የሞጣ ከተማ መንገዶች ጥራት ጥያቄ አስነሳ

0
372
  • የውሃ ፍሳሽ ማስወገጃዎቹ ተሠርተው ሳያልቁ እንደሚፈርሱ የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል

በምሥራቅ ጎጃም ውስጥ የሞጣ ከተማ ነዋሪዎች በ60 ሚሊዮን ብር በከተማው ውስጥ እየተገነቡ የሚገኙ መሰረተ ልማቶች ከጥራት በታች መሆናቸውን እና በተወሰኑ የከተማው አካባቢዎች አገልግሎት ሳይሰጡ ለብልሽት የተዳረጉ መንገዶች መኖራቸውን አስታውቀዋል።

በክልሉ መንግሥት እና በከተማ አስተዳደሩ ከዓለም ባንክ በተገኘ 59 ሚሊዮን 646 ሺሕ 480 ብር ተመድቦ እየተሠራ ያለው የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገድ የጥራት ችግር እንዳለበት፤ እንዲሁም ደግሞ በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ የውሀ ፍሳሽ ማስወገጃዎች ለረጅም ጊዜ አገልግሎት እንዲሰጡ ታስበው የተሰሩ ባለመሆናቸው ተሰርተው ሳይጠናቀቁ እንደሚፈርሱም የከተማዋ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በጉዳዩ ዙሪያ አዲስ ማለዳ ጥያቄ ያነሳችላቸው የሞጣ ከተማ አስተዳደር ቤቶች ልማት ኮንስትራክሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሰፊነው ወንድም፥ በአንዳንድ የከተማው አካባቢዎች አገልግሎት ሳይሰጡ ለብልሽት የተዳረጉ መንገዶች መኖራቸውን አምነው ለዚህ ደግሞ ልምድ የሌላቸው አዳዲስ ማኅበራት ወደ ሥራ እንዲገቡ መደረጉ፣ የከተማዋ መሬት ጥቁር አፈር የሚበዛው ዋልካማ መሆኑ እና መንገዱ ማስተናገድ ከሚችለው ክብደት በላይ ከባድ ተሽከርካሪዎች እንዲጓዙበት መደረጉ በምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው ብለዋል።

እንደሰፊነው ገለጻ፣ ከእነዚህ ግንባታዎች ጋር ተያይዞ በበጀት ዓመቱ ብቻ 2 ሺሕ 38 የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ይሁን እንጂ አዳዲሶቹን ጨምሮ ከዚህ በፊት በመንገድ ሥራው የተሳተፉ አንዳንድ ማኅበራት በኀላፊነት ስሜት በጥራት ሥራቸውን ባለማከናወናቸው የመንገዱ ጥራት ተጓድሏል። ስለዚህ ጥራት ያለው ሥራ እንዲሠራ የኢንተርፕራይዞችን አቅም ማጎልበት እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

የከተማዋ ነዋሪዎች ለከተማ አስተዳደሩ ባቀረቡት ቅሬታ እንዳሉት፣ ከተማ አስተዳደሩ የማኅበረሰቡን የልማት ጥያቄ ለመፍታት እያከናወናቸው ያሉ የመንገድ እና መሠል የመሠረተ ልማት ሥራዎች የሚበረታቱ ቢሆንም፣ ነገር ግን በርካታ ገንዘብ ወጥቶባቸው እየተሠሩ ያሉት የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ መንገዶች የጥራት ችግር እንደሚታይባቸው አስተያየት ሰጥተዋል።

የአማራ ክልል ቴክኒክ ሙያና ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮ ምክትል ቢሮ ኀላፊ ተፈሪ ታደሰ በበኩላቸው፣ ኢንተርፕራይዞች በሥራ ላይ እያሉ የሥራ ጥራት ቢያጓድሉ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው የሚያሠራቸው አካል ነው ሲሉ፣ የአሰሪውም አካል ተጠያቂነት ሊኖር እንደሚገባ ሰኔ 8/2011 ከሕዝቡ ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ መግለጻቸው ተዘግቧል። ሆኖም ኢንተርፕራይዞች አባካኝ ከሆኑ ወይም የሥነ ምግባር ችግር ካለባቸው ደግሞ ቴክኒክና ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት ቢሮው እስከ ታችኛው መዋቅሩ ኀላፊነቱን ሊወስድ እንደሚገባም አስታውቀዋል።

በከተማዋም እስከ ግንቦት ድረስ 26 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ መሠራቱን የሚናገሩት ሥራ አስኪያጁ፣ ከጠቅላላ በጀቱ ውስጥ ከ36 ሚሊዮን 860 ሺሕ ብር በላይ አገልግሎት ላይ እንደዋለ አስረድተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here