‘በሕዝብ ሥም ጫካ ገብቻለሁ’ የሚለው ቡድን እንደማይወክላቸው ነዋሪዎች ገለጹ

0
456

የኦሮሞን ሕዝብ በመወከል “ጫካ ገብቻለሁ” የሚለው ቡድን እንደማይወክላቸው በምዕራብ ኦሮሚያ የተለያዩ አካባቢ ነዋሪዎች ለተቃውሞ ሰልፍ በመውጣት ሀሳባቸውን መግለፃቸውን መገናኛ ብዙሀን ዘግበዋል።

የቄለም ወለጋ፣ የምዕራብና ምሥራቅ ወለጋ እንዲሁም ቡኖ በደሌ የተለያዩ ወረዳዎች ነዋሪዎቹ “የኦሮሞን ሕዝብ ነጻ አወጣለሁ” በማለት ጫካ የገባ ማንኛውም ቡድን እንደማይወክላቸው ሰሞኑን ባካሔዱት የተቃውሞ ሰልፉ ላይ ባሰሙት መፈክር አረጋግጠዋል።

በተለያዩ ዞኖች በተካሔዱት በእነዚህ የተቃውሞ ሰልፎች ለኦሮሞ ህዝብ ጥቅም የሚታገል በማስመሰል ዘረፋና ግድያ የሚፈጽመው ቡድን እንቅስቃሴን በመግታት መንግሥት የሕግ የበላይነትን እንዲያስጠብቅ የሰልፎቹ ተሳታፊ ወጣቶች ጠይቀዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ በሚገኙ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ማክሰኞ፣ ሰኔ 18 ባካሔዱት በዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ ቡድኑ ለወገን የሚሠራ በማስመሰል በሕዝቡ ላይ ስቃይና መከራ እያደረሰ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦነግ ሸኔ ሥምም ሰላምን ማወክና ሕዝብን ማሸበርን አጥብቀው የሚቃወሙት ድርጊት እንደሆነ ነዋሪዎቹ አጽንዖት ሰጥተውታል።
ኦነግ ባለፈው ወር በይፋ የትጥቅ ትግል እንደማያካሔድና ሠራዊትም እንደሌለው ማስታወቁ ይታወሳል። ትግሉ ሰላማዊ እንደሚሆን ይፋ አድርጓል። የኦሮሞን ሕዝብ ጥቅም ለማስጠበቅ ከሌሎች ጋር በሐሳብ ተወዳድሮ ለማሸነፍ መወሰኑን በስምምነት አረጋግጧል።

ይህም ሆኖ በኦነግ ሸኔ ሥም በሰዎች ላይ ጥቃት እየፈጸመና ንብረት እያወደመ መሆኑን ነዋሪዎቹ ገልጸዋል።

የኦሮሞን ሕዝብ ወክያለሁ በማለት ጫካ የሚገኘውን ቡድን ለመቃወም በተካሔደው በዚሁ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ነዋሪዎቹ “በኦሮሞ ሕዝብ ሥም ታጥቆ ጫካ የሚገኘው ኀይል አይወክለንም፤ በኦነግ ሥም በመታጠቅ ሰላምን ማወክና ሕዝቡን ማሸበርን እንቃወማለን” የሚሉ መፈክሮችን አሰምተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here