የውጭ ጉዳይ ፖሊሲያችንና እስላማዊ ባንክ

0
718

የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከአደጉ አገራት ተፅዕኖ ሙሉ ለሙሉ ነፃ ማድረግ ባይቻል እንኳን ከማንም ጋር ያልወገነ ገለልተኛ እንዲሁም የራሳችን ስትራቴጂያዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መቃኘት አለበት የሚሉት መላኩ አዳል፣ ከእስላማዊ ባንክ ምሥረታ ጋር ተያይዞ እስላማዊ አገራት እጃቸውን አያስገቡም ማለት ግን ሞኝነት ሲሉ መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ። የብሔር ልዩነታችንን ሳንወጣ የሃይማኖት ልዩነት መሠረት ያደረገ የኢኮኖሚና የሥልጣን ሽኩቻ ለኢትዮጵያ ኅልውናና አንድነት መደፍረስ መንስኤ ይሆናል በሚል ይሞግታሉ 

የውጭ ጉዳይ አገራት በአካባቢያዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም ዐቀፍ መድረኮች ላይ የሚኖራቸውን እንቅስቃሴ የሚመለከትና የአገራት ሉዓላዊነት መገለጫም ነው። አንዳንድ ጊዜ ክልሎች ባሕላቸውን፣ ኢኮኖሚያቸውን ለማሳደግ፣ የድንበር አካባቢ ጸጥታዎችን በተመለከተ ከሌሎች አገራት ጋር የውጭ ግንኙነት የማድረግ ፍላጎት ሊኖራቸው ይችላል። ይህም የአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ያልተቀናጀ፣ በተለያዩ ፍላጎቶች የታጀበ በማድረግ አገሪቱን በዓለም ዐቀፍ መድረክ ላይ ውጤታማ እንዳትሆን ሊያደርጋት ይችላል። ስለዚህም ውጭ ግንኙነት በአንድ ድምጽ የሚናገር ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት ይፈልጋል። ነገር ግን ክልሎችን የማማከርና በፌዴራል መንግሥቱ ሥር በሒደቱ የሚሳተፉበትን ማዕቀፍ ቢኖር ጥሩ ነው። የተወካዮች ምክር ቤትም የውጭ ጉዳይ ሕጎች የክልሎችን መብትና ጥቅም የማይጎዱ መሆናቸውን ማረጋገጥ ይኖርበታል። ይህም ማለት የፌደራል መንግሥት የውጭ ጉዳይን የሚመለከቱ ጉዳዩችን ጠቅልሎ የመሥራት ሕገ መንግሥታዊ ሥልጣን ቢኖረውም፤ የፌደራል መንግሥቱ የሚፈርማቸው ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች የክልል መንግሥታትን ጥቅምና ፍላጎት በቀጥታም ይሁን በተዘዋሪ መንገድ መንካታቸው አይቀርም። እንዲሁም አንዳንድ ስምምነቶች ካለክልል መንግሥታት ተሳትፎ ውጤታማ መሆን አይችሉም። ስለዚህ ክልሎች በውጭ ጉዳይ ላይ የሚኖራቸው ተሳትፎ ውጤታማ የሆነ የውጭ ግንኙነት ለማድረግም ሆነ ጤናማ ፌደራላዊ ስርዓት ለመፍጠር አስተዋጾዖ እንዳለው መገንዘብ ያስፈልጋል።

