ሕግ ይከበር፡- “ሆደ ሰፊነትም” ልክ አለው!

0
771

ባለፈው ሳምንት ሐሙስ፣ ግንቦት 29/2011 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከተለያዩ የሕግ አካላት ጋር በጽሕፈት ቤታቸው ውይይት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። ባለሙያዎቹ ብዙ ከሙያቸው ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን ያቀረቡ ሲሆን ሕግ ማክበርንና የሕግ ሉዓላዊነትንም በተመለከተ መንግሥት ያሳየውን ዳተኝነት ግን አጽዕኖት ሰጥተውት ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሕግ ሉዓላዊነት ጋር በተያያዘ ለተጠየቁት ጥያቄዎች ምላሻቸውንም ሰጥተዋል። በምላሻቸውም ሕግ በኹለት መልክ እንደሚከበር በመጥቀስ አብራርተዋል። ሕግ የሚከበረው በሕግ ስርዓቱ ማለትም በሕግ አካላት በሚወሰድ እርምጃ ብቻ ሳይሆን የዜጎችን አስተሳሰብና አመለካከት በመለወጥም ነው ብለዋል።

በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የደቦ ፍርዶች፣ ግድያዎች፣ ብጥብጦች፣ ወንጀሎች፣ ዘረፋና መሰል ሕገ ወጥ ድርጊቶች ሲፈጸሙ በተለይ የፌደራል መንግሥት አንድም አስቀድሞ የመከላከል ሥራ ሲሠራ አሊያም ድርጊቱ ከተፈፀመ በኋላ በፍጥነት እጁን በማስገባት የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ ያለመቻሉ ወቀሳና ትችት እያስነሳበት ለመሆኑ ምስክር መጥራት አያሻም። ድርጊቶቹ በራሳቸው አፋ አውጥተው ይናገራሉና።

ይህ ለምን ሆነ የሚለውን ለመመለስ ቀላል እንዳሆነ ይታወቃል ምክንያቱም በኢሕአዲግ ውስጥ ከተፈጠረው ለውጥ ጋር ተያይዞ ብዙ እስካሁን ምላሽ የሚያሻቸው ጥያቄዎች በመኖራቸው ነው።

እንደሚታወቀው በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ መንግሥት የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያት በዜጎች መካከል ሊነሱ የሚችሉ ግጭቶች የተወሰነ መብታቸውን ቆርጠው የሰጡት መንግሥት እንዲዳኛቸው ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ባለው ሁኔታ መንግሥት በተሰጠው ሕጋዊ ሥልጣን ኀይል በሚፈለገው ደረጃ ሕግ ማስከበር ካልቻለ፤ ከመንግሥት የበለጠ ለነፃነት አደገኛ የሆነ ስርዓት አልበኝነት ሊፈጠረ ይችላል። መንግሥት በየቦታው የሚፈጠሩት የጎበዝ አለቆች ኅብረተሰቡን ሊታደግና ሰላምና ደኅንነት ሊያስጠብቅ አይችልም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በመድረኩ ላይ ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ ሳይሆን የዜጎችን አስተሳሰብ መለወጥ ለሚለው ቅድሚያ እንደሚሰጡ አመልክተዋል። በርግጥም የዜጎችን ባሕርይና አስተሳሰብ መለወጥ በጣም አስፈላጊና ተገቢ ነው። ይሁንና የባሕሪና የአመለካከት ለውጥ በአንድ ጀምበር የሚመጣ ባለመሆኑ ይህ ሥራ የረጅም ጊዜ ሥራ መሆን ይገባዋል፤ በአንድ ቀን ወይም በአንድ ዓመት ውስጥ ተፈፃሚ የሚሆን አይደለም።

በመድረኩ ላይ በጠቅላይ ሚኒስትሩና በተሳታፊዎች ችግር ሆነዋል ተብለው ከተጠቀሱት መካከል ሙስና፣ የአስፈጻሚው የመንግሥት አካል አቅም ማነስ፣ የሕግ ክፍተት፣ የሕግና የፖለቲካ ሚዛን፣ ብሔርን መሰረት ያደረገ ሠራተኛ ቀጠራ ወዘተ ናቸው። እነዚህን ሁሉ ችግር መኖራቸው ግልጽ ነው፤ በአንድም በሌላ በኩል ኢትዮጵያ ሰላም እንድታጣ፣ መረጋጋት እንዲርቃትና ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳትገነባ እንቅፋት የሆኑ ጉዳዮች ናቸው።

በፌደራል መንግሥቱ በኩል የታየው የበዛ ሆደ ሰፊነት ወይም አንዳንዶች በትችት መልክ እንደሚገልፁት መንግሥት ሕግን በማስከበር ላይ ያሳየው ዳተኝነት ወይም ቸልተኝነት ወደ ለየለት ስርዓት አልበኝነት፣ አገሪቱንም ተስፋ የተጣለችበትንም ለውጥ ወደማይፈለግ መንገድ እንዳይወስዳት የተነሳውን ሥጋት ለብዙዎች ሚዛን የሚደፋ ነው። ይህ የዜጎች ሥጋት አዲስ ማለዳም ተገቢ ነው ብላ ታምናለች።

ስለሆነም በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ወሳኝ ጉዳይ ሆኖ የሚወጣው ምን መደረግ ይኖርበታል የሚለው መሆኑ ሊሰመርነት ይገባል። በተለይ መገናኛ ብዙኀን አዲስ ማለዳን ጨምሮ ይህንን ጉዳይ ዋና አጀንዳ ማድረግ ይገባቸዋል፤ ሕዝብ እንዲያውቅ በማድረግና የመንግሥት አካላት ላይ ደግሞ ከፍተኛ ጫና በመፍጠር አገሪቱ የምትሔድበት አቅጣጫ መግራትና ወደታለመለት ዴሞክረሲያዊ ስርዓት ግንባት እንድታመራ መርዳት ያስፈልጋል።

የሆነው ሆኖ መንግሥት ሰላሟና ደኅንነቷን የተከበረች አገር እንዲሁም መሰረታዊ ሕግ የሚከበርባት አገር ለማድረግ ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ይገባዋል። መንግሥት ለውጡን ለማስቀጠልም ሆነ የሚታለመውን ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት ቅድሚያ ሰጥቶ መሥራት ከሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች መካከል በመጀመሪያው ረድፍ ላይ የሚመጡት የዜጎችን የመኖር፣ የመሥራት እና በነፃነት የመንቀሳቀስ መብቶች ይገኙበታል።

ስለዚህ በተደጋጋሚ እንደሚገለጸውና አዲስ ማለዳም በአጽንዖት ማስተላለፍ የምትፈልገው በከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና በታችኛው መዋቅር በሚገኙት ትንናሽ ባለሥልጣናት መካከል በግልጽ የሚታየው ሰፊ ክፍተት ላይ በትኩረት በመሥራት ክፍተቱን ማጥበብ ይገባል ትላለች። ይህንንም ተፈፃሚ ለማድረግ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መንግሥት ጠንከር ያለ ቆራጥ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ ይገባዋል ስትል አዲስ ማለዳ መልዕክቷን ታስተላልፋለች።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here