በኢትዮጵያ የተከሰተውን የኀይል መቆራረጥ ተከትሎ የሲሚንቶ አቅርቦት በመቀነሱ በገበያ ላይ የ42 ነጥብ 8 በመቶ የዋጋ ጭማሪ በመታየቱ ምክንያቱ ምጣኔ ሀብታዊ መሆን አለመሆኑን የንግድ ውድድር እና የሸማቾች መብት ጥበቃ ባለሥልጣን ምርመራ ማካሔድ ጀመረ። የባለሥልጣኑ የምርመራ ቡድን አምስት ዋና ዋና የሲሚንቶ አምራቾችን ቃል የተቀበለ ሲሆን የተወሰኑት የዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውን ቢያስረዱም አብዛኞቹ ግን ምንም ዓይነት ጭማሪ አላደረጉም።
አዲስ ማለዳ በመገናኛ እና ሾላ አካባቢ የሚገኙ የሲሚንቶ ነጋዴዎችን በማነጋገር ለመረዳት እንደቻለችው ከዚህ ቀደም ለፋብሪካዎች የአቅርቦት ትዕዛዝ ባቀረቡ በቀናት ውስጥ ተፈጻሚንት ያገኙ እንደነበር እና አሁን ግን የኀይል መቆራረጡን ምክንያት በማድረግ ረዘም ላለ ጊዜ ወረፋ እንዲይዙ መደረጋቸውን ይናገራሉ።
ይሁንና ነጋዴዎች የአቅርቦት እጥረት አለ በማለት ከደላሎች ጋር በመመሳጠር ምርት በማከማቸት እና ሰው ሰራሽ እጥረት በመፍጠር ከተከሰተው የዋጋ ንረት ዋነኛ መሰረት መሆኑን ጋዜጣችን ያነጋገረቻቸው ቸርቻሪዎች ተናግረዋል።
“በመብራት አቅርቦት መቆራረጥ [ምክንያት] የሲሚንቶ እጥረት አጋጥሟል ነገር ግን ይህን የሲሚንቶ እጥረቱን እንደ ክፍተት በመጠቀም ነጋዴው በራሱ ዋጋ ሊመጨመር ይችላል” የሚሉት የሐበሻ ሲሚንቶ የሽያጭ ሠራተኛ ዳግማዊ ተካ ናቸው። አያይዘውም ሐበሻ ሲሚንቶ ፋብሪካ የዋጋ ጭማሪ ካደረገ ሦስት ወራት ማስቆጠሩን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።
ዳግማዊ የኀይል መቆራረጡ በከፍተኛ ኀይል ተጠቃሚዎች ላይ በተለይም በሲሚንቶ አምራቾች ላይ ከፍተኛ ጫና እንደሚያሳድርና በሥራቸው ላይም መስተጓጎልን እንደሚፈጥር አስረድተዋል፤ የነጋዴዎች ትዕዛዝ በቀናት ውስጥ ይስተናገድ እንዳልነበር ፍላጎቱና አቅርቦቱ ስለማይገናኝ እስከ 15 ቀናት አንዳንዴም ከዛ በላይ ሊጠብቁ እንደሚችሉም ገልጸዋል። በምርት በኩልም ፋብሪካቸው ከዚህ በፊት በመደበኛነት ያመርት ከነበረው የምርት መጠን እስከ 30 በመቶ የሚደርስ የምርት መቀነስ እንዳጋጠመው ዳግማዊ ለአዲስ ማለዳ የገለፁ ሲሆን፤ ይህን ተከትሎም በነጋዴዎች በኩል የምርት እጥረት ይኖራል የሚል ሥጋት በመኖሩ በብዛት አዘዋል ብለዋል።
የዋጋ ንረቱን በሚመለከት የንግድ ውድድርና ሸማቾች መብት ጥበቃ ባለሥልጣን ያለአግባብ የገበያ ውድድር የፈጠሩ ካሉ በሕግ ከመጠየቅ ባለፈ ከንግድ እና ኢንዱስትሪ እንዲሁም ከተለያዩ አካላት ጋር በመተባበር የማረጋጋት ሥራ እንደሚሠራ የባለሥልጣኑ የክስ ምርመራና ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክተር ጌትነት አሸናፊ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በምርመራውም ኢፍትሐዊ ድርጊቶች መኖራቸው ከተረጋገጠ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚጣልባቸውም አክለዋል።
ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011



