በፖለቲካ ጥያቄ 43 ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተና ላይ አልተቀመጡም

0
1057

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት ጉራጌ ዞን፣ የፖለቲካ ጥያቄያችን አልተመለሰልንም በሚል 43 ተማሪዎች አገር ዐቀፍ ፈተና ላይ እንዳልተቀመጡ ታወቀ።

በጉራጌ ዞን ቡታጅራ አካባቢ መሰረተ ወገራም በተባለ የፈተና ጣቢያ፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ ይሰጥ የነበረውን የዐሥረኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን በአካባቢው ከነበረው ፖለቲካዊ ጥያቄ ጋር በማገናኘት ተማሪዎች ፈተናውን እንዳልወሰዱ የአገር ዐቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ኤጀንሲው ጨምሮ እንደገለፀው በዞኑ ያጋጠመው ችግር ተማሪዎቹ በቀጥታ፣ ወይም በራሳቸው ተነሳሽነት ሳይሆን በወላጆቻቸው ግፊት መሆኑን ማረጋገጥ መቻሉን ለመረዳት ተችሏል። በጉራጌ ዞን መስቃን እና ማረቆ ወረዳዎች መካከል ያለውን እስካሁን እልባት ያላገኘውን የማንነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ፣ የተማሪዎች ወላጆች ልጆቻቸውን ፈተና ላይ እንዳይቀመጡ እንዳደረጉ የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የኤጀንሲው ሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ረዲ ሽፋ ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት፣ በአገር ዐቀፍ ደረጃ የተሰጠው የዐሥረኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በኹሉም ክልሎች በሰላም እና ያለምንም ችግር መጠናቀቁን ገልፀው፤ በተጠቀሰው ፈተና ጣቢያ ላይ ብቻ እንዲህ ዓይነት ችግር መፈጠሩን አክለዋል። በአገር ዐቀፍ ደረጃ ከሰኔ 3 እስከ 5/ 2011 ድረስ በመላው ኢትዮጵያ በተካሔደው አገር ዐቀፍ ፈተና ላይ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ተማሪዎች መቀመጣቸው ይታወቃል።

በተያያዘ ዜና አለመረጋጋት በነበረባቸው እና የመማር ማስተማር ሒደቱ ተስተጓጉሎባቸው የነበሩ የአገሪቱ አካባቢዎች ዐሥረኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናውን እንደወሰዱ ታውቋል። አዲስ ማለዳ ከዚህ ቀደም በየካቲት 30/2011 በቁጥር 17 ዕትሟ በአለመረጋጋት መማር ማስተማሩ የተስተጓጎለባቸው አካባቢዎች የማካካሻ ትምህርት ወስደው እንደሚፈተኑ እንዲሁም የፈተና መራዘም እንደማይኖር መዘገቧ ይታወሳል።

በዚህም መሰረት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የዐሥረኛ ክፍል ተማሪዎችና 3 መቶ 22 ሺሕ የዐሥራ ኹለተኛ ክፍል ተማሪዎች፣ በድምሩ ከ 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ተማሪዎች በላይ የአገር አቀፍ ፈተና ላይ እንደተቀመጡም ታውቋል። ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ፣ በሰሜን ጎንደር ዞን ጃናሞራ ወረዳ የጭሮ ለባ አንደኛ ደረጃ ተማሪዎች ፊዚክስ፣ ሒሳብና እንግሊዘኛ ትምህርቶችን ሳይማሩ የስምንተኛ ክፍልን ክልላዊ ፈተና እንዲወስዱ መደረጉ አግባብ አለመሆኑን ጠቅሰው ለአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት አስታውቀዋል። በዚህም ጉዳይ የጃናሞራ ወረዳ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ችግሩ መኖሩን አምነው፤ በጭሮ ለባ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ትምህርት ቤቶችም ላይ እንደሚያጋጥም ምላሻቸውን መስጠታቸው ታውቋል።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ አዲስ ማለዳ የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወረቁ ለምለሙን በስልክ ተጨማሪ ማብራሪያ በጠየቀችበት ወቅት፥ የተባለው ነገር በሙሉ ከእውነት የራቀ እንደሆነና የመማር ማስተማር ክፍተት ሳይፈጠር ዓመቱ እየተገባደደ ገልጸው፥ የስምንተኛ ክፍል ተፈታኞችም በቂ ዝግጅት እንዳደረጉ መረጃው እንዳላቸው አስታውቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 33 ሰኔ 15 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here