የመንግሥት ምርኮኝነት በኢትዮጵያ አለ?!

0
585

የመንግሥት ምርኮኝነት ብያኔ ጥቂት፣ ነገር ግን ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ቡድኖች የመንግሥታትን እጅ መጠምዘዝ ከመጀመራቸው ጋር የሚተሳሰር መሆኑን የዓለም ባንክን ዋቢ በማድረግ የሚጠቅሱት ይነገር ጌታቸው, ይሔ የመንግሥት ምርኮኝነት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን (ዶ/ር) አስተዳደር ጠልፎ ነበር ሲሉ ተጨባጭ ያሏቸውን አብነቶች በማስረጃነት አቅርበዋል። የዐቢይ አስተዳደር ከዳግም ምርኮ መንግሥትነት ለማላቀቅ መሥራት ይገባዋል ሲሉ ምክረ ሐሳባቸውንም ሰንዝረዋል።

ከሳምንታት በፊት የአማራ ክልል ምክር ቤት አባላት በሕገ መንግሥቱና ፌደራሊዝሙ ዙሪያ የሚያተኩር ሥልጠና እየተሰጣቸው ነበር። በዚህ መድረክ ላይ “የፌደራሊዝሙ ጠንካራ ጎን ምንድን ነው? ክልሉስ አሁን ከገባበት አለመረጋጋት እንዴት መላቀቅ ይችላል?” የሚሉ ሐሳቦች ተነስተዋል።

አዕላፍት ጥያቄዎች በተንሸራሸሩበት አዳራሽ ውስጥ የአንድ ተናጋሪ አሰተያየት ትልቅ ውዝግብን አስነሳ። በመንግሥት ኀላፊነት ላይ የሚገኙት እኒህ ሰው “አማራ ክልል ሰላም እንዲሆን ከተፈለገ ከጀርባ ሆኖ ክልሉን የሚመራው ኀይል እጁን ሊሰበስብ ይገባል?” የሚል መፍትሔን አቀረቡ።

እንዲህ ያለው የምክር ቤቱ አባል አስተያየት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ አባል የሆኑትን ጌታቸው ረዳ ንግግር የሚያስታውሰን ይመስላል። ጌታቸው ከወራት በፊት የኢትዮ ኤረትራን የሰላም ስምምነት በተመለከተ በጎልደን ቱሊፕ ሆቴል በተከሔደ የፓናል ውይይት ላይ ኹለቱ አገራት የተሰማሙባቸውን ነጥቦች እንደ ገዢ ፓርቲ አመራርነታቸው በውሉ እንደማያውቋቸው ሳይሸሽጉ ተናግረዋል። “እኔ ብቻ ሳልሆን አብዛኛው የሥራ አስፈፃሚ አባላት የስምምነቶቹን ዋና ዋና ነጥቦቹ ግለፁ ብንባል የምንሰጠው ምላሽ የለንም” ሲሉም ተደምጠዋል።

የኹለቱ ግለሰቦች አስተያየት “በኢትዮጵያ ያለው አስተዳደር ምርኮኛ መንግሥት (state capture) ሊባል ይችላል ወይ?” የሚለውን ጥያቄ አንድናነሳ ዕድል ይሰጠናል።

የመንግሥት ምርኮኝነት ወይስ ስውር መንግሥት?
የፖለቲካ ታሪካችን አዳሪያን አቋርቋዥና ኪራይ ሰብሳቢ የሚሉ ቃላትን ወዝ የጠገበ ቢሆንም ስለገዥዎቻችን ምርኮኝነት ግን ብዙ አይናገረም። በመሆኑም ምርኮኛ የሆኑ ስርዓቶች በኢትዮጵያ ነበሩ ወይንስ አልነበሩም የሚል ሙግት ከማንሳታችን በፊት የመንግሥት ምርኮኝነት በራሱ ምንድን ነው የሚለውን መመለስ ያስፈልጋል።
የመንግሥት ምርኮኝነት የሚለውን ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ያስተዋወቀው የዓለም ባንክ ሲሆን ትርጉሙንም ጥቂት፣ ነገር ግን ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ቡድኖች የመንግሥታትን እጅ መጠምዘዝ ከመጀመራቸው ጋር እንደሚተሳሰር ያወሳል። ከሶቨየት ኅብረት መፈራረስ በኋላ ዓለምን የሞሏት እንደካዛኪስታ፣ ኡዝቤክስታንና ካራኪስታን የመሳሰሉት አገራትም በዚህ ዓይነቱ ማዕበል የተጠቁ እንደነበሩ ያስታውሳል።

