በመንግሥት ቸልተኝነት ውንብድና በስፖርት ሜዳዎች

0
735

በመቐለ ሰባ እንደርታ እና በኢትዮጵያ ቡና የእግር ኳስ ቡድኖች መካከል ማክሰኞ፣ ሰኔ 11 በአዲስ አበባ ስታዲየም የሚካሔደውን ግጥሚያ ተከትሎ ዕለቱ የኹለቱ ቡድኖች ደጋፊዎች ከተማዋን በጭፈራ አደበላልቀውት ነበር። ይህም አንዳንድ ነዋሪዎችን ብጥብጥ ይፈጠር ይሆን ወይ በሚል ሥጋትን ላይ እንዲወድቁ አደርጓቸዋል። ግዛቸው አበበ የዐቢይ አስተዳደር የኅብረተሰቡን ሰላምና ደኅንነት እንዲሁም የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴውንና ሌሎችን የታዩ የአስተዳደር ድክመቶች መነሻነት ስፖርት ሜዳዎች በስርዓት አልበኝነት እየታወኩ ነው ሲሉ ይተቻሉ።

የሕዝብ እና የቁሳቁስ እንቅስቃሴን ለመገደብ መንገዶች ይዘጋሉ፣ ሕዝብ በመቶ ሺዎች ተፈናቅሎ ለወራት ለሥቃይ ይዳረጋል፣ በየቦታው ኬላ በሠሩ ሕገወጦች አማካኝነት ጭነት ይዘረፋል፣ በየቦታው መንገድ በሚዘጉ ወንበዴወች ከባድ መኪኖች ከነጭነታቸው ታግተው ማስለቀቂያ ገንዘብ በመቶ ሺዎች ይጠየቃል-ይከፈላል፣ አዲስ አበባንና መቀሌን ጨምሮ በከተሞች ውስጥ በሚካሐየዱ ውንብድናዎች ሰው በጠራራ ጸሐይ ሳይቀር ከቤቱ ወጥቶ በሰላም መመለስ እየተሳነው ነው።
የአገሪቱ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴ በዘመነ ኢሕአዴግ/ሕወሓት ባለ ጸጎችና በደላሎች ሴራ ተሸመድምዶ አብዛኛው ሕዝብ በኑሮ ክብደት እየደቆሰው ነው። ዳቦ ተወዶ፣ የጤፍ ዋጋ ተመንድጎ፣ አትክልትና ፍራፍሬም የባለጸጎች ምግብ ሆነው፣ የእህልና ጥራጥሬ ዋጋ ሰማይ ደርሶ ወዘተ…. የመንግስታችን ባለሥልጣናት ሕዝቡ ረከስ ያለ ነገር እየመረጠ ይብላ እያሉ እየቀለዱብን ነው።

ቲም ዐብይ ቤተ መንግሥቱን ለጎብኚዎች ለመክፈት ከፍተኛ ገንዘብ እያፈሰሰ፣ ለቀጣዮቹ መቶ ዓመታት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መታሰቢያ የሚሆን ሐውልት እየሠራ መሆኑን ‘አትጠራጠሩ’ እያለ እየነገረን ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አካፋ ይዘው ቆሻሻ ሲጠርጉና ዶማ ይዘው ችግኝ ሲተክሉ እያየን ነው። ሕዝቡ ዐቢይ የብሔረሰቦች ቀን እና የባንዲራ ቀን እየተባለ ሲቀለድ የነበረውን ዓይነት ሥራ ትተው፣ ዶማውንና አካፋውን ለሚመለከታው ክፍሎች አስረክበው አገሪቱን መምራት ይጀምሩ ዘንድ እየወተወተ ነው።

ዓመቱን ሙሉ እየፈሰሰ የማያልቅ የውሃ ምንጭ ባይኖራትም፣ አዲስ አበባ መዝናኛ የሚሆን ወንዝ ‘ይሰራላታል’ እየተባለ ነው፣ ሙዚየምና የቴአትር አዳራሽ ሊጨመርላት ነው፣ ዓረቦች ለአዲስ አበባ ዘመናዊ ክፍል ከተማ ሊሠሩላት ነው። በሌላ በኩል በአዲስ አበባ እና በዙሪዋ ድሆች የመኖር ዋስትና እንዳያጡ ሥጋት አለ። ክልልን ማጽዳት የሚመስል ዘር ተኮር የማፍለስ ዘመቻ እያንዣበበ ነው።

