የሰኔ ሰላሳ ትዝታዎች

0
740

ሰኔ ሰለሳ ተማሪው ውጤቱን በሰርተፊኬት ማረጋገጫ የሚቀበልበትና የቀጣዩን ክፍል ዕጣ ፈንታ የሚያውቅበት በመሆኑ ጎበዞቹ በጉጉት ይጠብቁታል። በትምህርታቸው ደከም የሚሉት ደግሞ በታላቅ ፍርሃትና ሥጋት ቀኑ ላይ ይደርሳሉ። ከዚህ ባሻገር ግን ሰኔ ሰላሳን ለተለየ ውሎ የሚጠቀሙበት ተማሪዎች ጥቂቶች አልነበሩም። በየክፍሉ ውጤት ተሰጥቶ ከተጠናቀቀ በኋላ እንደተለመደው ከትግል ሜዳው ወርደው በይዋጣልን ፍልሚያ ራሳቸውን የሚያጀግኑ በርካቶች ነበሩ። የድብድቡን አጀብ ዙሪያውን ከበውና በቡድን ተሰባስበው ተደባዳቢዎቹን የሚያበረታቱና እሳቱን የሚያባብሱም ጥቂት አይደሉም። የዛን ዕለት ሁሉም እንደ ነጻ ትግል ከዳር ሆነው እየጮሁና እያዋከቡ ተፋላሚዎቹን ለጠብ ይጋብዛሉ። አብዛኞቹም የሚሆነውን ከማየት የዘለለ ለማገላገል ሲሯሯጡ አይስተዋልም።

እንግዲህ የድሮን ነገር ድሮ ያነሳዋል እንደሚባለው እኔ ደግሞ ዘንድሮ ላይ ሆኜ ከዓመታት በፊት ስለነበረኝ የሰኔ ሰላሳ ትዝታዎች ላስታውስ። ከአመታት በፊት የአንደኛ ደረጃ ተማሪ እያለው የብዙ ጓደኞቼን ፊት ክረምቱ አልፎ ወደ ትምርት ቤት በሚገባበት ወቅት ፊታቸው ላይ የሚታየው ጠባሳ እንዲሁም ከተፋላሚያቸው ጋር የሚተያዩትን የቂም በቀል እይታ ሊረሳ የሚቻል አልነበረም። የዚህ ምልክት በቶሎ ያለመፍዘዝ ምክንያት ደግሞ ጉዳዩ ጥቂት ጊዜያትን ብቻ ያስቆጠረ በመሆኑና በቀላሉ ለመጥፋት አዳጋች ስለሚሆን ነው።

እነዚህ ታሪኮች ደግሞ ክፉም ይሁኑ በጎ የማይረሱ መሆናቸው አይቀርም። ቀናት እንደዋዛ እየፈጠኑ፣ ወራት በዓመታት ሲተኩ ደግሞ ያለፈው ሁሉ በትዝታ እየተዋዛ ትውስ ባለ ቁጥር እንባና ፈገግታን ቢዳብስ የሚያስገርም አይሆንም። ያማ ባይሆን ኖሮ ያለፈውን እውነታም አሁን ላይ ሆነን “ነበር” እያልን ባላራነው።

ይህንንም አስመልክቶ የልጅነት ትውስታውን በማይጠገብ አነጋገር “ነበር” በሚል ቃል እየቋጨ ሲተርክልን የነበረው አንተነህ ዕድሜው ወደ አርባዎቹ ገደማ የሚጠጋጋ ቢሆንም በሰኔ 30 ቀን የሚያሳልፋትን ቀን ግን አልዘነጋትም። “ሰባተኛ ክፍል እያለው በክፍል ጓደኞቼ በተለየ በሁሉም ቦታ የምገኝ እንዲሁም በትምህርቴ ጎበዝ ነገር ግን ረባሻ ከሚባሉ ተማሪዎች ውስጥ የምመደብ ተማሪ ነብርኩ። በዛን ወቅት ነበር ከጓደኞቼ ጋር በመሆን ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ተጣላን እና ሰኔ 30 ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘን ተለያየን። የማደርስ የለምና በጉጉት እንዲሁም በፍርሃት ስጠብቃት የነበረችው ቀን ደረሰች። በጠዋት ተነስቼ ከዩኒፎርም ላይ ወፍራም የክረምት ጃኬቴን ደርቤ ከቤት ወጣሁ። ትምርት ቤት እንደደረስኩ ከጓደኞቼ ጋር ተገናኘን። በዕለቱ የሚቀር ተማሪ አልነበረም ምክንያቱም ውጤታችንን በእጃችን የምናስገባበት እንዲሁም ደግሞ የደረጃ ተማሪ ከሆንን ሽልማት የምናገኝበት ቀን ስለነበረ። ይሁንና ጓደኞቼን ሳገኛቸው ፊታቸው ላይ ምንም ዓይነት ፍርሃት ባይነበብም የመረበሽ ስሜት ግን ይስተዋልባቸው ነበር። ከጓደኞቼ ጋር ስለ ቀጠሯችን እንዲሁም ደግሞ ለስምንተኛ ክፍል ክብራችን ስንል እንዴት በድል እንደምንወጣው በመነጋገር ሰርተፍኬት ለመውሰድ ወደየ ክፍሎቻቸን ተበታተንን። እንደተለመደው የሰኔ 30 ቀን በትምህርት ቤት ግቢ ውስጥ አስገራሚ አስቂኝ እንዲሁም ደግሞ አሳዛን ታሪክ አይጠፋም። አብዛኛው ተማሪ ግብ ሰርተፍኬቱን በእጁ ካስገባ በኋላ ስለውጤቱ መቀነስ እንዲሁም መጨመር ሳይሆን ውጪ ስለሚጮኸው ጩኸት እና በቀጣይ ዓመት ለትንሽ ሳምንታት የሚስቁበትን ተማሪ ለማወቅ ሲሯሯጡ ይስተዋላል።