ለችካጎ ዩኒቨርሲቲው የሕዝብ አስተዳደር ተመራማሪው ራስማ ካርኪልንስ (ፕሮፌሰር) ግን የዓለም ባንክ ብያኔ ጉድለቶች ያሉበት ነው። በዚህ መነሻም የመንግሥት ምርኮኝነትን ለየፖለቲካ ሙስና በተጠናወታቸው አገራት ውስጥ የሚስተዋልና አንድን ስርዓት ለተሰወነ ቡድን ወይንም ግለሰብ ሎሌ እንዲሆን የማድረግ ሒደት ነው። የአፍሪካን ነባራዊ ሁኔታ ከምርኮ መንግሥታት አንፃር የተመለከቱት ቶም ሎጅ በአንፃሩ የቃሉ ትርጉም በአገራት ዓውድ ውስጥ መታየት አለበት የሚል አስተያየትን ይሰነዝራሉ። “State capture in Africa” በተባለው ጥናታዊ መጽሐፍ ላይ ምርምራቸውን ያሰፈሩት ሎጅ አፍሪካ ውስጥ ያለው የመንግሥታት ምርኮኝነት በምሥራቅ አውሮፓ የታየውን ዓይነት ጥቂት የማፍያ ቡድኖች የሚዘውሩት ፖለቲካ ሳይሆን ሌላ መልክ ያለው ነው ሲሉ ይሟገታሉ።

የሰሃራ በታች አገራት የመንግሥት ምርኮኝነትም ከአምባገነናዊ መሪዎች ፈላጫቆራጭነት አንስቶ እስከ ትላልቅ ባለሥልጣናት የሙስና ወንጀሎች እንደሚደርስ ይጠቅሰሉ።

ለቃሉ የሚሆን አጭር ብያኔን ለመስጠት የተቸገሩ የሚመስሉት ሎጅ መንግሥታዊ ምርኮኝነት የተወሰነ ቡድን አልያም ግለሰብ ለራሱ የሚመቸውን ዓይነት የፖለቲካ መጫወቻ ሕግ ለማውጣት ሲሞክር አልያም አውጥቶ አገራትን የሚዘውርበት መንገድ መሆኑን ያስረግጣሉ። ይህ ደግሞ በገዥ ፓርቲዎች ውስጥም የሚፈጠር መሆኑን ያስረግጣሉ።

እዚህ ላይ ግን በአፍሪካ አገራት የሚሰተዋለውን የቃሉን አረዳድ ትርጉም ለመለየት የሚያስችለን አንድ ጥየቄ እናንሳ።ምርኮኛ መንግሥታት ከስውር መንግሥታት (deep state) በምን ይለያሉ? ስውር መንግሥት በአብዛኛው አምባገነናዊ በሆኑ ስርዓቶች ውስጥ የሚስተዋል ሲሆን ወታደራዊና የደኅንነት ሹማምንት ከግሉ ዘረፍ ጋር በመጣመር ለራሳቸው የሚመቻቸውን ዓይነት አስተዳደር የሚፈጥሩበት ሒደት ነው። ይህ ሒደት ከመንግሥታዊ ስርዓቱ ኪራይ ለመሰብሰብ ከመሞከር ይልቅ በሥልጣን ላይ ያለውን ኃይል ሽፋን አድርጎ አገርን ከመመራት ጋር ይያያዘል። በኢትዮጵያ የእንዲህ ያለ ስርዓት ስለመኖሩ ጠቋሚ ምልክቶች በጠቅላይ ሚኒስትር ኀይለማሪያም ደሳለኝ የመሪነት ዘመን ይስተዋሉ የነበረ ሲሆን ለውጡን ተከትሎ ግን እየቀነሱ ሔደዋል።