ዩንቨርሲቲዎች በዘር ጥላቻ ከመናቆር አልፈው ወደ ዘር ተኮር ግድያ እያመሩ ነው። ልጆቻውን ወደ ዩንቨርሲቲ የላኩ ቤተሰቦች ምሩቅ ልጃቸውን ሲናፍቁ አስከሬን ተቀብለዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ የታከለ ዑማ ቡድን በታሪካዊ ቦታዎች ላይ ጆፌውን ጥሏል። የታከለ ቡድን በታሪካዊ ቦታዎች ላይ ሲያንዣብብ ታየ የሚል ወሬ ሲሰማ ማስተባበያወች ይዥጎደጎዳሉ። የፈረሱና የሌላወን ውበትና ስፋት በመጠበቅ ሰበብ ኅልውናቸው አደጋ ላይ የወደቁ ቅርሶች መኖራቸው ግን የማይታበል ሃቅ ነው።
ይህን መሰሉ ሰላምንና ደኅንነትን የነፈገ ዝርክርክነት፣ ይህን የመሰለ የኢትዮጵያውያንን የኑሮ ዋስትና ችላ ያለ ፌዘኝነት፣ ይህን የመሰለ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ዒላማ ደረገ አካሔድ ከፖለቲው ዓለም አልፎ በስፖርቱ ዓለምም እየታየ ነው። የስፖርት ውድድሮች በተለይም በኢትዮጵያ ፕሪምየም ሊግ ግጥሚያወች የሕይወትና አካል ግብር የሚጠይቁ የጦርነት አውድማወች እየሆኑ ነው። የዐቢይ አሕመድ አስተዳደር ችላ ባይነትና ዓቅመ ቢስነት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን በኩል እየታየ ነው። የስቴዲዮም ውስጥ ውንብድና ለአንዱ መብት ለሌላው የሚስያቀጣ ወንጀል ሆኖ በተደጋጋሚ ይታያል። የፌዴሬሽኑ ቁንጮ ሰው ሳይቀር በታደመበት ስቴዲዮም የተፈጸመ ጋጠ ወጥነት ያለ ቅጣት ሲታለፍ ታይቷል። ጨዋታውንና ጨዋታ የሚካሔድበትን የሜዳ ድባብ በመመልከት ስፖርታዊ ጨዋነት መስፈኑንና የስፖርቱ ሕግጋት መከበራቸውን ይከታተሉ ዘንድ ኀላፊነት ተጥሎባቸው የተሰየሙ ኮሚሽነሮችና ዳኞች ዐይኔን ግንባር ያድርገው ብለው ስህተቶችንና ሕገወጥ ተግባራትን የፈጸሙ ቡድኖችና ደጋፊወች እንዳይቀጡ የሚያደርግ የአድልኦ ሥራ ሰርተዋል። በተቃራኒው ያ በዝምታ የታለፈ ወንጀል ሌላ ወንጀል ሊስከትል ይችላል በሚል ጥርጣሬ የተበደሉት ቡድኖች ከሜዳቸው ውጭ እና ደጋፊዎቻቸው በሌሉበት እንዲጫወቱ ለማስገደድ አሳፋሪ ሕሊና ቢስነት የሞላበት ብይን እየተሰጠ ነው። ይህ ደግሞ ተበደልኩ የሚሉ ወገኖች በራሳቸው መንገድ የስፖርት ሜዳ ፍትሕን ለማግኘት እንዲነሳሱ እያደረገ ነው። ባለፉት ኹለት ወራት በኢትዮጵያ ቡና እና በመቀሌ ቡድኖች መካከል የተፈጠረው ውዝግብ ከዚህ የመነጨ ነው። ይህ አጋጣሚ የኢትዮጵያ እግር ኳሰ ፌዴሬሽን ኀላፊዎች ኀላፊነት የጎደላቸው፣ ሕግን ለማስከበር ብቃቱና ፍላጎቱ የሌላቸው መሆናቸውን ያጋለጠ ነው።

