“በሬ ካራጁ. . .”

0
551

ቅዳሜ፣ ሰኔ 15 አመሻሽ ላይ የማኅበራዊ ትስስር አውታሮች ላይ በሰፊው የመወያያ ርዕስ ሆኖ የወጣው ከፍተኛ የአማራ ክልል መንግሥት ባለሥልጣናት እርግጠኛ ባልሆነ ሁኔታ በጥይት ተመተው መቁሰላቸውን በተመለከተ ሲሆን አንዳንዶቹም የሰዎቹን ፎቶዎች በማስደገፍ ጭምር ወሬውን አራግበውታል። ሌሎች በበኩላቸው እከሌና እከሌ ላይ አንድ እርምጃ ከተወሰደባቸው እንደሚበቀሉ ሲያስጠነቅቁና ሲዝቱ ነበር።

ከምሽቱ አንድ ሰዓት ተኩል አካባቢ በሰፊው ሲናፈስ የነበረውን ወሬ በሚያረጋግጥ ነገር ግን የበለጠ ግርታን በሚፈጥር መልኩ የጠቅላይ ሚኒስትር ፕሬስ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ንጉሱ ጥላሁን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው በአማራ ክልል መፈንቅለ መንግሥት መካሔዱን ገለፁ፤ ነገር ግን መክሸፉንም አስታወቁ። በክልል ደረጃ መፈንቅለ መንግሥት ተካሒዷል መባሉ ብዙዎችን አነጋግሯል፤ ግርታም ፈጥሯል። አንዱ የግርታው ምክንያት መፈንቅለ መንግሥት ከአገር ጋር እንጂ እምብዛም ከክልል መንግሥታት ጋር ተያይዞ ባለመሰማቱ ነው።

ሌላው የዚሁ ቀን አመሻሽ ወሬ የነበረው የጦር ኀይሎች ኤታ ማዦር ሹም ሰዓረ መኮንን በጥይት ተመቱ የሚለው ወሬ ሲሆን ብዙዎችን አስደንግጧል፤ አሸብሯል፤ አደናግሯል። የሚያረጋግጥ ወይም የሚያስተባብል ባለመኖሩ ደግሞ የባሰ ፍርሃትንና ያለመረጋጋት ሥጋትን በበርካቶች ዘንድ አሳድሯል።

ከምሽቱ አራት ሰዓት ገደማ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ በማኅበራዊ ትስስር አውታሮች ይሰራጩ የነበሩ እውነተኛም ሆኑ በሬ ወለደ ወሬዎች ሥርጭት ተገታ። በዚህም ምክንያት የመረጃ ወይም ወሬ ድርቀት አጋጠመ። እኩለ ሌሊት እየተቃረበ ባለበት ሰዓት ጠቅላይ ሚኒስርት ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሙሉ ወታደራዊ ልብስና ከበድበድ ባለ የፊት ገጽታ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለው በአማራ ክልል የተካሔደው መፈንቅለ መንግሥት መክሸፉን አስታውቀው ከመፈንቅለ መንግሥቱ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ኤታ ማዥር ሹሙ ላይ ጥቃት መፈጸሙን አረጋገጡ። ያጋጠመው ድንገተኛ አደጋ ለተጀመረው ለውጥ ከባድ ሥጋትን ቢደቅንም ለውጡ ግን እንደማይቀለበስ ያላቸውን እምነት በልበ ሙሉነት ገልጸዋል፤ የሕዝቡን የአብሮነት ድጋፍም ጠይቀዋል።

ረቡዕ፣ ሰኔ 19 ሦስቱ የአማራ ክልል ባለሥልጣናት ባሕር ዳር እንዲሁም ኹለቱ ጀነራል መኮንኖቹ ደግሞ መቐለ በከፍተኛ መንግሥታዊ የቀብር ሥነ ስርዓት ተፈጽሟል።

ከግድያዎቹ ጋር በተያያዘ በተለይ ጀነራል ሰዓረንና ጀነራል ገዛኢን የገደለው ወታደር ራሱን እንዳጠፋ ፖሊስ ኮሚሽነሩ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የተናገሩ ቢሆንም አፍታም ሳይቆይ ተጠርጣሪው በከባድ ሁኔታ ቆስሎ በሆስፒታል ጽኑ ሕሙማን ክፍል የሕክምና እርዳታ እየተደረገለት መሆኑ መነገሩ በአንድ ራስ ኹለት ምላስ ሆኖ ሰንብቷል፤ እስካሁንም ተጠርጣሪውን በተመለከተ ጥርት ያለ ምላሽ አልተገኘም። ይህም ሕዝቡም የትኛውን መረጃ እንደሚያምን ግራ እንዲጋባ አድርጓል። የሆነው ሆኖ አንዳንዶች ይህ በመንግሥት አካላት መካከል የተፈጠረው የመረጃ መሳከር ከመናበብ ችግር ወይስ በሌላ ፖለቲካዊ ሴራ ሲሉ ጥያቄ ያነሳሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here