በመሆኑም ዛሬ ላይ ሊፃፍ የሚገባው የፖለቲካ ሐቲት ከስውር መንግሥት ይልቅ ለምርኮ መንግሥት ያደላ መሆን ይኖርበታል።

የመንግሥት ምርኮኝነት – ትናንት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ያለፈው ዘመን የስርዓት ገመና ለአደባባይ መብቃት ጀምሯል። የሜቴክ የቢሊዮን ብር ፕሮጀክቶች ውጤታማ አለመሆንና የእርምት እርምጃ ሳይወሰድ ለዓመታት መንከባለልም መንግሥታዊ ምርኮኝነት ለአገራችን አዲስ አለመሆኑ ያረጋግጣል። የኀይለማሪያም ምርኮኛ ስርዓት አንድም ምሥራቅ አውሮፓዊ መልክ ሲኖረው አንድም አፍሪካዊ ገፅታን የተላበሰ ነው። ምሥራቅ አውሮፓዊ መልኩ ከምጣኔ ሀብታዊ የምርኮ መንግሥትነት ባሕሪው ይመነጫል። ሩቅ ሳንሔድ ከመንግሥት አሠራር ጋር የሚጋጩና በማናለብኝነት ሲካሔዱ የነበሩ የሜቴክ ተግባራት ለዚህ ማሳያ ናቸው።

የዚህ ድርጅት አመራሮች ኀይለማሪያም መራሹን አስተዳደር የይስሙላ መንግሥት በማድረግ እንዳሻቸው የመንግሥት ፖሊሲዎችን በማስቀየር በተላያዩ የምጣኔ ሀብት ሙስና ተግባራት ተዘፍቀው መኖራቸው ተደጋግሞ ተነግሯል። ከፑቲን በፊት እንደነበሩት የሩሲያ ባላሀብቶች የምጣኔ ሀብት ውድድር መጫወቻ ሕጉን እራሳቸው አርቀቀው መንግሥት እንዲያውጅላቸው ሲያደርጉም ኖረዋል።

በዚህም ተሸናፊና ተጠያቂነት በሌለው አካሔድ የቢሊዮኖች ብር ኪሳራን በአገር ላይ አስከትለዋል። ከዓመት በፊት የነበረው የመንግሥት ምርኮኝነት የተወሰኑ ቡድኖች ከታች ሆነው የሚዘውሩት ብቻ ሳይሆን ግሰቦችም እንዳሻቸው መፈንጨት የጀመሩበት ነበር።

በርከት ስምዖን “ትንሳኤዘ-ኢትዮጵያ ከመንታ መንገድ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ኢሕአዴግ በ2008 ክረምት ላይ ያካሔደው ግምገማ ያረጋገጠው እውነት ጥገኛ ባለሀብቶች መንግሥትን ወደ ማሾር እየተንደረደሩ መሆኑን ነው ይላሉ። አንድ ባለሀብት በሥልጣን ላይ ያለን ሚኒስትር ወንበርህ ላይ ለመቆየት ከፈለክ የምልህን አድርግ ብሎ ማስገደድ ወደ ሚችለበት ደረጃ መሸጋገራችንንም ያነሳሉ። በረከት የእምነት ክህደት ቃላቸውን የሰጡበት በሚመስል በዚህ የመጽሐፋቸው ክፍል የመንግሥት ምርኮኝነት ስርዓቱን ተብትቦ የያዘ መሆኑን ከመናገር ወደ ኋላ አላሉም።

በማረሚያ ቤት ያሉ ባላሀብቶ ወደ ቢሯቸው ጎራ እያሉ ድርጅታቸውን እንደሚያስተዳድሩ፤ ከዛም አልፎ ከትዳር አጋራቸው ልጅ እስከ መውለድ እንደደረሱም ይገልፃሉ። ቡድናዊም ሆነ ግለሰባዊ ምርኮኛ የሆነው የኀይለማሪም አስተዳደር ወደ ነጣቂ መንግሥትነት (predatory state) መሽቆልቆል ቢጀምርም ሕዝባዊ ተቃውሞው ግን እዚያ የሚያደርሰው አልነበርም። በዚህ የተነሳም ስውርም ምርኮኝነትም የተጣባው መንግሥት ተንኮታኮተ። በኢትዮጵያም በግማሽ ምዕተ ዓመት ውስጥ ስድስተኛ የተባለው የፖለቲካ ለውጥ ጉዞውን አሃዱ አለ።

የምርኮ መንግስት – ዛሬ
በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የፖለቲካ ለውጥ ተከትሎ መንግሥት ምረኮኛ ነው የሚለው አሰተሳሰብ ሰፊ ቦታን እያገኘ ሔዷል። በአገሪቱ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የእኔ እበልጥ አስተሳስብ የተጠናወታቸው የሦስቱ ብሔር ልኂቃን ልዩነት የሚጠብበት ብቸኛ መስመርም ይኼው የመንግሥት ምርኮኝነት ሆኗል፤ ግን ምርኮኛ መንግሥት መኖሩ እንጅ ለማን ነው የተማረከው የሚለው ሐሳብ አያግባባም።