ለመሆኑ የመቀሌ ከተማ ቡድን ደጋፊዎች በየትኛውም ከተማ ሲገኙ ‘ፑሽ-አፕ’ የሚሠሩት ለምንድን ነው? ይህ ‘ፑሽ-አፕ’ የመቀሌ ከተማ ደጋፊዎች ጅማ እና አዲስ አበባ ሲገኙ በቃላት ታጅቦ መካሔዱስ ምን ለማለት ተፈልጎ ነው? ይህ ‘ፑሽ-አፕ’ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ለማቃለል ሆነ ተብሎ የሚደረግ ነው የሚል ጭምጭታ ቢኖርም የመቀሌ ከተማ የደጋፊዎች ማኅበር አመራሮች ራስን ለማነቃቃት ተብሎ የሚደረግ ስፖርት ነው እያሉ ሽፋን ሲሰጡ ይደመጣሉ። ነገሩን ማስቆም ሲገባቸው የጋባዥ ከተሞች ስፖርት ታዳሚ ሕዝቦችን ለጠብና ለቁጣ እያነሳሱ ነው። የመቀሌ ከተማ ደጋፊዎች ‘እኔ ወያኔ ነኝ፣ እኔ ጌታቸው አሰፋ ነኝ’ ማለት መብታቸው ቢሆንም ይህን ቀረርቶ በስቴዲዮሞች ውስጥ፣ የሕወሓትና የጌታቸው አሰፋ በደል ያቆሰላቸው ሰዎች ባሉበት የስፖርት ማዘውተሪያ በተደጋጋሚ ሲያስተጋቡ የእግር ኳስ የፌዴሬሽኑ እና የመቀሌ ከተማ የደጋፊዎች ማኅበር አመራሮች ዝም ማለት ለምን ይሆን?

የስቴድዮም ግጭቶች የተለመደ ቢሆኑም የመቀሌው የከፋ እና ሃይ ባይ ያታ እየሆነ ነው። ደደቢት መቀሌ ላይ ስጫወት የመቀሌ ከተማ ደጋፊወች ስቴዲዮም ተገኝተው ጥቃት ይፈጽማሉ። በመቀሌ ከተማ ፋንታ ደደቢቶች ይቀጣሉ። በኢሳያስ ጅራ ደካማነት መቀሌወች ሕግና ደንብ የረሳቸው ሆነዋል። ድሮ ድሮ አባ ዱላ ገመዳን መለስ እንደሚዘውረው ሁሉ ዛሬ ኢሳስ ጅራ በደደቢቱ ሰው በመዘወር ላይ ያለ ይመስላል።

በዕለተ ማሰኞ፣ ሰኔ 11/2011 ዓም በአዲስ አበባ ስቴዲዮም የጠቅላይ ሚ/ሩ እና የጌታው አሰፋ ስሞች በለበጣ እና በሙገሳ መነሳሳታቸው በፌዴሬሽኑና በመቀሌ ከተማ የደጋፊወች ተጠሪወች ብሎም አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ የኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያወች ውስጥ ተሰግስገው የዲጂታል ወያኔነትን ተልዕኮ የሚያራምዱ የስፖርት ዲጄወች ‘እኔ ወያኔ ነኝ ማለት፣ እኔ ለመብቴ እቆማለሁ ማለት ነው’ ወዘተ… እያሉ ሲሰነዝሯቸው የነበሩት ማስተባበያወችንና መሸፋፈኛወችን ሁሉ ከንቱ አድርገዋቸዋል።

የዐብይ አሕመድ መንግስት ትግራይ ሄዶ ወንጀለኛን መያዝም ሆነ ወንጀልን ማስቆም እንደማይችል በተግባር ተረጋግጧል። እነ ድብረጽዮን በታጣቂወቻቸው ሆነ በዲጂታል ወያኔወቻቸው አማካኝነት በራያ፣ በእንደርታ፣ በተንቤን፣ በወልቃይት ወጣቶችና ነዋሪወች ላይ የሚያደርሱትን አፈና እና ጥቃት የዐብይ አሕመድ መንግስት ሊከላከልላቸው ቀርቶ ሊቃወምላቸው አልቻለም። እንዲያውም ወሬው ያልደረሰውና ምንም ነገር ያልሰማ መስሎ እያለፈው ነው። ታዲያ ወደ ትግራይ በተለይም ወደ መቀሌ ለስፖርት ውድድሮች የሚሄዱ ተጫዋቾችና ደጋፊወች ጭፍጨፋ ሊባል የሚችል ጥቃት ቢቃጣባቸው የሚከላከልላቸው ማን ነው? ጥቃት ቢደርስባቸውስ አጥቂወቻቸውን ለፍርድ የሚያቀርብላቸው ማን ነው?

ግዛቸው አበበ መምህር ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here