የቀድሞ አርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮችን በተመለከተ ኢዜማ ከኮሚሽነሩ ጋር መከረ

0
653

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ፓርቲ (ኢዜማ) ሥራ አስፈጻሚ አባላት ከብሔራዊ የአደጋ ሥጋት እና ሥራ አመራር ኮሚሽንነር ምትኩ ካሳ ጋር በኤርትራና በአገር ውስጥ የነበሩ የአርበኞች ግንቦት 7 ታጋዮችን መልሶ በማቋቋም ዙሪያ ሰኔ 10/2011 ውይይት ማካሔዳቸው ታወቀ። በውይይቱ ላይ የሚመለከታቸው የኮሚሽኑ ባለሙያዎች መሳተፋቸውም ታውቋል።

በውይይታቸው ወቅት፣ ኮሚሽነሩ መልሶ ማቋቋምን በተመለከተ ኹለት ነገር ሊሠራ እንደታሰበ ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት እማዋይሽ ዓለሙ፣ የመጀመሪያው ለዕለት መንቀሳቀሻ የሚሆን ገንዘብ እንዳይቋረጥ እየተጣረ እንደሆነና፣ በኹለተኛነት ደግሞ ወደ መደበኛ ሕይወታቸው እንዲመለሱ ለማድረግ ሥራ መፍጠርና ማመቻቸት ላይ እየተሠራ እንደሆነ ገልፀዋል።

ኮሚሽነሩ የጀርመን መንግሥትና ሌሎች አገራት እርዳታ እንሰጣለን ብለው ቃል ገቡ እንጂ፣ ገንዘቡ ገና አልመጣም፤ እኛም ጋር በቀጥታ የገባ የለም፤ የእነሱ ድጋፍ መጣም አልመጣም እኛ ግን መልሶ ማቋቋሙን እንሠራለን ማለታቸውን እማዋይሽ ተናግረዋል።

አያይዘውም፣ ከኤርትራ የመጡትን እስካሁንም ድጋፍ እያደረጉላቸው መሆኑን ገልጸው፣ ነገር ግን ኤርትራ በረሃ ከነበረው ባልተናነሰ በአገር ውስጥ ተበታትነው የነበሩ ታጋዮችና ለረዥም ዓመታት በእስር ላይ የነበሩ ስላሉ ሁሉንም ያማከለ ሰፊ ሥራ ለመሥራት ኮሚሽኑ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ አስታውቀዋል።

የአርበኞች ግንቦት 7ንም ሆነ የሌሎች ድርጅቶችን ወደ አገር ቤት የገቡ ታጋዮችን “መልሶ ማቋቋምን የሚመለከተው መንግሥትን ነው ያሉት ኮሚሽነሩ፣ የፓርቲዎች ሥራ ለኮሚሽኑ የተጣራ መረጃ መስጠትና ክትትል ማድረግ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

የኢዜማን ፓርቲ ወክለው የተገኙት የጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች ኮሚሽኑ የጠየቀውን መረጃ በፍጥነት አሟልተውና ሰርተው እንደሚመጡ በመግለጽ፣ ከኮሚሽኑ ጋር በመሆን ጉዳዩ እልባት እንዲሰጠው እንደሚሠሩ እማዋይሽ ተናግረዋል።

ከአርበኞች ግንቦት 7 ለአንድነትና ዴሞክራሲ ንቅናቄ መክሰም በኋላ፣ ኢዜማ የንቅናቄውን ታጋዮች መልሶ ለማቋቋም ሲሠራ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here