አኳ ሴፍ በኪሳራ አንደኛውን ፋብሪካ ዘጋ

0
1096
  • ድርጅቱ 150 ሠራተኞቹን በትኗል

በደብረ ብርሃን ከተማ ከዐሥራ ሦስት ዓመት በፊት የተመሰረተው አኳ ሴፍ የታሸገ ውሃ ማምረቻ በሦስት ዓመት ውስጥ 102 ሚሊዮን ብር በመክሰሩ ፋብሪካውን መዝጋቱን አስታውቋል። በድርጅቱ ይሠሩ የነበሩ 150 ሠራተኞችም ሥራ ማቆማቸውም ታውቋል።

በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የፋብሪካው ሥራ አስኪያጅ የሆኑት በፍቃዱ ካፌን ሰኞ፣ ሰኔ 3 የድርጅቱ ቦርድ አባላት ተሰብስቦ ከመከረ በኋላ፣ ፋብሪካው አዋጪ ሆኖ ስላላገኘውና በዚህ ከቀጠለ ሌሎች እህት ድርጅቶችንም አደጋ ውስጥ ሊከት ስለሚችል መቆም አለበት ብሎ ወስኗል ብለዋል።

ሥራ አስኪያጁ አክለውም ለመዘጋቱ ምክንያት የሆነው ድርጅቱ ሥራ ሲጀምር ወደ አገር ውስጥ ያመጣቸው ዕቃዎች ያረጁ በመሆናቸው እና አሁን ላይ የምርት አቅማቸው በመድከሙ የምርት ማሽቆልቆል በማጋጠሙ ነው ብለዋል።

ፋብሪካው ከመዘጋቱ በፊት በሠራተኞችና አመራሩ መካከል አለመግባባት እንደነበር ለአዲስ ማለዳ የገለጹት ሥማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የድርጅቱ ሠራተኛ፣ ሠራተኛው በተደጋጋሚ የመብት ጥያቄዎችን ያነሳ እንደነበር ገልፀዋል። “ቀጥታ ከሚመለከታቸው የድርጅቱ ባለቤቶች ጋር አገናኙን ብለን ብንጠይቅም ምላሽ አላገኘንም፣ የፋብሪካውን ባለቤት አገናኙን የሚል ጥያቄ በማንሳታችን የፋብሪካው ኀላፊዎች ከሥራ አግደውናል” ሲሉም ተናግዋል። የመብት ጥያቄዎች በተደጋጋሚ ሲነሱ ምላሽ አለማግኘታቸውን የገለጹት እኚሁ ግለሰብ፣ ከደሞዝ ጭማሬ ጋር በተያያዘ ከሠራተኛው ተደጋጋሚ ጥያቄዎች ይነሱ እንደነበረም አብራርተዋል።

በአሁኑ ሰዓት ፋብሪካው እድሳት ላይ በመሆኑ ሥራ አቁሟል መባሉን እንደሚያውቁ የጠቆሙት ሠራተኞቹ፣ የድርጅቱ አመራሮች ፋብሪካውን ከመዝጋታቸው በፊት እኛን ሰብስበው ሥራው ስለቆመበት ምክንያት ሊያዋዩን ይገባ የነበረ ብለዋል። ድርጅቱን ላለፉት ኹለት ሳምንታት ስለቆመበት ምክንያት የምናውቀው ነገር የለም ሲሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በፍቃዱም የሠራተኞቹን ጥያቄ ሲመልሱ ፋብሪካው ከተዘጋ ከሳምንት በላይ መሆኑን ጠቁመው፣ ሰኞ፣ ሰኔ 3/2011 ሠራተኞቹን ሰብስቦ ማነጋገሩንና ፋብሪካውን በይፋ መዝጋቱን ለሠራተኛው ማስታወቁን ተናግረው፣ በአሰሪና ሠራተኛ አዋጅ 377 መሰረት የሠራተኛው ጥቅማጥቅም ተከብሮ እንደሚሸኙ በይፋ መናገራቸውን አውስተዋል።

ከድርጅቱ ሠራተኞች ጋር አልፎ አልፎ ከሚታዩ አለመግባባቶች ባለፈ፣ ለድርጅቱ በሕጋዊ መንገድ የቀረቡ አቤቱታዎች አለመኖራቸውን የገለጹት በፍቃዱ ከሠራተኛው ጋር በሰላማዊ መንገድ ለመለያየት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
አኳ ሴፍ ውሃ በዛው በደብረ ብርሃን ጠባሴ አካባቢ ኹለተኛ ፋብሪካውን ከፍቶ በመሥራት ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ የቀድሞው ፋብሪካ በመዝጋትና ሠራተኛውን በመበተን በአንዱ ፋብሪካ ብቻ በማምረት ላይ ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 32 ሰኔ 8 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here