ብሔራዊ ባንክ ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት መመሪያ እያሻሻለ ነው

0
655

ከወለድ ነጻ የባንክ አገልግሎት በመደበኛው ባንክ ውስጥ በሚገኙ መስኮቶች ውስጥ ብቻ እንዲገደብ ያደረገው መመሪያ እየተሻሻለ በመሆኑ በመመስረት ላይ ለሚገኙ የወለድ ነጻ ባንኮች ሕጋዊ መሰረት ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ታወቀ። ዘምዘም ባንክ ከዓመታት በፊት ወደ ሥራ ለመግባት ሲሞክር በብሔራዊ ባንክ የወጣው ከልካይ መመሪያ ከመሻር ይልቅ ባለበት የማሻሻል ሥራዎች እየተሠሩ ነውም ተብሏል።

የሕጉ መሻሻል በመንግሥት ላይ እምነት በመጣል በመደራጀት ላይ ላሉት ባንኮች አስተማማኝ ምህዳር እንደሚፈጥር የዘርፉ ባለድርሻዎች በጉጉት እንደሚጠብቁትም ተናግረዋል።

ከወለድ ነፃ ባንክን በማስመልከት የሚወጡት ሕጎች ከሸሪያው ጋር የማይጋጭና የሚጣጣም መሆን ያለበት ነው ሲሉ የሒጅራ ባንክ የአደራጆች ሰብሳቢና የኤክስፕሎር ሞር አማካሪ ድርጅት ዳይሬክተር አህባቡ አብደላ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

አዲስ እየተቋቋሙ ያሉ ባንኮች ሲመጡ አሁን ያሉትን ባንኮች የመንግሥትን ስትራቴጂ ከማስፈፀም አንጻር የባንክ ተደረሽነት ከሌላቸው የታችኛው ማኅበረሰብ ጋር የመድረስ አቅም እንደሚኖረው አህባቡ ይናገራሉ።

ከወለድ ነፃ ባንክን በማስመልከት የሚወጡት ሕጎች ሙስሊሙን እንዲያካትቱ ከሸሪዓው ጋር የማይጋጭና የሚጣጣም መሆን ያለበት ቢሆንም ባንኮቹ ለሙስሊሞች ብቻ የሚቋቋሙ ግን አይደሉም ሲሉ ያስረዳሉ። ንግድ ባንክን ጨምሮ ሌሎች ዐሥር ከወለድ ነጻ አገልግሎትን የሚሰጡ ባንኮች አትራፊ እንደሆኑ ታይቷል የሚሉት አህባቡ አንዳንድ ባንኮች በአንድ መስኮት ከወለድ ነፃ አገልግሎት እየሠሩ እስከ 35 በመቶ ያተረፉ እንዳሉ ተናግረዋል።

የሚሻሻለው መመሪያ ከመስኮት አገልግሎት በተሻሻለ መልኩ ራሳቸውን ችለው እንዲቋቋሙ አሠራር እንደሚዘረጉና ሕግጋቶችንም እያወጡ እንደሆነ ታውቋል።
ሰባት የሚሆኑ እስላማዊ ባንኮችን ለማቋቋም በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እንቅስቃሴ የተጀመረ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ሦስቱ መሥራች ጉባኤ አካሒደው ወደ ምዝገባ ሒደት መሔዳቸውን ለማወቅ ተችሏል። ዘምዘም፣ ሒጅራ እና ነጃሺ ባንኮች ሥማቸውን መርጠው መሰረት ከያዙት መካከል ሲሆኑ ኩሽ እና ሁዳ የሚባሉ ባንኮችም በምሥረታ ሒደት ውስጥ መግባታቸው ታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ በመመሪያ ወደ ሥራ እንዳይገባ የተከለከለው ዘምዘም ባንክ መልሶ ለመቋቋም ባደረገው ጥረት ሼር መሸጥ መጀመሩን መግለጹ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here