ሕጋዊ የስፖርት አወራራጆቹ

0
1172

ይርገዱ ጫኔ ኢራቅ በነበረችበት ጊዜ ለዓመታት በቱርኮች ባለቤትነት በሚመራው የስፖርት ማወራረጃ ተቋም ውስጥ በመጀመሪያ በጽዳትነት ቀጥሎ ደግሞ በገንዘብ ያዥነት አገልግላለች። ይህም የስፖርት ውርርድ ሥራ ምን እንደሚመስል ጥልቅ ግንዛቤና እውቀት እንዲኖራት አስችሏታል። በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆና ለጥቂት ዓመታት ከሠራች በኋላ እውቀትዋን ወደ አገሯ ይዛ በመምጣት ለራስዋና ለሌሎች ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ወሰነች።

ኢትዮጵያ ከተመለሰች በኋላ ሥራዋን ለመጀመር ስትነሳ የገጠማት የመጀመሪያው ፈተና ሥራው በአገራችን ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ ሥራውን ለማስጀመር የሚረዳ ሕጋዊ ማዕቀፍ የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር አለማዘጋጀቱ ነበር። ነገር ግን ይህ ተስፋ አላስቆረጣትም ይልቅስ ብሔራዊ ሎተሪን በማሳመንና የስፖርታዊ ውርርዶች የሚመሩበት አዲስ ሕግ እንዲወጣ በማድረግ በአንድ ሚሊዮን ብር መነሻ ካፒታል ከሦስት ዓመት በፊት አክሱም ቤቲንግን በዘርፉ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ተመሰረተ። “የሥራ ዘርፉን ጀማሪዎች በመሆናችን በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመውናል። በተለይ ሥራው ለአገራችን እንግዳ በመሆኑ ከሕግ ማዕቀፍ ባለመኖሩ ድርጅታችንን ለማቋቋምና ህልማችንን ዕውን ለማድረግ ጊዜ ወስዶብናል” በማለት ይርገዱ ስለመጀመሪያውና ፈታኙ እንቅፋት ትናገራለች።

አክሱም ቤቲንግ አሁን ሥራውን ከጀመረበት ጊዜ ጋር ሲነጻጸር ካፒታሉ በአምስት እጥፍ ያደገ ሲሆን 25 ቋሚና 150 ጊዜያዊ ሠራተኞች አሉት። ይርገዱ ድርጅትዋን ከመሰረተችበት ጊዜ ጋር ሲነጻጸር አሁን ስፖርት ቤቲንግ በመታወቅ ላይ ያለና ከፍተኛ ተቀባይነት እያገኘ የመጣ የመዝናኛ ዘርፍ እየሆነ ይገኛል። ለዚህም ማሳያው ዐሥር የንግድ ፈቃድ የወሰዱ ድርጅቶች መኖራቸውና አምስት ኩባንያዎች ደግሞ ዝግጅት ላይ መሆናቸው ነው።

በስፖርት ቤቲንግ የሥራ ዘርፍ ላይ የተሰማሩት ድርጅቶች አጠቃላይ ካፒታል ሀያ ሚሊዮን እንደሆነ የሚገመት ሲሆን ለብዙ ሰዎች የሥራ ዕድል እየፈጠሩና ለደንበኞቻቸው የገቢ ምንጭ እየሆኑ ይገኛሉ። ለዚህም ይመስላል ገና በጠዋቱ የስፖርት ውርርድ የሚከናወንባቸው ቤቶች ሲከፈቱ ዳንኤል ፍቅሬን መሰል ወጣቶች ለመወራረድና ስፖርታዊ ውድድሮችን ለማየት ቤቱን የሚሞሉት። በሥራ ቀናት በአማካይ 450 ሰዎች ከአክሱም ቤቲንግ የመወራረጃ ትኬቶችን ለመግዛት የሚመጡ ሲሆን ቅዳሜና እሁድ ይህ ቁጥር ወደ አንድ ሺሕ ከፍ ይላል።

አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኝ አንድ የግል ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የአንደኛ ዓመት የአካውንቲን ተማሪ የሆነው ዳንኤል የዐሥራ ዘጠኝ ዓመት ወጣት ነው። ዳንኤል ከልጅነቱ ጀምሮ የእግር ኳስ አድናቂ የነበረ ቢሆንም ስለሕጋዊ የስፖርት ውርርድ ከጓደኞቹ የሰማው በቅርቡ ነው። ምንም እንኳን የመጀመሪያ ውርርዱን ቢሸነፍም ከአምስት ወር በፊት ግን በ25 ብር በገዛው ትኬት ከጋላክሲ ቤቲንግ አምስት ሺሕ ብር ማሸነፍ ችሎ ነበር። ዳንኤል “መጀመሪያ ላይ ለመዝናናት ነበር ትኬት የምገዛው አሁን ግን ከመዝናናት አልፎ እንደ አንድ የገቢ ምንጭ ነው የምቆጥረው” ይላል። እንደ ግርማ አለሙ (ሥሙ የተቀየረ) ያሉ ወጣቶች ደግሞ አሸናፊውን ቀድመው መገመትን እንደመዝናኛ ነው የሚቆጥሩት። ግርማ ከአንድ ዓመት በፊት ጀምሮ የጋላክሲ ቤቲንግ ደንበኛ የነበረ ሲሆን አሁን ደግሞ ከጋላክሲ በተጨማሪ የአቢሲኒያ ቤቲንግ ድኅረ ገጽ መጠቀም ጀምሯል። “ሱሰኛ አይደለሁም። ነገር ግን ቅዳሜና እሁድ የእግር ኳስ አድናቂ ከሆኑት ጓደኞቼ ጋር ጥሩ ጊዜ ለማሳለፍ ስል አሲዤ እጫወታለሁ። በዐሥር ብር የገዛዋት ትኬት እምብዛም የማያጓጓን ጨዋታ አጓጊ ታደርገዋለች” በማለት ከአንድ ወር በፊት ሦስት ሺሕ ከጋላክሲ እንዲሁም ከሰባት ወር በፊት ደግሞ አንድ ሺሕ ብር ከአቢሲኒያ አወራራጆች ማሸነፉን የሚናገረው ግርማ ለምን የስፖርት ውርርድ ትኬቶችን እንደሚገዛ ያስረዳል። አብዛኞቹ የእነዚህ አወራራጅ ደንበኞች ከዳንኤልና ከግርማ ጋር የሚመሳሰል አስተያየት ነው የሚሰጡት።

