ከሥልጠን ጀርባ የድብቅነት ሥነ ልቦና አባዜ

0
1448

አብዛኞቻችን የድብቅ ሥነ ልቦና ተጠቂዎች ነን የሚሉት ጌታቸው መላኩ፥ ከግለሰብና ቤተሰብ አልፎ በአገር ደረጃ ዋጋ እያስከፈለን ነው ሲሉ ከዘርፈ ብዙ የሕይወት ገጠመኞች በመጨለፍ ማሳያዎችን አነሳስተዋል፤ መፍትሔውንም ግልጽ ሥነ ልቦናን ማሳድግ ነው ሲሉም ምክረ ሐሳብ ሰንዝረዋል።

 

በትርክት ሰምተን ከፅሁፍ ሰነዶች አንብበን፣ ነገር ግን ልክ እንደኖርንበት ጊዜ የምናውቀው (ከጊዜው ቅርበት የተነሳ ይመስለኛል) የቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ አገዛዝ በተለይ ከጣሊያን ሽንፈት በኋላ በአንፃራዊ ሁኔታ የተረጋጋ ነበር። ማሳያውም ለረጅም ዓመታት የዘለቀው የአገዛዙ ሥልጣን ከሌለው አንፃር ረጅም መሆኑ ነው። ነገር ግን ንጉሱ ዓለም ሲቀየር፣ አገር ወደ ውጪ እየተመለከተ ሲለወጥ ምልክቱን እንኳን መመልከት አቅቷቸው፣ እኛ በዓለም ቢያንስ በግርማቸው የሚፈሩና የሚከበሩ ንጉሥ እንደሰማነው በወታደሮች በትራስ ታፍነው ተገደሉ። ቀዳማዊ ኀይለ ሥላሴ ከስደት መልስ አገሪቱን ለማረጋጋት የሔዱበት መንገድ እጅግ አስተዋይ ያስባላቸው ነበር።

አገሪቱ ከ1933 በኋላ በአርበኛ፣ በስደተኛና በባንዳ ተከፋፍላ ለዘላቂ የሥልጣን መደላድሉ አስጊ ጊዜ ላይ ነበረች። እንግሊዞቹ ሳይቀሩ ለራሳቸውም ይሁን ለሌላ ምክንያት ራስ አበበ አረጋይን የመሰሉ አርበኞችን ሥልጣን እንዲዙ ቢያበረታቱም ይህንን ጊዜ ለማለፍ ንጉሡ ያለፉበት መንገድ አስገራሚ ቢሆንም ይህ ብልሃታቸው በተለይ አስተዋነታቸው በስተርጅና የት ገባ የሚሉም አሉ። ድብቅ አባዜ ይሆን ይሆን?

የደርግ ወታደራዊ ስብስብ አብዮቱን ጠልፎ ወደ ሥልጣን ከመጣ በኋላ የኢትዮጵያን የተማሪዎችና የሌሎች አብዮተኞችን ትግል መስመር አሳተው። በኹለት አዋጆች/ደንቦች መሬትን ላረሹ እንዲሁም “ትርፍ” የከተማ ቤትና መሬት ለመንግሥት ብሎ አብዮተኛውን በእጅጉ ጥያቄና ምክንያት አሳጣው። ይባስ ብሎ ዴሞክራሲያዊ መብትን ለመደፍጠጥ መሞከሩ የፈጠረው በተለይ በኅቡዕ ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር የፈጠረው መላተም ብዙዎች ሕይወታቸውን የገበሩበትን ክፉ አጋጣሚ ፈጠረ። አሁንም በደርግ ወታደራዊ ቡድንም ይሁን በኅቡዕ በሚንቀሳቀሱት አካላት ውስጥ የራሳቸውም ሆነ ኢትዮጵያዊ የሆነ የድብቅነት ሥነ ልቦና ተጠቂዎች ያደረጋቸው ስሪት እንዳለ ይሰማኛል። በተጨማሪም የአሸናፊና ተሸናፊው ስልቦና አሁንም ድረስ እያማሰነን ይገኛል።