የአማራ ፖለቲካ ልኂቃን ጀዋር መሐመድ እና አክራሪ የኦሮሞ ብሔርተኞች መንግሥትን ከጀርባ ሆነው እንዳሻቸው እያሾሩት ነው የሚል ወቀሳ ይሰነዝራሉ። ጀዋር መሐመድ በይፋ የሚቃወማቸው ነገሮች ሙሉ በሙሉ አልያም በከፊል መሰረዛቸውም ለዚህ ማስረጃ ነው ይላሉ።

የትግራይ ፖለቲካ ልኂቃን በአንፃሩ የዐቢይን አስተዳደር ምርኮኝነት ከውጭ መንግሥታት ጋር ያስተሳስሩታል። ካለፈው መጋቢት በኋላ የመጣውን ለውጥም የምዕራባዊያን ሎሌነት የተጠናወተው ስለመሆኑ ይገልፃሉ። ከዚህ ጋር አስተሳስረውም የተባበሩት አረብ ኤምትና ሳዑዲ አረቢያ አራት ኪሎ ፖለቲካ ውስጥ እየፈተፈቱ ነው ይላሉ። ከወራት በፊት ፋይናንሽያል ታይመስ ያወጣውን ዘገባ ዋቢ በማድረግም የአቡዳቢው ንጉሥ ቤንዛይድ ዐቢይ አሕመድን የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ግብፅን ስለሚጎዳ ከቻልክ አቋርጠው አልያም አዘግየው ብለው እንደመከሩና ተፈፃሚም እንደሆነም ይጠቅሳሉ።

የአክራሪ ኦሮሞ ብሔርተኞች የምርኮኛ መንግሥት ክርክር በአንፃሩ ከላይ ከጠቀስናቸው የሰሜን ፖለቲካ ልኂቃን ሙግት የተለየ መልክ ያለው ነው። ለእነዚህ ወገኖች የለውጥ ኀይል የሚባለው አካል በአንድነት ሥም ጨፍላቂ የዜግነት ፖለቲካን በሚያራምዱ ፖለቲከኞች ተማርኳል። በሥልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትርም የሚያከናውኑት ተግባርም ለቀደመው አሃደዊ ስርዓት ማደራቸውን ያረጋግጣል።

ኢትዮጵያ ባለፈው አንድ ዓመት የሔደችበትን የፖለቲካ ፍኖት መሰረት አድርጎ ብሔር መር ምርኮኝት መኖሩ ባያጠራጥርም የአራት ኪሎን ፖለቲካ በዚህ ውስጥ መቃኘቱ ግን አዳጋች ይሆናል። ለዚህ ደግሞ ኹለት ምክንያቶችን መጠቀሱ በቂ ነው።የመጀመሪያው ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑ ላይ አሁንም አለሁ ከማለቱ ይቀዳል። ገዥው ፓርቲ ዛሬም በጋራ ውሳኔዎች አገር እያስተዳደርኩ ነው ማለቱን ቀጥሏል።

እህትና አጋር ፓርቲዎችም በአደባባይ ቢዘላለፉም አራት ኪሎ ያለው አስተዳደር የእኔን ብሔር አይወክልም ወደ ማለት አልተጠጉም። ሌላው እና ወሳኙ ነጥብ የዐቢይ አስተዳደር ፍኖተ ካርታ የሌለው ከመሆኑ ይመነጫል። የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በምን ዓይነት የአስተዳደር ስርዓት መፍታት እንደሚቻል ባላስቀመጠበት ሁኔታው ግን እንደዚህ ነው ማለት ያዳግታል። የስርዓቱ ቁንጮዎች መርህ አልባ ሆነው እያለ እዚህ ናቸው ብሎ መመደብም የሚቻል አይመስልም። የእነዚህ ነገሮች ድምር ውጤት ደግሞ የምኒልክ ቤተ መንግሥትን የአንድ ብሔር የፖለቲካ ልኂቃን ምርኮ ነው ለማለት እንድንቸገር ያደርጋል።

