የቴሌኮም አገልግሎት ተቆጣጣሪ ባለሥልጣን ተቋቋመ

0
604

በተለያዩ ሕጎች ተበታትነው የሚገኙ የኮሚኒኬሽን ሥራ ሕጎችን በአንድ የሰበሰበው እና በተለይም የቴሌኮም አገልግሎት ወደ ግል ዘርፍ ሲዘዋወር ጠንካራ ቁጥጥር ለማደድረግ ታስቦ አካል በማስፈለጉ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣን በሚል ስያሜ ተቆጣጣሪ ተቋም ተቋቋመ።

የቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍ አሁን የደረሰበትን ዓለም ዐቀፋዊ ደረጃ ታሳቢ በማድረግና ዕድገቱን ተከትሎ የሚመጡትን ለውጦች በአግባቡ ክትትልና ቁጥጥር እንዲደረግባቸው በማሰብ ባለሥልጣኑ እንደተቋቋመም ታውቋል።

የሰው ሀብትና ቴክኖሎጂ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ እና የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዩች ቋሚ ኮሚቴ በጋራ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረቡት አዲሱ የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣን፤ መንግሥት በቴሌኮም ዘርፉ ያለው አገልግሎት ለኅብረተሰቡ በጥራት እንዲዳረስ እና ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢም ለማሳደግ በሚያስችል መልኩ የሚሠራው ሥራ ውጤታማ እንዲሆን ይረዳል ተብሎ ታስቧል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የቴሌኮም አገልግሎቱ ከማንኛውም የስርቆት እና የማጭበርበር ተግባር ለመከላከልም የሚያስችል አደረጃጀት የሚፈጥር እንደሚሆንም ይጠበቃል።

በባለሥልጣኑ ማቋቋሚያ አዋጅ ላይ እንደተገለፀው የቴሌኮም አገልግሎቱ ወደ ግል ይዞታነት በሚዘዋወርበት ጊዜ ምን ያህል አዲስ መንግሥታዊ ያልሆኑ አገልግሎት ሰጪዎች እንደሚገቡ፣ በምን መልኩ እና መቼ ፈቃድ እንደሚሰጥ በመንግሥት እንደሚወሰን ለመረዳት ተችሏል። ለዚህ ደግሞ እንደምክንያት የተቀመጠው በቀጣይ የኢንቨስትመንት ሕጉ ማሻሻያ እስከሚደረግበት ድረስ በዘርፉ የሚሰማሩ ሰዎች ቁጥር በግልፅ መታወቅ ስላለባቸው እንደሆነ ተጠቁሟል።

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ እዮብ ተካልኝ ረበዕ፣ ሰኔ 5 ሰባተኛው የሥራ አስፈፃሚዎች ፎረም ላይ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የቴሌኮም ሴክተሩን ለግሉ ሴክተር እንደደሚከፈት ተናግረዋል። “በሚቀጥለው ዓመት በዚህ ሰዓት ምናልባት የተለያዩ ሲም ካርዶች ይኖራችኋል” በማለት ገልፀዋል።

በተመሳሳይም የገንዘብ ሚኒሰትሩ አሕመድ ሺዴ ከደቡብ አፍሪካው የዜና አውታር ጋር ባካሔዱት ቃለ ምልልስ ሳፋሪ ኮም እና ኤም ቲ ኤን ወደ ኢትዮጵያ ገበያ ዓይናቸውን የጣሉ ናቸው ብለዋል።

አምስት ዓመት የሥራ ዘመን ባለው ቦርድ የሚመራው ባለሥልጣኑ በቴሌኮም ማስፋፋት ወቅት የሚያጋጥሙ መሰረታዊ ችግሮችን ሊፈታ በሚችል ቁመና እንደተቋቋመ ተገልጿል።

የባለሥልጣኑን በአዋጅ መቋቋም ተከትሎ ዘርፈ ብዙ ተቀሜታዎች እንዳሉት የሚገልፁት በገንዘብ ሚኒስቴር አማካሪ ሆነው የሚያገለግሉት ብሩክ ታየ (ዶ/ር) “ኢትዮ ቴሌኮም ብቻ በነበረበት ጊዜ ችግር አልነበረም” በማለት በቀጣይ የቴሌኮም አገልግሎቱ ወደ ግል ይዞታነት በሚዞርበት ጊዜ በርካታ ጭቅጭቆችና አለመግባባቶች ሊከሰቱ ስለሚችሉ ባለሥልጣኑ እንዲህ ዓይነት ችግሮችን ለመፍታት ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በተለይ ደግሞ በማማ ተከላ ወቅት ይኖራሉ ተብሎ የሚጠበቁ ውዝግቦች ከወዲሁ ቅድመ ዝግጅት መደረጉ ትልቅ እንቅስቃሴ ነው ብለዋል። “በቴሌኮሙኒኬሽን ዘርፍም ዳኛ ያስፈልጋል” የሚሉት ብሩክ እንዲህ ዓይነት ገለልተኛ ተቋም ማቋቋም ብቻ በቂ እንዳልሆነና በአዋጅ የተሰጠውን ሥልጣንና ኀላፊነት እንዲወጣም ነፃ ማድረግ እንደሚገባና ተገቢም እንደሆነ ጨምረው አስታውቀዋል።

የቴሌኮሙኒኬሽን አገልግሎት ወደ ግል በሚተላለፉበት ጊዜ ቀድመው የተዘረጉ የመሠረተ ልማት ተቋማት ተገቢ ካሳ እንዲከፈል እንደሚደረግ በግልፅ የተቀመጠ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለባለሥልጣኑ የመቆጣጠር ሥልጣን እንደሚኖረውም ታውቋል። የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣኑ ተጠሪነቱ ለኢኖቬሽን ሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር እንደሆነም ታውቋል። ሰኔ 5/2011 ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባለሥልጣን ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 39/2011 በሙሉ ድምፅ ፀድቋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here