ዕድሜ ጠገብ የጦር መሳሪያዎች ሲሰበሰቡ ካሳ እንዲከፈልባቸው ተጠየቀ

0
772

ዕድሜ ጠገብ የሆኑና አሁን በሥራ ላይ የማይገኙ የጦር መሳሪያዎችን መንግሥት ለቅርስነት ሲሰበስብ ለባለቤቶች ተመጣጣኝ ካሳ እንዲከፍል ተጠየቀ። ይህ የተጠየቀው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ላይ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት ባካሔደበት ወቅት ነው።

ሰኔ 10/2011 ቋሚ ኮሚቴው በጦር መሳሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ላይ ይፋዊ የሕዝብ ውይይት ባካሄደበት ወቅት እንደተገለፀው ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያን መቆጣጠር የመጀመሪያው እና ዋነኛ ዓላማው መሆኑ ተጠቁሟል። ከዚህም ጋር ተያይዞ ረጅም ዕድሜ ካገለገሉ እና አሁን በሥራ ላይ ከማይውሉ የጦር መሳሪያዎች ጋር በተያያዘ የተነሳውን የካሳ ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴው ከሕዝብ የመነጩ ሐሳቦች እንደመሆናቸው መጠን አፅንዖት ሰጥቶ እንደሚመለከታቸው የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ተስፋዬ ዳባ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ተስፋዬ ጨምረው እንደገለፁት ከተሳታፊዎች ስለሚከፈለው ካሳ እንደምክንያት የተነሳው ነገር በቤታቸው የጦር መሳሪያዎች ደብቀው ያስቀመጡ ግለሰቦች በፈቃደኝነት ለመንግሥት እንዲያስረክቡ ዓይነተኛ ማበረታቻ ይሆናል በሚል እንደቀረበ ተናግረዋል። አያይዘውም ገና ብዙ ውይይት የሚጠበቅበት በመሆኑ ጉዳዩን በሒደት ማየት እንደሚሻል ጠቅሰው የተነሳው ጉዳይ ይፀድቃል አይፀድቅም ለማለት ጊዜው ገና መሆኑንም ገልፀዋል።

በይፋዊ የሕዝብ ውይይቱ ላይ በአስረጅነት ከፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና ከፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ተወካዮች መገኘታቸውን የገለፁት ተስፋዬ፥ በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ የሚገባውን የጦር መሳሪያ መፍትሔ እንዲበጅለት ከማድረግ አንፃር አዋጁ ጠቀሜታው የጎላ እንደሚሆን መግለፃቸውን አስረድተዋል።

አዋጁ በዋናነት ያስፈለገበት ምክንያት በሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ምክንያት ሚከሰተውን የሰላም መደፍረስ ለመፍታት እንጂ ትጥቅ ለማስፈታት እንዳልሆነ ለመረዳት ተችሏል።

በዚህ ጉዳይ ከዚህ ቀደም የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በሕገ ወጥ መሳሪያ ዝውውርና ባለቤትነት ዙሪያ እስከ 10 ዓመት የሚደርስ እስር የሚጥል ሕግ ለማፀደቅ እየሠራ እንደሆነ ማስታወቁ የሚታወስ ነው። አሁን በይፋዊ የሕዝብ ውይይቱ ላይ የተገኙት የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተወካይ ቅጣቱ ከ8 -20 ዓመት እስር እንደሚደርስ ማስረዳታቸውን ተስፋዬ ዳባ ገልፀዋል።

በውይይቱ ወቅት ከሕዝብና ከባለ ድርሻ አካላት የተነሱትን አስተያየቶች ቋሚ ኮሚቴው ተቀብሎ ከመረመረ በኋላ አዋጁን በሚያፅድቅበት ወቅት በሕዝቡ ላይ ሊፈጠር ይችላል ያለውን ብዥታ ከወዲሁ ለማጥራት የግንዛቤ ማስጨበጫ እንቅስቃሴዎችን ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደሚሠራ አዲስ ማለዳ ያገኘችው መረጃ ያመላክታል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here