አካታች ፋይናንስ ፍለጋ እና ስጋት

0
826

“የእስላማዊ ባንክ ፖለቲካ!?” በሚል ርዕስ የአዲስ ማለዳ አምደኛ ይነገር ጌታቸው በግንቦት 24/2011 ዕትም ያስነበቡትን ጽሁፍ በመቃወም ኢብራሒም አብዱ ረዘም ያለ ምላሽ አዘጋጅተዋል። የይነገርን የጽሁፍ ጨመቅ ለአንባቢዎቻችንን ለማስታወስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እስላማዊ ባንክ እንዲመሰረት የሚችሉትን ሁሉ እንደሚያደርጉ በአደባባይ የተናገሩትን መሰረት በማድረግ “ከእስላማዊ ባንክ ጀርባ የሚኖረው ማነው?” የሚል ጥያቄ በማንሳት የአገራትን ተመክሮ ከእጀ ረጃጅሞቹ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት በተለይም ከተባበሩት አረብ ኤምሬት የውጪ ጉዳይ ፖሊሲ አንጻር የሚደረጉ ግንኙነቶች በብርቱ ጥንቃቄ መታየት አለበት የሚል መከራከሪያ ነጥቦችን አንስተዋል።

(ክፍል አንድ)
የይነገር ጽሁፍ ርዕሱ ሰለኢስላማዊ ባንክ ቢሆንም ጭብጡም ሆነ ይዘቱ “ኢስላማዊ አክራሪነት” በራችን እያንኳኳ ነው የሚል አስፈራሪ ድምዳሜ ማቅረብ ነው። ከክስተቶች ጀርባ ሊኖሩ የሚችሉ የቢሆን መላምቶችን (Scenario) ደርድሮ በመረጃና ማሰረጃ፣ በምክንያትና አመክንዮ የዳበረ ድምድሜና ጥቆማ ማቅረብ የአንድ ጋዜጠኛ አልያም ፖለቲካን በንቃት የሚከታተል ዜጋ ኀላፊነት ነው። የይነገር ጽሁፍ ግን የቢሆን መላምት አላባውያንን ያላሟላ፣ መነሻ የሌላው አልያም ሐሳዊ መደጋፊያን የተመረኮዘ ክፉ ጥርጣሬ፣ ራስን ብቸኛ የአገር ዘብ አድርጎ ከማሰብ እና ከአገር ይልቅ በራስና በቡድን ጥቅም የተቃኘ ውንጀላ ነው። በጽሁፉ ለተነሱት በድፍረት የተሞሉ መደምደሚያዎች አመክኗዊ መነሻ ሊያቀርብ ቀርቶ ደጋፊ ለማድረግ የሰበሰባቸው የሐሳብ ቡትቶዎች በህፀፅና ተፋልሶ የታጨቁ ናቸው።

የጽሁፉ ፍሰትን በጥሞና ላሰተዋለ የታቀኘበት መንገድ በምሁራዊ አለመታመን (intellectual dishonesty)፣ በማወቅ ብዥታ (knowledge illusion) እና ጥቁር ወይም ነጭ (Black and White) በተሰኙ ኢ-አመክኗዊ የአሰተሳሰብ አጥሮች ነው። እነዚህ ኢ-አምክኗዊ የአሰተሳሰብ አጥር መረጃን ማዛባት፣ የራስን የተዛባና አድሏዊ ዕይታ ከተጨባጭ እውነታ (objective reality) ጋር ማሳከር፣ ስሜትን እንደመረጃ ማቅረብ እንዲሁም ሁሉንም ነገር በኹለት ፅንፎች ከፍሎ በማሳየት ይሄን አልያም ያኛውን መምረጥ አለብን የሚሉ መልዕክቶችን ለማሰተላለፍ ያገለግላሉ። ብዙ ጊዜ ፕሮፓጋንዳዎች በዚህ መልኩ ነው የሚቃኙት።