ይህ ማለት ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ብሔርን መሰረት ያደረገ መንግሥታዊ ምርኮ የለም ማለት አይደለም። በአሁኑ ወቅት በየክልሉ የሚስተዋሉ ፖለቲካዊ ትኩሳቶችም በትልልቅ ባለሀብቶች የገንዘብ ድጋፍ የሚዘወሩ የራስን ስርዓት ለመትከል የሚደረጉ ትንቅንቆች ናቸው። ደቡብ ክልል ለዚህ ጥሩ ማሳያ ይሆናል። የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሕዝባዊ የመሆኑን ያህል፣ የራስን ምቹ ስርዓት ለመፍጠር የሚሞከርበት መንገድ መሆኑ አያጠያይቅም። ከፋ፣ ወላይታ፣ ጋሞ የምንመለከታቸው የክልልነት ጥያቄዎችም ከማኅበረሰባዊ ፍላጎት ባልተናነሰ የራሳቸው ሎሌ መንግሥትን ለመፍጠር የሚተጉ ኀይሎች መገለጫ ናቸው ።

በዛሬዋ ኢትዮጵያ የየራሳቸውን የፖለቲካ ፓርቲ የሚረዱና በየክልላቸው ካለ ከልካይ ያሻቸውን ነገር የሚፈፅሙ ሚሊየነሮች መበራካታቸው አያጠያይቅም። በፌደራል መንግሥት ደረጃም የሚኒስትሮችን የውጭ ሕክምና ወጪ የሚሸፍኑ፤ የባለሥልጣናትን ልጆች የትምህርት ቤት ክፍያ የሚችሉ ከዚህ ከፍ ሲልም በድብቅ የቤተሰብ አባል አስገብተው በሽርክና የሚሠሩ መኖራቸው አያጠራጥርም። በቅርብ አንድ ወዳጄ እንዳጫወተኝ ደግሞ በአሁኑ ወቅት ሥልጣን ላይ ካሉ ሚኒስትሮች ስድስቱ በአንድ ታዋቂ ባላሀብት ሃይማኖት የቀየሩና በእርሱ ይሁንታ ለኀላፊነት የበቁ ናቸው።

የተባበሩት አረብ ኤምሬት ባላሀብቶች በለገሀር ከአዲስ አበባ ከተማ የዐሥር ዓመት መሪ ፕላን ጋር በሚጣረስ መልኩ ካለጨረታ መሬት ተሰጥቷቸው ወደ ሥራ መግባታቸው፤ ከኢትዮ ኤርትራ የሰላም ወዳጅነት ጋር የተደረጉ ስምምነቶች ምን እንደሆኑ በይፋ አለመሰማታቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአሜሪካ በነበራቸው ቆይታ ከአርበኞች ግንቦት 7 መሪዎች ጋር የነበራቸው ውይይት ምን እንደሆነ በግልፅ አለመታወቁ በቶም ሎጅ የተጠቀሰው የምርኮ መንግሥታት መግለጫ የኢትዮጵያም የዛሬ እውነት መሆኑን ያረጋግጣል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሕግ ባለሙያዎችን ባነጋገሩበት ወቅት የአብዛኞቹን ክልል አመራሮች ቀይረናል የሚለው የአፍ ወለምታቸውም የፌደሬሽኑ አባለት ሉዓላዊነት ተንዶ ከአማራ ክልል ምክር ቤት የምንሰማውን ዓይነት ቅሬታ ሰፊ መሰረት እንዳይኖረው ያሰጋል። ይህ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 12(1) ላይ የተደነገገውን የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መልኩ መከናወን አለበት የሚለውን ከመጣሱም በላይ የአገሪቱን ፖለቲካ ለውጥ ጅምር በጊዜ ሒደት አደጋ ይጥለዋል።

በመሆኑም ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ አስተዳደራቸውን ከዳግም ምርኮ መንግሥት (restate capture) የማላቀቅ ሥራውን ሊጀምሩ ይገባል። ትናንት በወደቁበት መንገድ ተጉዞ ለውጥን ማምጣት ሞኝነት ነውና ለጉዳዩ ትኩርት መስጠት ያስፈልጋል።

አስማማው ኃይለጊዮርጊስ ጋዜጠኛ እና የኢንዶውመንት ፎር ዴሞክራሲ ፌሎ ናቸው። በኢሜይል አድራሻቸው
asamamawg@ned.org ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here