“በሚያሳዝን ሁኔታ ግን” አለ አንተነህ ፈገግታ በተሞላበት ቀጭን ፊቱ “የዛን ዓመት ተረኛ ነበርኩና ከበፊቱ ዘግየት ብዬ እንዲሁም የሚቆራረጠውን ትንፋሼ ለማስተካከል እየጣርኩ ነበር ከግቢ የወጣሁት። በሚያሳዝን ሁኔታ ግን ከጓደኞቼ ሁሉ ለድብድቡ የተዘጋጀሁት እና በቦታው የተገኘሁት እኔ ነበርኩና ከጠላቶቼ ጋር ፊት ለፊት ተጋፈጥኩ። የዛን ቀን ነበር በሕይወቴ ለመጀመርያ ጊዜ በአንዴ የተለያዩ አስገራሚ አሳቦችን ያሳብኩት። ያም ሆኖ ግን አንዱም አልተሳካልኝም የስምንተኛ ክፍል የሳምንቱ ርህስ ነበርኩ አለ። ጎላ ብላ የምትታየው ወላቃ የዛ ሚስጢር መሆኗን ለማሳወቅ ፈገግ ያለ ይመስላል። በዛን ወቅት ከሁሉም ጊዜ በበለጠ የሰኔን ወር የመጨረሻውን ቀን በጉጉትና በፍርሃት የሚጠብቁ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ሊበዛ ይችላል። የሚያስገርመው ነገር ግን ለሰኔ 30 ተቀጣጥሮ የሚቀር ተማሪ አለመኖሩ ነው። ይህን አድርጎት ቢገኝ እንኳን ለከርሞ የሚለጠፍበትን “ፈሪና ቦቅቧቃ” የሚለውን ሥያሜ መቋቋም አይቻለውም። መልሶ ትምህርት ቤት ሲከፈትና ተማሪው ዳግም ሲገናኝ ይህ ሥም እንዲለጠፍባቸው የማይሹ ተፋላሚዎች በድብድቡ ቢሸነፉም ባያሸነፉም በቀጠሮ ይገናኛሉ። በዕለቱም አሸናፊ ባይሆኑ እንኳን ጉልበታቸውን እና አቅማቸውን አሳይተዋልና ማንነታቸውን በማስከበራቸው ብቻ ደስተኛ ይሆናሉ።

አንዳንዴ ጎበዝ የሚባሉት ተማሪዎች ሰነፍ የሚባሉትን የክፍል ጓደኞቻቸውን ለማስኮረጅ ባልፈቀዱ ጊዜ ዓመቱን ሁሉ የሚደርስባቸው ማስፈራሪያ “ሰኔ ሰላሳ እንገናኝ” የሚል ነበር። አንዳንዶችም ራሳቸውን እንደ ስፖርተኛ አበርትተውና ለድብድቡ በእጅጉ ተዘጋጅተው ይጠብቃሉ። የእነሱ የመደባደብ አዋጅ የሚሰማው ለአብዛኛው ተማሪዎች በመሆኑም ደጋፊዎቻቸውና አጃቢዎቻቸው ይበረክታሉ።