ከአመክንዮና ምክኒያታዊነት እንዲሁም ከሳይንሳዊ አቀራረብና ተጨባጭ ማሰረጃ(empirical evidence) ይልቅ ሐሳቦችን፣ ክሰተቶችን በአጠቃላይ ዓለምን ጥሩና መጥፎ፣ ጎጂና ጠቃሚ፣ እኛና እነሱ፣ ነጭና ጥቁር፣ ሁሉንም አልያም ምንም፣ የመሳሳሉ ፅንፎች ውስጥ በማቆር ከአዕምሮ ይልቅ ስሜትን በመኮርኮር ወደሚፈልገው መደምደሚያ ማውረጂያ መንገዶች ናቸው። ሰለፆታ፣ ሕዝቦች፣ ብሔሮች፣ ባሕሎች፣ እምነቶች ዙሪያ የተያዙ የተዛቡ አመለካከቶች (steroetypes) በዚህ ዓይነት ቀመር የሚቀርቡ ጽሁፎችና ንግግሮች ውጤት ናቸው። የይነገር ጽሁፍ ላይ የሚሰተዋሉ እነዚህንና መሰል ህፀፆች በየረድፋቸው ለመዳሰስ እሞክራለው። በርግጥ ያነሳቸው ብዥታዎችና በጽሁፉ ውስጥ ያሉ ህፀፅና ተቃርኖዎች አንድ መጽሐፍ የሚወጣቸው ቢሆንም አንኳር የሆኑት ላይ ብቻ አተኩራለው።

የቀጠና የበላይነት ፖለቲካ ወይስ ሃይማኖት?
የተባበሩት አረብ ኢማሬት የውጭ ግንኙነት ከሃይማኖታዊ ይዞታው ይልቅ ከቀጠናዊ የበላይነትና ደኅንነት ፖሊሲ ጋር የሚያያዝ ቢሆንም ይነገር ግን መድምደሚያውን ይደግፍላቸው ዘንድ ሃይማኖታዊ ካባ በግዳጅ አልብሰውታል። በጽሁፉ ላይ ለመረጃነት የጠቀሰው መሀሪ ታደለ (ዶ/ር) መጣጥፍ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትን የአገር ውስጥና የውጭ ግንኙነት የሚወስኑ አራት ምሶሶዎችን ንግድ፣ ቱሪዝም፣ ሽብርን እና የኢራንን ቀጠናዊ የበላይነት መዋጋት ሲል በግልፅ አሰፍሯቸዋል። ጸሀፊው ግን አንባቢ ላይ የሃይማኖታዊ አክራሪነት ሥጋትን ለመፍጠርና ለማሳመን “ሽብርን መዋጋትን እና የኢራንን ቀጠናዊ የበላይነት መግታትን” (የነዳጅና የተፈጥሮ ጋዝ ሀብት ፖለቲካውም ሳይረሳ) የቀጠና የበላይነትን መሰረት ካደረገ የኀይል ግንኙነት (Regional dominancy and power relation) ማዕቀፍ አውጥቶ በግዳጅ የሃይማኖት ማዕቀፍ ከቶታል። ይነገር በፅሁፋቸው እማኝ አድርጎ የጠቀሳቸው መሀሪ ቃል ቃል በቃል “Islam is not treated as a state doctrine that dictates the policies of the UAE” በግርድፉ ወደ አማርኛ ሲመለስ “ኢስላም የተባበሩት አረብ ኢሚሬትን የውጭ ጉዳይን የሚመራ አገራዊ ቀኖና አልተደረገም” ሲሉ ያክላሉ።

