እስክንድር ነጋ በባሕር ዳር አየር መንገድ እንዳይበር ተከለከለ

0
542
  • ባልደረቦቹ በዓየር ሲመጡ እርሱ በመኪና ለመምጣት ተገዷል

ሰኔ 15/2011 ለስብሰባ ወደ ባሕር ዳር ያቀናው እስክንድር ነጋ በባሕር ዳር አየር መንገድ የጸጥታ ሠራተኞች መታገቱንና፣ ወደ አዲስ አበባ በአውሮፕላን መመለስ እንደማይችል ተነግሮት በመኪና ወደ አዲስ አበባ መመለሱ ታወቀ።

አብረውት የነበሩት የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት አባላት በአውሮፕላን እንዲመለሱ ቢፈቀድላቸውም፣ እስክንድር ነጋ ግን መመለስ እንደማይችል ተነግሮት፣ መኪና ተከራይቶ ሰኞ ለሊት አዲስ አበባ መግባቱን ወደ ስፍራው አብሮት ያቀናው የባለ አደራ ምክር ቤት አባል ኤልያስ ገብሩ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ቅዳሜ፣ ባሕር ዳር የደረሱት የአዲስ አበባ ባለአደራ ኮሚቴ አባላት፣ በዕለቱ በነበረው ግርግር ምክንያት አልጋ ለመያዝ ወደ አንድ ትልቅ ሆቴል ቢገቡም፣ ለእናንተ አናከራያችሁም በመባላቸው፣ ወደ ባሕር ዳር አየር መንገድ ቢመለሱም ወደ አዲስ አበባ መመለስ እንደማይችሉ ተነግሯቸው፣ ከአየር መንገዱ መውጣት እንደማይችሉ ስለተነገራቸው እዛው አየር መንገድ ማደራቸውን ያስታወቀው ኤልያስ፣ በማግስቱ ዕሁድ እስከ 8 ሰዓት ምግብ ሳይቀምሱ በዛው አየር መንገድ መቆየታቸውን አስታውቆ፣ ከ8 ሰዓት በኋላ ወደ ባሕር ዳር ከተማ እንዲመለሱና ስብሰባውን ማስቀጠል እንደሚችሉ ቢነገራቸውም፣ እስክንድር ባልተረጋጋ ሁኔታ ስብሰባውን አናደርግም የሚል ምላሽ መስጠቱን ገልጿል። ይሁን እንጂ በአውሮፕላን መመለስ እንደማይችሉ ተነግሯቸው ወደ ከተማ መመለሳቸውን አክሎ ገልጿል።

የአዲስ አበባ ባለአደራ ኮሚቴ አባል የሆነው ሄኖክ አክሊሉ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቀው፣ ከሰዓት በኋላ በባሕር ዳር አየር መንገድ መመለስ እንደማይችል የተረዳው እስክንድር የቀሩትን አባላት በባሕር ዳር ጥሎ፤ መኪና በመከራየት ወደ አዲስ አበባ ጉዞ ሲጀምር ኹለት ቦታ ፍተሻ እንደተደረገበት ተናግሯል። “ገና ከጅምሩ ከቦሌ አየር መንገድ ስንነሳ እስክንድርን ኹለት ጊዜ ጠርተው ፈትሸውታል” የሚለው ኤልያስ፣ ባሕር ዳር ሲገቡም ያልጠበቁት ነገር እንደገጠማቸው ያወሳል።

እሁድ፣ ሰኔ 16/2011 አስራ አንድ ሰዓት ገደማ ሥልክ ተደውሎላቸው በባሕር ዳር አየር መንገድ ወደ አዲስ አበባ መመለስ እንደሚችሉ የተነገራቸው ኤልያስ ገብሩ፣ ሰናይት ታደገና ከዴንማርክ የመጡት ጥሩነሽ ወደ አየር መንገዱ ደርሰው ለእስክንድር ሲደውሉለት፣ “መሔድ የምትችሉት እናንተ ብቻ ናችሁ፤ እስክንድር መሔድ አይችልም” የሚል መልስ ከአየር መንገዱ የጸጥታ አካላት ተሰጥቷቸው ወደ አዲስ አበባ ሲመጡ፣ እስክንድር በመኪና ለመምጣት መገደዱን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

አዲስ አበባ ከገቡ በኋላም የተወሰኑ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት አባላቶች ቅዳሜ፣ ሰኔ 15/ 2011 በባሕር ዳርና አዲስ አበባ ከተሞች በሰዓታት ልዩነት በአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣ እንዲሁም በአገር መከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ ተጠርጥረው ማክሰኞ ጠዋት በፌደራል ፖሊስና በአዲስ አበባ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here