ንግድ ባንክ ራሱ ያወጣውን የሕንፃ ሐራጅ አሸነፈ

0
691

ንግድ ባንክ ለድሬ ኢንዱስትሪዎች በብድር መተማመኛ የያዘውን ሕንፃ ለመሸጥ ባወጣው ጨረታ ላይ 99 ነጥብ 8 በመቶ የባንኩ ንብረት የሆነው ኮሜርሻል ኖሚኒስ 75 ሚሊዮን ብር በመስጠት ያለፈው አርብ፣ ግንቦት 30/2011 ጨረታውን አሸነፈ።

በሚያዚያ 30/2011 በጋዜጣ ታትሞ በወጣው የግልፅ ጨረታ ጥሪ መሰረት በመነሻ ዋጋ 38 ነጥብ 7 ሚሊዮን ለሽያጭ የቀረበው ሕንፃ በሴቭ ዘ ቺልድረን ኪራይ ሥር የነበረ እንደሆነም ተገለጿል። በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ የሚገኘው እና በ637 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ሲሆን ባለ ስምንት ፎቅ ሕንፃ ለቢሮ አገልግሎት የሚውል ሕንጻ ነው።

በጨረታው የተሳተፉት የባንኩ የሠራተኛ ማኅበር እና ከሊፋ ሕንፃ ሲሆኑ ጨረታውን ያወጣው ባንክ ንብረት የሆነው እና የ0.2 በመቶ ድርሻ ለማኔጅመንቱ በመስጠት ባንኩ የጠቀለለው ኮሜርሻል ኖሚኒስ ከፍተኛ ዋጋ በማቅረብ ማሸነፉ ተገልጿል። በጨረታውም ያሸነፈው ድርጅቱ ከፊሉን ገንዘብ ከባንኩ በብድር የማግኘት መብት የተሰጠው ሲሆን ያሸነፈበትን ገንዘብም በ15 ቀናት ውስጥ አጠቃሎ ይከፍለል ተብሎ ይጠበቃል።

ባንኩ በሕጉ መሰረት የንግድ ሥራ መሥራት የማይፈቀድለት መሆኑን አስመልክቶ ከቀድሞው የኮንስትክሽን እና ቢዝነስ ባንክ ጋር በጋራ በተለያዩ የአገልግሎት ሥራዎች ተሰማርቶ የንግድ ሥራ እንዲሠራ ኮሜርሻል ኖሚኒስን አቋቁሞታል። ንግድ ባንክ ኮንስትክሽንና ቢዝነስ ባንክን በመጠቀለለበት ወቅትም በሕጉ መሰረት የሚጠየቀውን ግዴታ ለማሟላት ሲባል በኮሜርሻል ኖሚኒስ የማኔጅመንት አባለት ሥም 0.2 በመቶ ድርሻ እንዲዝይ በማድረግ ሲንቀሳቀስ ቆየቷል።

ምንም እንኳን አዲስ ማለዳ የንግድ ባንክንም ሆነ የኮሜርሻል ኖሚኒስን ኀላፊዎችን በስልክ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት ባይሳካም እንዲህ ዓይነት የግዢ ውል በኹለቱ መካከል ሲፈፀም የመጀመሪያው እንደሆነ እና ይህም ሌሎቹን ተጫራቾች ምርጫ ያሳጣ መሆኑን ከተጫራቾቹ አንዱ ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

በውል ሕጉ መሰረት አንድ ሰው ከራሱ ጋር ውል መፈፀም የማይችል ቢሆንም ኹለት ተለያየ የሕግ ሰውነት ያላቸው ድርጅቶች ግን መገበያየት እንደሚችሉ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የሕግ ባለሞያ ይገልፃሉ። ይህም በእናት ድርጀት እና በሥሩ ባሉ ድርጅቶች መካከል የሚደረግ ግብይትን ጨምሮ ሌሎች ግብይቶችን የሚጠቃልል ነው ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here