በጥቅሉም የመካከለኛው ምሥራቅ የውጭ ግንኙነት ፖለሲ የኢራንን ፖለቲካን መፍራት፣ ለዘወዳዊ አገዛዛቸው እንቅፋት የሚሆንን ዲሞክራሲን መቃረን ላይ የተመሰረተ መሆኑን የቀጠናው ፖለቲካ አጥኚና ተንታኞች ይናገራሉ። ይነገር ግን የመሀሪ ታደለን ምሁራዊ ጽሁፍ ሳይቀር ከዓውዱ አውጥተውና አዛብተው ለራሳቸው ቀድሞ የተያዘ ድምዳሜ ተገዢ በማድረግ ምሁራዊ አለመታመን (Acadamic dishonesty) ፈፅመዋል።

ከውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ምሶሶ ገዢ እሴቶቻቸው እንደምንረዳው የኢራን ሃይማኖታዊ ቀኖና የተባበሩት አረብ ኢሚሬትን ጨምሮ በነዳጅ ሀብት ለበለፀጉት የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ሥጋት የሆነው ለሚከተሉት የሃይማኖት መስመር ቀናዒ በመሆናቸው ሳይሆን የኢራን ቀኖና ከፍተኛ ፖለቲካዊ ኀይልን ለሃይማኖታዊ መሪ (አያቶላህ) የሚሰጥና ሌሎች ፖለቲካዊ ሥልጣኖች በዲሞክራሲያዊ ምርጫ የሚገኙ በመሆናቸው በቀጠናው መሰል ፖለቲካዊ ሞዴል መኖሩ የእነርሱን ከፍተኛ ፖለቲካዊ ኀይልን ለንጉሣን የሚሰጠውን ፖለቲካዊ ሞዴል የሚቃረንና ለፖለቲካዊ ሥልጣናቸው ሥጋት የሚሆን በመሆኑ ነው።

ይህንን ሙግት የሚደገፍልን የውጭም ሆነ የአገር ውስጥ ፖሊሲያቸው መዘውር ሥልጣናቸውን ማሰጠበቅን ያለመው ፀረ ዲሞክራሲያዊነታቸው ሁሉንም የሚያስማማ መሆኑ ነው። በጥቅሉ ከኢራንም ሆነ ከሙስሊም ወንድማማቾች ጋር ያለው ግጭት የሃይማኖታዊ ቀኖና ሳይሆን የቀጠናዊ ኀይልና የፖለቲካ ሞዴል የበላይነት ግጭት ነው። የኒዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ የሆነው ዴቪድ ክርክፓትሪክ “The most powerful leader is not M.B.S., its M.B.Z.” በሚል ርዕስ ባሰነበበው ሰፊ ዳሰሳ የዊክሊክስን ያፈተለከ መረጃ ጠቅሶ የአቡዳቢው ገዢና የአገሪቷ Defacto መሪ መሐመድ ቢንዛይድ ከአንድ የአሜሪካ ዲፕሎማት ጋር ባደረጉት ውይይት “መካከለኛው ምሥራቅ ለዲሞክራሲ ገና ነው የሚል ፅኑ አቋም ያላት የተባበሩት አረብ ኢሚሬት ዴሞክራሲያዊ ምርጫን መርሁ ያደረገው የሙስሊም ወንድማማቾች የፖለቲካ ሞዴል ዜጎቼን ያማልልብኛል የሚል ሥጋት እንዳነሱ በመጠቀስ በቀጠናው ከፍ ሲልም በአረብ አገራት ዲሞክራሲ መሰረት እንዳይኖረው ማድረግ ቀዳሚ ትኩረታቸው መሆኑን ይሞግታል። የፀረ ሙስሊም ወንድማማቾች አቋሟም ይህ የዲሞክራሲ ሥጋት እንደሆነ እሙን ነው።

በርግጥ የተባባሩት አረብ ኢሚሬት ጥልቅ ወዳጆች አሜሪካ፣ እስራኤልና የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ተቋም አባል አገራት መሆናቸውን ለታዘበ የውጭ ግንኙነቷ ሃይማኖት ሳይሆን ቀጠናዊ የበላይነት የገፋው መሆኑን በቀላሉ የሚረዳው ነው።