ኢሕአዴግና ሻዕቢያ ለዓመታት የዘለቀ “ከቀኝ ገዢ” ስርዓት የመላቀቅና የራስን ክልል “ነፃ የማውጣት” ጦርነት እንዲሁ በድብቅነት ሥነ ልቦና በተጠናወተው ምክንያት ተሸፍነው ባደረጉት ተጋድሎ አንዷ አገር ኹለት ሆነች። ለዘመናት በድብቅ አጀንዳ ተታሎ ነፃ የመውጣት እንቅስቃሴውን የደገፈው ኅብረተሰብም የሌላ ዙር “ቀኝ ገዢ” ሰለባ ሆኗል ብለው የሚከራከሩ ብዙኀን ናቸው። የማይታበለው ሀቅ ግን ብዙዎች የስኳር ነገር አልሆን ብሏቸው የድብቅ ነፃ አውጪነት ካባቸው እስኪገለጥ ድረስ ሞሰኑ፣ ነቀዙ፣ ተበላሹ ድመት ብትመነኩስም አስተረተባቸው። ይህም የድብቅ ሥነ ልቦናቸው መገለጫ ሆኖ ወጣ። ከኢሕአዴግ ውስጥ ጊዜው ዕድል የፈጠረላቸው ከውስጥ ገፍተው ሥልጣን ሲይዙ ከውጪ የነበረውን ግፊት በመመልከት የጠለፋ ያህል የጥያቄው ወራሽ ሆነው ብቅ ያሉት እነዚህ አካላት የድብቅ ሥነ ልቦናው ችግር ተጠቂ ይሁኑ አይሁኑ ጊዜ የሚፈታው ጉዳይ ነው።

የሚገርመው ነገር ይህ የድብቅነት ሥነ ልቦና ችግር በመንግሥትነት ባሕርይ ሁሉንም ሲጎዳ ጎልቶ ይታይ እንጂ አጋጣሚዎች እያሳየን ያሉት ይህ የድብቅነት ሥነ ልቦና በግለሰብ፣ በቤተሰብ፣ በድርጅትና በማኅበረሰብ ደረጃ የሚንፀባረቅ ችግር መሆኑን ነው። ከጓደኝነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ ከትዳርና ቤተሰብ ምሥረታ ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ ከድርጅት ባልደረብነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ ከማኅበረሰብ አባልነት እንዲሁም ወኪልነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና። ከአነቃቂ ንግግር አቅራቢነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ ከሥራ ፈጠራ ስኬት ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ ከበጎ አድራጎት ተግባር ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ ከፓርቲ አባልነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና። የድብቅ ሥነ ልቦናው ዝርዝር በየፈርጁ ማለቂያ ሳይኖረው ሊቀጥል ይችላል። ከተቃዋሚነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ ከደጋፊነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ ከፓርቲ መሪነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ ከአገር መሪነት ጀርባ ሌላ ድብቅ ሥነ ልቦና ዝርዝሩ ያደክማል።

ለዚህ ጉዳዬ አስረጅ እንዲሆነኝ እስቲ እንድ ምሳሌ ላንሳ። የሰሞኑ የኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን (ኢሳት) ጉዳይ እጅግ የሚገርም ነው። በየማኅበራዊ ሚዲው የሚገልፀውና የሚሰራጨው መልዕክት፣ ኢሳት ባልደረቦቹን በአመለካከታቸው ምክንያት የማግለል ሥራ እየሠራ እንደሆነ ሲሆን፤ ድርጅቱ ያወጣው ግልፅነት የጎደለው መግለጫ (ለዓላማ እንደሆነ በድንብ ስለሚያስታውቅ ኢሳቶች ቢያስቡበት መልካም ነው) ደግሞ የሚያትተው የለውጥ ሒደት እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ ነው።
ኢሳት በአገሪቱ ለመጣው ለውጥ እንደ ብዙኀን መገናኛ ጣቢያ ዋነኛ ድርሻ እንዳለው የማይታበል ነው። ብዙዎች ግን ሙያዊ ሥነ ምግባርን በተለመከተ በኢሳት ላይ ጥያቄ አላቸው። በጊዜው ኢሳት የነፃ አውጪ ዓይነት እንቅስቃሴ በስሜት ያደርግ ስለነበር ይመስለኛል። የዚህ ዓይነቱ የብዙኀን መገናኛ ሥነ ምግባር የማይደገፈው በምክያትና በማስረጃ ከሚያምን ተከታይ ይልቅ ስሜቱን የሚከተል ተከታታይ መፍጠሩ ነው። የሚገርመው ይህ ተከታታይ ሁኔታዎች የተቀየሩ ዕለት በራሱ በጣቢያው ላይ መነሳቱ የማይቀር ነበር፣ እንሆ ሆነ።

