የጂ አይ ዜድ ሠራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ

0
531
  • የተራድዖ ድርጅቱ ላይ የአምስት ዓመት የምርመራ ኦዲት እየተደረገ ነው

ዓለም ዐቀፉ የጀርመን ተራድዖ ድርጅት ጂ አይ ዜድ የኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ሐሰተኛ ሰነድ በድርጅቱ ሥም በማዘጋጀት እንዲሁም ኹለት የጭነት አስተላላፊ ድርጅት ሠራተኞች ደግሞ ያለአግባብ የቀረጥ ነፃ መብትን በመጠቀም ክስ ተመሰረተባቸው።

ሐሙስ፣ ሰኔ 6/2011 በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ችሎት እስካሁን በቁጥጥር ሥር መዋል ያልቻለውን አቤል አክሊሉን ጨምሮ በአራት ተጠርጣሪዎች ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ መስርቷል። የጂ አይ ዜድ ባልደረባ የሆኑት ራሔል እንዳለ እና የራይድ የጭነት አስተላላፊ ባልደረባ የሆኑት እቃው በቦሌ አየር ማረፊያ የዕቃ ጭነት ውስጥ በሚገኘው የጉምሩክ ኮሚሽን ቅርጫፍ ሳይታወቅ እንዲያልፍ አድርገዋል የተባሉት ኹለት ግለሰቦች ክስ ከተመሰረተባቸው መካከል ናቸው።

የጭነት አስተላላፊዎቹ ቴዎድሮስ ተስፋዬ እና ሱራፌል ዓለሙ ፖሊስ እጅ ከፍንጅ በቁጥጥር ሥር አውዬዋለሁ ያለውን 219 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ ዕቃዎች በሐሰተኛ ሰነድ ተጠቅመው የማስተላለፍ ሥራቸውን ያለአግባብ ተጠቅመዋልም ተብሏል።

የዓለም ዐቀፍ የዲፕሎማቲክ መብትን በመጠቀም በጂ አይ ዜድ ሥም ሳዑዲ አረቢያ በሚገኝ እና ዓለም ዐቀፍ በሆነ ድርጅት የተጫኑ የመኪና መለዋወጫዎች፣ የተለያዩ የሞባይል ስክሪኖች፣ ካነን ካሜራዎች፣ ፕሮጀክተሮች፣ መድኀኒቶች፣ የብር ጌጣጌጦች እና ድሮኖች ሊገቡ ሲሉ ከተያዙት እቃዎች መካከል መሆናቸውን የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ገልፀው እንደነበረ ይታወሳል።

ፖሊስም የገቡት ዕቃዎች ወደ ካዛንቺስ ይዞ እንዲሔድ ትዕዛዝ የተሰጠውን ሹፌር ቃል በመውሰድ የተባለውን አካባቢ ለይቶ ለማግኘት የምርመራ ሥራ እየሠራ መሆኑ ታውቋል። በተጨማሪም ዕቃውን የጫነው የሳዑዲ አረቢያ ድርጅት ላይ ተመሳሳይ ማጣራቶችን በማካሔድ ላይ እንደሆነ ተገልጿል። የአየር መንገዱ የካርጎ ቅርንጫፍ ሠራተኞች ላይም ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ታውቋል።

ከዚህ ቀደም ጂ አይ ዜድ 410 ኪሎ ግራም ዕቃን የዲፕሎማቲክ መብትን በመጠቀም ከቀረጥ ነፃ እንዲያስገባ የተሰጠውን ሰነድ መነሻ በማድረግ 4 ሺሕ 100 ኪሎ ግራም ዕቃ ከቀረጥ ነፃ እንዲገባ እንደተፈቀደለት በማስመሰል ወደ አገር ውስጥ ዕቃው መግባቱን የጉምሩክ ኮሚሽን ገለፆ ነበር።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here