በዋናነትም ከአሜሪካ ጋር ያላትም ጥብቅ ቁርኝት ቀጠናዊ የኀይል ሚዛንና ሥልጣን ማሰጠበቅ ላይ የተመሰረተ መሆኑ በርካታ ምሁራን የሚስማሙበት ነው። መሀሪ ታደለ “Why the US is engineering political change in East Africa” በሚል ርዕስ አልጀዚራ ላይ ባሰነበቡት ትንታኔ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትና ሳዑዲ አረቢያ ምሥራቅ አፍሪካ ላይ መብዛት በአሜሪካ ቀጣናዊ የፖለቲካ ስታራቴጂ እንደሚመራ ይገልፃሉ። በግንቦት 2017 (እ.ኤ.አ) የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የውጭ ጉብኝታቸው የመጀመሪያ መዳረሻ ባደረጉት ሪያድ በተካሔደው የአሜሪካና አረብ አገራት ጉባዔ የኢራንን ተስፋፊነት መግታት፣ ሽብርን በጋራ መዋጋት፣ የአረብ እስራኤልን ሰላማዊ ድርድር መመለሰ፣ በመካከላቸው የሚኖሩ ግጭቶችን ማረቅ በጋራ የሚሠሩበት የውጭ ግንኙነታቸው አቅጣጫ መሆኑን መስማማታቸው ከላይ የተነሱትን ሐሳቦች የሚያጠናክር ነው።

ሌላው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዘመን የውጭ ግንኙነታችን ከተቋማዊነት ይልቅ ግለሰባዊ መሆኑን ብዙ ምሁራንን የሚያስማማ፣ ራሳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀር በተለያዩ መድረክ ያነሱት እውነታ ነው። ከአቡዳቢው ንጉሥ ጋር ያላቸውንም ወዳጅነት ኹለትዮሽ እንጂ ተቋማዊ እንዳልሆነ በተለያዩ ወቅቶች ያደረጓቸው ንግግሮች እማኝ ናቸው። ይህን መነሻ ካደረግን የኢቫንጀሊካን ቤተ ክርስቲያን ተከታይ የሆኑት ዐቢይና የአቡዳቢው ገዢ ግንኙነት ሃይማኖታዊ እንደማይሆን ለማንም አይጠፋም። ይነገር ግን ከዚህ ነባራዊ፣ ቀጠናዊና ታሪካዊ ዳራ በማፈንገጥ የተባበሩት አረብ ኢሚሬትና የኢትዮጵያን ግንኙነት ሃይማኖታዊ ቀለም በማልበስ የኢትዮጵያውን ሙስሊሞች እንቅስቃሴዎችም በዚሁ በግድ ሃይማኖታዊ ካባ በለበሰ የኢትዮጵያና የተባበሩት አረብ ኢሚሬት ግንኙነት እንዲቃኝ ለማድረግ ሞክረዋል።

