች የአንድ ዓመት የነዳጅ ፍጆታ ጋር እኩል ነው። ከኤምሬትስ አየር መንገድ ያገኘነው መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ደግሞ 90 በመቶ የሚሆነው የፕላስቲክ ምርት ተመልሶ አገልግሎት ላይ አይውልም።

ኤምሬትስ በ1959 ኹለት ቢሊዮን ቶን ፕላቲክ እንደተመረተና ይህ ምርት በ2019 ስምንት ነጥብ ሦስት ቢሊዮን ቶን እንደደረሰ ይናገራል። በ2050 ደግሞ ይህ ቁጥር 34 ቢሊዮን ቶን ይደርሳል ተብሎ ይገመታል።

የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ለ12 ዓመት የሠሩት ወንደሰን ስንታየሁ እነዚህ ምርቶች በአብዛኛው ወደ ውሃ አካላት በንፋስ፣ በእነስሳት እንዲሁም በሰዎች እንደሚጣሉ ይናገራሉ። ይህም የውቅያኖሰን የብዝኀ ሕይወት ትስስር በማዛባት አልፎ የምግብ እጥረትን ይፈጥራል ባይ ናቸው። በመሆኑም ይህን ችግር ለመቅረፍ ኹለት አማራጭ ያሰቀምጣሉ። የመጀመሪያው አማራጭ የፕላስቲክ ምርቶችን ማምረት ማቆምና በሌላ አማራጮች መተካት ሲሆን ኹለተኛው ደግሞ መልሶ ጥቅም ላይ ማዋል ናቸው።

ወንደሰን “ምንም እንክዋን ታዋቂው ባለሀብት ዋረን ባፌት ፕላስቲክ አምርቶ መልሶ መጠቀም የሚለው ሐሳብ ቀልድ ነው ቢልም መመረቱ ካልቀረ ግን መልሶ አገልግሎት ላይ ማዋሉ የተሻለ አማራጭ ነዉ” ይላሉ።

ኤምሬትስ እንደማሳያ
የኤምሬትስ ዓየር መንገድ የፕላስቲክ ምርቶች በአካባቢ ላይ የሚያደርሱት ጉዳት አስከፊ የሚሆነው ጠርሙሶቹን በአግባቡ ስለማንጠቀምባቸው እንጂ ይህንን ምርት መልሰን ጥቅም ላይ ለማዋል በጥሬ ዕቃነት ብንጠቀመው አካባቢን ከጉዳት ለመጠበቅ ይረዳል ይላሉ። ኤሜሬትስ ግንቦት 28 (ጁን 5) የተከበረዉን የአካባቢ ጥበቃ ቀን ምክንያት በማድረግ 100 በመቶ ከፕላስቲክ ጠርሙሶች መልሰው የተሰሩ ዘላቂ ብርድ ልብሶች አስተዋዉቋል። እነዚህ ለስላሳና ሙቀት የሚሰጡ ብርድ ልብሶች ከኢኮትሬድ የፈጠራ ቴክኖሎጂ የተሠሩ ሲሆን በረጅም ጉዞዎች ላይ በኢኮኖሚ ክላስ ውስጥ ማግኘት ይቻላል። ሁሉም የኤሜሬትስ ኢኮትሬድ ብርድ ልብሶች ከ28 መልሰው ከተሰሩ ፕላስቲክ ጠርሙሶች የሚሠሩ ሲሆን የቅርብ ጊዜ ፈጠራዎች በመጠቀም ጠርሙሶቹ ወደ ፕላስቲክ ቁርጥራጮች ከዛም ወደ ክር፤ በመቀጠልም ወደ ፍሊስ ጨርቅነት ይቀይራል። በመቀጠልም እነዚህ ለስላሳ ብርድ ልብሶች በክሮች ይሠፋሉ። እነዚህ ለአካባቢ ተስማሚ ብርድ ልብሶች የተሰሩት ከባዝ ድርጅት ጋር በመተባበር ሲሆን፣ ከዓለም ቀዳሚ የበረራ ልዩ ልዩ ምርት ውጤቶች ባለሙያ ሲሆኑ የኤሜሬትስ ምርት ፈጠራ እና ዘላቂ ምርት ተባባሪ አካል ናቸው። የኤሚሬትስ አረንጓዴ ዘመቻ በሁሉም በረራዎቹ ውስጥ በአሁኑ ጊዜ ያለ ሲሆን የአልሙኒየም መጠጫ ቆርቆሮዎችን፣ የፕላስቲክ እና የመስታወት ጠርሙስዎች፣ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች እና ካርቶኖች የመሳሰሉ ንፁሕ የወረቀት ምርቶች መልሶ በመሥራት ይጠቀማል።

በ2012 አጋማሽ የኤሜሬትስ ኢኮትሬድ ብርድ ልብሶች 88 ሚሊዮን ወይም የ44 A380 አውሮፕላኖች ክብደት የሚመዝን የፕላስቲክ ጠርሙሶች መሬትን ከመሙላት ይታደጋል። በተጨማሪም መልሰው ጥቅም ላይ ለማዋል በሚደረገው የፖሊቴሊን ቴሬፓታሌት (ፒ.ኢ.ቲ) የማምረት ሒደት በ70 በመቶ የኀይል ፍጆታ ይቀንሳል። ኢኮትሬድ በሦስተኛ ወገን ኢንተርቴክ ግሪን ሊፍ ማርክ፤ ነጻ የምስክር ወረቀት ሰጪ አካል በተደረጉ ፍተሻዎች 100 በመቶ መልሰው ከተሠሩ ቁሶች እንደሆነ ተረጋግጧል። የኤሜሬትስ ኢኮትሬድ ብርድ ልብሶች በኢኮኖሚ ክላስ መገኘት በሁሉም ሦስቱም ክፍሎች ውስጥ ተመሳሳይ ምቾት እንዲኖር ያደርጋል።

ይህ የኤምሬትስ ተሞክሮ ሌሎች አየር መንገዶችም ሆኑ ባለሀብቶች እንደ አንድ የኢንቬስትመንት አማራጭ ቢከተሉት ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው፤ አካባቢ ጥበቃ፣ ንጽሕ ከባቢ እና ለብዙዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here