እንደነዚ ዓይነት ትዕቢተኛ ተማሪዎች በበርካቶች ዘንድ የሚፈሩና የሚከበሩ በመሆናቸው እነሱን በውዴታም ይሁን በግዴታ ለመደገፍ የሚሰባሰበው ተማሪ ቁጥር የበዛ ነው። የዛኔ ታዲያ አስቀድሞ የድብድቡ ዜና ቤተሰብ ዘንድ ከደረሰ በዕለቱ ከልጆቻቸው ጋር አብረው የሚሄዱ አልፎም ለቀጣዩ ዓመት ትምህርት ቤት እስከመቀየር የሚደርሱ ወላጆች አይጠፉም።

“አይ ሰኔ ሰለሳ” በጣም የሚገርመው በአንዳንድ ሴት ተማሪዎች የሚደረገው የድብድብ መሰናዶ ነው። እነዚህ ልጆች በተለየ ዝግጅት ጥፍሮቻቸውን አሹለው ከማሳደግ በዘለለ የምትፋለማቸውን ተማሪ ዕይታ ለማደናቀፍና ዕድለኛ ለመሆን ሲሉ ሚጥሚጣ አልያም በርበሬ ይዘው ይመጣሉ። በተለይ ድብድቡ ከመጀመሩ አስቀድሞ የያዙትን ብናኝ ዓይን ውስጥ ከጨመሩ ያለምንም ጥርጥር ጨዋታውን በድል ያጠናቅቃሉ።

እንዲህ ዓይነቶቹ ልጆች ታዲያ ባሾሏቸው ጥፍሮች መቧጠጥ የሚፈልጉት የተፋላሚያቸውን ፊት ብቻ ይሆናል። ምናልባትም ይህን ማድረጋቸው ገጽታን ለማበላሸትና “ምልክቱ እኮ! የእኔ ነው” ብሎ ለመጎረር ያግዛቸው ይሆናል። እግረ መንገዳቸውንም በፊት ላይ ያኖሩት በጥፍር የመቧጨር ምልክት ማንነታቸውን የሚያስመሰክር ነውና ማንም እንዳይዳፈራቸው ጭምር ይጠቀሙበታል። እነዚህኞቹ በሰኔ ሰላሳ የሚተውት አሻራ ነው መስከረም ድረስ ሳይደበዝዝ የሚቆየው።

“ሰኔ ሰላሳ የተማሪ አበሳ” የምትለዋን አባባል አብዛኛው ተማሪ የሚረሳው አይመስለኝም። በዛን ቀን የድብድብ ቀጠሮ ካላቸው ተማሪዎች በዘለለ ምንም ሳይነጋገሩ ለጠብ የሚገባበዙ ተማሪዎች ሊያጋጥሙ ይችላሉ። ለምን ከተባለ ደግሞ ቀኑ ሰኔ ሰላሳ ስለሆነ! ብዙ ጊዜ ይህ ሲያጋጥም በተለይ ፈጽሞ ለመደባደብ ላላሰቡት አንዳንድ ተማሪዎች ፈተና የሚሆንበት ጊዜ ይበረክታል። ጠቡን ያሰበው ልጅ የቀደመ ቂሙን የማይረሳና እሱ ብቻ የሚዘጋጅ ስለሚሆንም አንዱ ወገን ያልታሰበ ጉዳትን ማስተናገዱ አይቀሬ ይሆናል።

አንዳንዴ ግን የሰኔ ሰላሳ ጉዳይ የፍቅር ጉዳይንም ያካታል። ይህ አጋጣሚ ብዙ ጊዜ ወንዶች በዓይን ብቻ የወደዷትን ተማሪ ስለማፍቀራቸው የሚገልጹበት መንገድ ስለሚሆን ዕድሉን ይጠቀሙበታል፤ ደብዳቤን ተቀብሎ ማስቀመጡ ብቻ በቂ ስለማይሆን። ምክንያቱም ዓመቱን ሙሉ የፍቅር ግጥሞችን እና ስዕሎችን እየሰጠ ሲጠብቅ የከረመ አፍቃሪ እሺታን ይፈልጋል። እናም ይህ አፍቃሪ ሰኔ ሰላሳን ጠብቆ “እህሳ” ማለቱ አይቀርም። የደብዳቤው መልስ በተማሪዋ እሽታ የሚጠናቀቅ ከሆነ እሰዬው ነው፤ ካለበለዚያ ግን በካልቾ ማንከባለል ስለማይቀር ይህ አይነቱ አጋጣሚ አስቂኝ ትዝታ ይሆናል። የዘንድሮውስ ሰኔ ሰላሳ ምን ዓይነት ይሆን?

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here