ከዚህ ባሻገር ለችኩል ድምዳሜያቸው ያቀረበው መነሻ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይም ሆኑ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የአሪገቱን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡና፣ ፖለቲካዊ ውሰብስብነት የጎደላቸው የዋሆች (Naïve) ናቸው የሚል ክፉ እሳቤና ራስን ብቸኛ ተቆርቋሪ የማድረግ ልቦለዳዊ አርበኝነትን ነው። ዐቢይ በኢትዮጵያውያን አዘጋጅነት በአሜሪካ በተደረገው መርሃ ግብር ላይ ባደረጉት ንግግር ለአቡዳቢው ገዢ አገራችን በቂ የሃይማኖት ምሁራን እንዳሏትና በተለይም ከሃይማኖቱ ፍፁም ከራቁት የመካከለኛው ምሥራቅ ዘውዳውያን በዚህ ረገድ ምንም ድጋፍ እንደማያሻት አፅንዖ ትሰጥተው መናገራቸው ይታወሳል። ይህ ንግግርም የአቡዳቢውን ገዢ እንዳሰከፋ የመካከለኛው ምሥራቅ መገናኛ ብዙኀን አሰነብበውናል። ይነገር ግን በአዕምሯቸው ውስጥ ያለውን ድምዳሜ ይደግፍላቸው ዘንድ፣ ብዥታ ላይ የተገነባ የግል ዕይታቸውን ተጨባጭ ለማሰመሰል የንግግራቸውን ከፊል ብሎም ከዓውድ ውጪ በመጠቀም ሌላ ተጨማሪ ሸፍጥ ሰርተዋል። ተጨባጭ ማሰረጃና አመክኗዊ ድጋፍ ሳይኖር ከጋራ ሃይማኖት ውጪ የጋራ ራዕይም ሆነ ሌላ አሰተሳሳሪ በሌለበት የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን ከእነዚህ ፀረ ዲሞክራሲያን ጋር ማስተሳሰር ኢትዮጵያዊ ሙስሊሞች ለአገራቸው ያላቸውን ፅኑ ታማኝነት ከውጭ ኀይል ጋር በማሰተሳሰር የተከፋፍሎ ታማኝነት (Divided loyality) ያላቸው የማስመሰል ክፋት እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይቻላል?

በዋናነት በተባበሩት አረብ ኢሚሬትና አጋሮቿ በአንድ ጎን ኢራንና የሁሲ ታጣቂዎችን በሌላ በኩል ያሰለፈው ለበርካታ ንፁሐን ሞትና ስደት ምክንያት የሆነው የየመን ጦርነትም ቀጣናዊ ወዳጅ የሚያስፈልግ ሌላው መግፍዔ ነው። የተለያዩ ባለሥልጣናትን በጉቦ በመደለልና የአገር ሉዓላዊነትን በማወክ ክስ ከሱማሊያ የተባረረችው፣ የጅቡቲ የወደብ አሰተዳደሯ ተነጥቆ ለወዳጇ አሜሪካ ባላንጣ ቻይና የተሰጠባት አገር ጠንካራ ቀጠናዊ ወዳጅ ፍለጋ የኢትዮጵያን ደጅ ማንኳኳቷ ሃይማኖታዊ ግንኙነት የሚል ቅብ ሊሰጠው የሚችለው እንደ ይነገር ከምክንያትና አመክንዮ በራቀ ዓለም ውስጥ ብቻ ነው።

ጸሀፊው መረጃን በማዛባት፣ ለራስ እሳቤ ተገዢ ለማድረግ በመጠምዘዝና ብዥታን እንደመረጃ ከማቅረብ ባሻገር በሴኔጋል የኢትዮጵያ አምባሳደር ተደርገው የተሾሙት አምባሳደር ሀሰን ታጁ የዲፕሎማሲ ሥልጠና ከወሰዱ በኋላ በተባበሩት አረብ ኢሚሬት ውሳኔ ከሹመታቸው እንዲቀሩ ተደርገዋል ሲሉ ፍፁም ከእውነታ የራቀ መረጃ አቅርበዋል። የይነገር ጽሁፍ ለንባብ የበቃው ግንቦት 24 ቀን ሲሆን አምባሳደር ሀሰን ታጁ ሦስት ቀን ቀደም ብሎ ረቡዕ፣ ግንቦት 21 የሽኝት መርሃ ግብር ተደርጎላቸው ነበር። ከዚህ የመረጃ ማዛበትና ያልተጣራ መረጃ የማቅረብ ተግባራቸው በላይ የተባባሩት አረብ ኢሚሬት በአገራችን እያደረገች ነው ያሉትን እንቅስቃሴ በአንድ ጎኑ ጥሩ ነው ብለው በማወደስም የአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ እንደማያሰጨንቃቸውም ገልፀውልናል።
(ይቀጥላል)

ኢብራሒም አብዱ በኢሜል አድራሻቸው
ibrahimabdulaziz011@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here