የለውጡን መምጣት ተከትሎ በኢሳት ውስጥ በተለይ በተፅዕኖ ፈጣሪነታቸው የሚታወቁት ግለሰቦች የለውጡ ግልፅ ደጋፊ ሆነው መምጣታቸው ባያስገርምም፣ በኢሳት ውስጥ ለሐሳብ ልዩነት የሚሰጠው ቦታና ግምት እንደተወራውና እንደተዘመረው እንዳልነበር የሚያሳዩ ነገሮች ከለውጡ መምጣት ማግስት ጀምሮ መከሰት ጀምረው ነበር። ይህም አብዛኛውን ተመልካችና አድማጭ አሁን ከአንድ ዋንጫ መጠጣት ሊቀር ነው፤ የሐሳብ ፍትጊያ የሚያመጣውን ልዕልና ልናይ ነው፤ ያለው አድማጭ ተመልካች በርካታ ነበር። በእርግጥ በኢሳት ላይ የነበረውን የቆየ የብዙኀን መገናኛ ጣቢያነት ሚናን ያኮሰሱና የነፃ አውጪ ግንባርነት ሚናን ያላበሱ የቀን ተቀን አሰራሮች በብዙዎች ዘንድ አልተዘነጉም። እንዲሻሻሉ ለማገዝ ያሰበና መሳተፍ የቆረጠ ሰው ቢያንስ በእኔ ዙሪያ እንደነበር አውቃለሁ።

ነገር ግን አሁን ሁኔታዎች የሚያሳዩት እንደ ሌላው ሁሉ ኢሳትም የድብቅ ሥነ ልቦና ችግር ተጠቂ የሆነ ጣቢያ መሆኑን ነው። በእርግጥ ከአገራቸው ተሰደው የነበሩ ግለሰቦች ወደ አገራቸው የመመለስ ዕድል ማግኘታቸው አስደሳች ነው፣ ለእነሱም፣ ለቤተሰባቸውም እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዳቸው። ከጥቂት ቀናት በፊት ታማኝ በየነን አንድ ሆቴል ውስጥ በአካል ስመለከተው እኔንም ለየት ያለ ስሜት እንደተሰማኝ ልደብቅ አልፈልግም። ከአገር ከወገን በተለይ የመለየት ስሜቱ ለኢትዮጵያዊ ካልደረሰብት በቀር ለመረዳት ስለሚከብድ ባልፈርድም ለማስረዳት ግን ከባድ ጉዳይ የሚሆንብኝ ይመስለኛል። ለጥቂት ዓመታት ለትምሀርት እንኳን አገርን ሲለዩ የሚሰማው ስሜት ባያስቸግረኝም ጎሻሽሞኛል። ነገር ግን የኢሳት ባልደረቦች በተለይ “ተፅዕኖ ፈጣሪ” ሰዎች ድብቅ ዓላማ ወደ አገር ቤት የመግቢያ ዕድል ለማግኝት ወይስ እውነተኛ የሰላምና የዴሞክራሲ ስርዓት ለመገንባት የሚደረግ ጥረት ድጋፍ።

የድብቅ ሥነ ልቦና መነሻው ምንም ይሁን ምን ችግሩ ግን ግለፅ ነው። በመጀመሪያ ግለሰቦች ባለባቸው የድብቅነት ሥነ ልቦና ምክንያት የረጋና የተመቻቸ ሕይወት እንዲሁም ውጤታማነት ሲርቃቸው፤ በአንድ አጋጣሚ የሠሩትን መልካም ሥራ በሌላ ጊዜ በተቃራኒው እያጠፉ የመኖር አባዜ ውስጥ ይከታቸዋል። ድርጅቶችም እንደዚሁ ብዙ ድብቅ ሥነ ልቦና ባላቸው ግለሰቦች ተወጥረው የአመፃና የተንኮል አውድማ ሲሆኑ፣ የማደግና የመለወጥ ዕድላቸው መክኖ ለሌሎች ውድቅና ክሽፈት ምክንያትም ሲሆኑ ይስተዋላል። ድብቅ ሥነ ልቦና በአገር ደረጃ ያስከፈለንን ዋጋ ስንመለከተው ከበሽታነቱ አልፎ ሞተን ወደ መቃብር ካልወረድን የማይተወን ክፉ ደዌ እንደሆነብን የተረዳን አይመስለኝም።