በወፍ በረር በአዲስ አበባ ውስጥ ያሉ ስፖርት ባሮችን ያየን እንደሆነ ስፖርታዊ ውርርዶች ምን ያህል የከተማ ሕይወት አንዱ አካል እየሆነ እንደመጣ መገንዘብ ይቻላል። ምንም እንኳን ከተጫዋቾች አንጸር ነገሩን ካየነው ማንም መወራረድ የፈለገ ሰው በአቅራቢያው አገልግሎቱን ወደሚሰጡት ቦታዎች ሔዶ ከ30 እስከ 300 ሺሕ ብር በማስያዝ መሳተፍ የሚችል ቢሆንም ከስፖርት ቤቲንግ አገልግሎት ሰጪዎች አንጻር ካየነው ግን ነገሩ ቀላል አይደለም። ተቋማቱ የእያንዳንዱን ስፖርት ጨዋታ ተወዳዳሪ የማሸነፍ ዕድል ቀድሞ በመገመት ከፍተኛ የማሸነፍ ዕድል ላለው ቡድን ትንሽ ክፍያ መመደብን ጨምሮ አገልግሎታቸው ውስጥ ያካተቱትን ከሰማንያ በላይ አማራጮችን በጥንቃቄ ማዘጋጀት ይጠይቃል። ይህንን በአግባቡ የተረዳ ተወዳዳሪም በዛ ያለ ብር የማግኘት ዕድሉ እየሰፋ ይሔዳል። ለምሳሌ አክሱም ቤቲንግ የድርጅታቸው ከፍተኛ ክፍያ የሆነውን 300 ሺሕ ብር ለሦስት ደንበኞቹ ከፍሏል። የአክሱም ቤቲንግ የገንዘብና አስተዳደር ኀላፊ የሆነው ናዚም እንደገለጸው ከሆነ ድርጅታቸው በወር በአማካይ በጠቅላላው እስከ 7 ሚሊዮን ብር ለደንበኞቻቸው የሚከፍሉ ሲሆን ወርሃዊ ገቢያቸው ደግሞ 300 ሺሕ ይደርሳል።

ከአክሱም ቤቲንግ በኋላ ወደ ኢንደስትሪው የገቡት እንደ ጋላክሲ ቤቲንግ ያሉ የስፖርት አወዳዳሪ ተቋማትም ተመሳሳይ ልምድ አላቸው። በቅርቡ ጋላክሲ ቤቲንግ የ300 ሺ ብር ዋጋ ያላቸውን በርካታ ትኬት ለገዛ አንድ ደንበኛቸው ሁሉንም ማሸነፍ በመቻሉ 3 ሚሊዮን ብር ከፍሎታል። “ሥራው በባሕሪው የሚዋዥቅ በመሆኑ ቀድሞ ትርፍና ኪሳራን መተንበይ አስቸጋሪ ነው። የዚህ ወር ገቢ የሚቀጥለው ወር ወጪ ሊሆን ይችላል” የምትለው የጋላክሲ ቤቲንግ ባለቤት የሆነችው ሳሮን ሰለሞን ናት።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንዳንዶች ስፖርት ቤቲንግ ሱስ የመሆን ዕድል አለው የሚል ሥጋት አላቸው። ዳንኤል ለዚህ ሥጋት ጥሩ ማሳያ ነው። ለትምህርት ቤት ክፍያ የሚሆነኝን ክፍያ ትኬት ገዝቼበት ነበር። በወቅቱ ጓደኞቼ ባያበድሩኝ ኖሮ ትምህርቴን ለማቋረጥ እገደድ ነበር ብሏል። ናዚም ምንም እንኳን ጨዋታው ሱስ የመሆን አቅም ቢኖረውም ከ18 ዓመት በላይ ያሉ እና ማገናዘብ የሚችሉ ሰዎች በፈቃዳቸው የሚጫወቱት ጨዋታ በመሆኑ አስጊ አይደለም በማለት ይከራከራል። በሌላ በኩል ደግሞ የአቢሲኒያ ቤቲንግ ባለቤት ስፖርት ቤቲን ወጣቶችን እንደ መጠጥ፣ ሲጋራና ሺሻ ካሉ አጓጉል ሱሶች ይጠብቃል ባይ ነው። እንዲሁም ሰዎች እየተዝናኑ ተጨማሪ ገቢ የሚያገኙበት መንገድ ነው ይላል። የስፖርት ጋዜጠኛ የሆነው ግርማቸው ከበደ በበኩሉ ድሮም ስፖርታዊ ውርርዶች በልማድ በየሰፈሩ የሚከናወን ተግባር መሆኑን ገልጾ እንዳሁኑ ሕጋዊ በሆነ መንገድ መጀመሩ መልካም መሆኑን ያምናል፤ ነገር ግን ይህ ዘርፍ በጠንካራ ሕጎች ቁጥጥር ሊደረግበት እንደሚገባ አሳስቧል። “ጠንካራ ሕግ ከሌለ ግን ያኔ ነው ችግር የሚፈጠረው” በማለትም አክሏል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here