የስኳር ኮርፖሬሽን ለስድስት ዓመታት ኦዲት አልተደረገም

0
751

ሒሳባቸውን በወቅቱ ኦዲት ካላስደረጉ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ውስጥ ስኳር ኮርፖሬሽን ላለፉት ስድስት ዓመታት ኦዲት ባለመደረግ ከፍተኛው መሆኑ ታወቀ። ኮርፖሮሽኑ ላለፉት ስድስት ዓመታት የተጠራቀመውን ሒሳብ በዚህ ዘመን አዲስ በተቋቋመው አማካሪ ፕሮጀክት ኦዲት በማስደረግ ለማጠናቀቅ ማሰቡ ታውቋል።

የስኳር ኮርፖሬሽን ኮርፖሬት ኮሙዩኒኬሽን ኀላፊ የሆኑት ጋሻው አይችሉህም እንደገለጹት ኮርፖሬሽኑ በአሁኑ ሰዓት ላለፉት ዓመታት ኦዲት ያልተደረገበት ዋናኛ ምክንያት በአገሪቱ የሚገኙ ሁሉም ነባርና አዳዲስ ስኳር ፋብሪካዎች እና ኮርፖሬሽኑ የሚካሔደውን የመስኖና የቤቶች ግንባታ ተከናውነው ባለማለቃቸው መሆኑን ተናግረዋል። እንዲሁም ጅምርና አዳዲስ የስኳር ልማት ፕሮጅክቶችን ኦዲት አድርጎ ለማቅረብ አንድ ዓመት በጣም ትንሽ ከመሆኑም ባሻገር ከዚህ ቀደም ኮርፖሬሽኑ ሳይቋቋም በፊት ተንከባለው የመጡትን ውዝፎችን ኦዲት አድርጎ ለማቅረብ ሰፊ ጊዜ ስለወሰደ ነው ሲሉ ጠቁመዋል።

በተመሳሳይም ሒሳባቸውን በወቅቱ ኦዲት ካላስደረጉ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ውስጥ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን፣ ብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር እንዲሁም የኢትዮጵያ ነዳጅ ድርጅት ለአምስት ዓመታት ኦዲት ያላሰደረጉ ሲሆን ሌሎች 44 ድርጅቶችም ከአራት እስከ አንድ ዓመት ድረስ ኦዲት እንዳላስደረጉ ዋና ኦዲተር አስታወቋል።

በአገሪቱ የመጀመሪያው ስኳር ፋብረካ ወንጂ ሲሆን በ1950 ተመስርቶ ከ30 ሺሕ ሔክታር በላይ እርሻ ቦታን ላይ 4 የሚሆኑ አነስተኛ እና መካከለኛ ፋብሪካዎች በማስተዳደር አጠቃላይ 12 ሺሕ 500 ቶን የመፍጨት አቅም አለው።የኢትዮጵያ ዓመታዊ የስኳር ማምረት አቅም 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ሲሆን ይህም ከ50 በመቶ ዓመታዊ ፍጆታ በታች ሲሆን ይህንንም ክፍተት ለመሙላት አገሪቱ ብዙ ሺሕ ቶን ስኳር ከውጪ ታስገባለች።

አገሪቷ የስኳር ፋብሪካዎችን ግንባታ ማምረት ከጀመረች 60 ዓመት በላይ ያስቆጠረች ቢሆንም በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የሕዝብ ቁጥር እና የፍጆታ መጠን ተከትሎ ከፍተኛ የሚባል የስኳር እጥረት በተደጋጋሚ ሲከሰት ይታያል።ሆኖም በአሁኑ ወቅት አገሪቱ አጠቃላይ ሰባት የስኳር ፋብሪካዎች ሲኖሩዋት እነሱም ቆየት ብለው የተመሰረቱ የትንዳሆ፣ አርጆ ዴዴሳ፣ ቀሰም እና በከፊል ሥራ የጀመረው አሞ ኩራዝ ይገኙበታል።

ከዚህ ቀደም ሜቴክ ከጀመራቸው ዐሥር ፕሮጀክቶች አንዳቸውንም ማጠናቀቅ ሳይችል የተነጠቀ ሲሆን ከሜቴክ ተነጥቆ ለቻይና ኩባንያ የተሰጠው ኦሞ ኩራዝ ኹለት ተጠናቆ ወደ ምርት ሒደት ሲገባ የወልቃይት ስኳር ፋብሪካም እንደዚሁ ተነጥቆ ለሌላ የቻይና ኩባንያ መሰጠቱ አይዘነጋም።

እነዚህም በአጠቃላይ እስከ 500 ሺህ ቶን የሚጠጋ ዓመታዊ ምርት ሲኖራቸው አዳዲስ በመገንባት ላይ ያሉት የወልቃይት እና የጣና በለስ የስኳር ፋብሪካዎች ተጠናቀው ወደ ሥራ ሲገቡና ከላይ የተጠቀሱት በቅርቡ ሥራ የጀመሩት ፋብሪካዎች በሙሉ አቅም ማምረት ሲጀምሩ አጠቃላይ የአገሪቱን ምርት ሰባት ሚሊዮን ኩንታል እንደሚሆን ይጠበቃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here