በተለይ የወላጅ፣ የአስተዳዳሪ፣ የአመራርና የእናትነት/የአባትነት ኀላፊነት ያለባቸው ሰዎች የድብቅነት ሥነ ልቦናው ችግር ተጠቂነት እየጨመረ መምጣቱ ወላጅ አልባ፣ አስተዳደሪ የማይበረክትለት፣ መሪ ያጣ፣ እጓለማውታን አድርጎን እነሆ ለዘመናት ዘለቀ። ለመፍትሄው ማን ምን ያስብ ሆን? የድብቅነት ሥነ ልቦና በእኛ አገር በሰፊው መገለጫ የሆነው “የጠላቴ ጠላት ለእኔ ወዳጄ ነው” በመሆኑም፤ ጠላቱ የጠፋ ዕለት ወዳጅነትን የሚያዘልቅ ዓላማም ይሁን ተነሳሽነት ሲጠፋ ይስተዋላል። “እውቀት የጎደለው ይጎዳል አስተወሎት የጎደለው ደግሞ እጅግ ይጎዳል” ነውና በጠላቴ ጠላት ዓላማ መስተጋብር የፈጠረ ሁሉ ጠላቱ ሲጠፋ ወይም ሲዳከም አስተውሎ የጎደለው ስለሆነ ከጠላቱ በላይ መበታተኑ መድከሙና መውደቁ ያስገርማል። ድብቅ ሥነ ልቦናና አባዜው ማለት ይህ ነው።

ከሙያና ከመሥሪያ ቤት ምርጫ ጀርባ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ የፖለቲካ ፓርቲ ከማደረጃት ጀርባ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ የብዙኀን መገናኛ ድርጅት ከማደራጀት ጀርባ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ የበጎ ድራጎት ድርጅት ከማቋቋም ጀርባ ድብቅ ሥነ ልቦና፣ ከሰፈር ልማት አስተባበሪነት ጀርባ ድብቅ ሥነ ልቦና እንዲሁም ሲብስ ጓደኝነት ከመመስረት ጀርባ ድብቅ ሥነ ልቦና ወዘተ… ኢትዮጵያዊነታችንን አውርደውታል።

መድረሻችን የት ይሆን?
ድብቅ ሥነ ልቦና የግልፅ ሥነ ልቦና ተቃራኒ ነው። በግልፅ ሥነ ልቦና ሰዎች የምንሻውን እንመኛለን። እርሱን ለማግኘት እንጥራለን። ሌሎች ፍላጎታችንንና ጥረታችንን ተመልክተው ሊረዱን ባይችሉ እንኳን መንገዳችን ላይ በመቆም ደንቃራ ከመሆን ይታቀባሉ። በዚህ የቀጠለና ያደገ የግልፅነት ሥነ ልቦና ግንዛቤ ባይኖ መማርን፣ ቢሳሳቱ ማረምን፣ ቢበድሉ ይቅርታ መጠየቅን ስለሚያስተምርና በውስጣችን ስለሚያዳብር መለወጥ እንችላለን። በመሆኑም ግለሰባዊ ዕድላችን፣ እንደአገር ፅዋ ተርታችን በተጠናወተን የድብቅ የሥነ ልቦና ችግር እንዲቀረፍ ብንተጋ። ግላዊ አስተሳሰብና አመለካከት ክቡር ሆኖ ሳለ ለድብቅ ሥነ ልቦና የሚዳርገንን ችግር በትውልድ ላይ ብንሠራ።

ጌታቸው መላኩ የሚዲያና ተግባቦት አማካሪ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው
getachewmelaku@gmail.com ላይ ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here