የውጭ ግንኙነት ፖሊሲያችንን በአደጉ አገራት ተፅዕኖ ውስጥ እንደመሆኑ ከዚህ ተፅዕኖ ሙሉ በሙሉ የመውጫ መንገድ ባይኖርም ከማንም ባልወገነ ገለልተኛና የራሳችን ስትራቴጂያዊ ጥቅም በሚያስጠብቅ መልኩ መቃኘት አለበት። ይህም አገራችን ማግኝት ያለባትን ጥቅም እንዳታጣ ከየትኛውም አገር ጋር በጋራ ተጠቃሚነት መርህ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንድታደርግ፣ ሉዓላዊነቷንም እንድትጠብቅ ያግዛታል። ዋናዎቹ የኢትዮጵያ የውጭ ተፅዕኖዎች በሆኑት የልዕለ ኀያላን ሽኩቻና የቀይ ባሕር ወደ ወታደራዊ ቀጠናነት መቀየር፤ የርዕዮተ ዓለም ተፅዕኖና የመካከለኛው ምሥራቅ ፖለቲካና የነዳጅ ሀብት ጡንቻ በአገራችን ላይ ሊያስከትል የሚችለውን አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ተፅዕኖ ማጥናትና ተገቢውን ሥራ መሥራት ይኖርብናል። በተጨማሪም ከአፍሪካ ቀንድ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅና ከሰሜን አፍሪካ በኩል የሚመጣን አደጋ ለመቆጣጠር የዓለም ዐቀፋዊና የአካባቢያዊ ዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት የአካባቢያችን ብሎም የአገራችን ሰላም መጠበቅ አለብን። የመሪዎች በአካባቢያዊ፣ አሕጉራዊና ዓለም ዐቀፍዊ ጉዳዮች መሳተፍ፤ ብሎም የአገር መከላከያ በተለያዩ ቦታዎች በሰላም ማስከበር መሰማራቱ ለውጭ ግንኙነት ያግዛል።

በቻይና፣ ራሽያ፣ ኢራን፣ ካታር፣ ቱሩክ በአንድ በኩል፤ አሜሪካ፣ ምዕራብ አውሮፖ፣ ሳዑዲ፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሪት፣ ባሕሬን፣ ግብፅ በሌላ በኩል ተሰልፈው በሚጠዛጠዙበት የዓለም ፖለቲካ ገብተን አንዳንጨፈለቅ፣ ውስብስብ የሆነውን የምሥራቅ አፍሪካ ፖለቲካ መረዳት፣ አስተውሎ መንቀሳቀስን፣ የኀያላን ፍላጎትን መረዳት፣ አገራችን የገለልተኝነት መርህዋን መከተል ያስፈልጋል። የኹለቱ ቡድን የመን ላይ በጦር እንዲሁም በዲፕሎማሲ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ተመሳሳይ ሁኔታ ተጎጂ እንዳንሆን እየተጠነቀቅን የአገራችን ጥቅም ማስጠበቅ ይኖርብናል። የምዕራቡንም የምሥራቁንም ዓለም የማያስከፋና ኢትዮጵያዊ በሆነ የራሳችን ርዕዮተ ዓለም በመቀመር፤ የውጭ የዲፕሎማሲ ግንኙነታችን በማጠንከር፤ አገራችንን ከውጭ ጣልቃ ገብነት በመጠበቅ ዕድገታችን ማስቀጠልና የሕዝባችን አንድንትም መጠበቅ ይኖርብናል።

ከጎረቤት አገራት በተለይም ከሱዳንና ከኤርትራ ጋር ያለውን ግንኙነት በጥንቃቄ መያዝ አለበት። ከኤርትራ ጋር የተደረገው ስምምነት በአረብ አገራት የሚደረገውን ከበባና የማዳከም እንቅስቃሴ በተወሰነ የሚቀንስ መሆኑ እሙን ነው። ለዚህም የበለጠ መሠራት አለበት። ኤርትራ ትናንት የኢትዮጵያ አካል የነበረች፤ ነገር ግን በአፄ ኀይለ ሥላሴ (ልብ በሉ በፌደሬሽን ለመዋሐዷም የሳቸው እና የጸሐፊ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተወልድ እጅ አለበት) እና በደርግ የዲፕሎማሲ ድክመት፤ ብሎም ዓለም የነበረችበትን የቀዝቃዛውን ጦርነት በትክክል በማጤን እንዴት ለራሳችን ልንጠቀምበት እንደምንችል፣ ካልሆነም የማንጎዳበትን መንገድ ባለመፈለጋችን ያጣነው ሕዝብና ምድር ነው። ለዚህ መጥፎ ፖሊቲካ ማስፈጸሚያ ሆኖ ያገለገለው ደግሞ በሻዓብያ፣ በወያኔና በኦነግ የሚመራው የዘውግ ፖለቲካ እና የእንገነጠላለን ጥያቄ ነው። አሁንም ቢሆን ፖለቲካችን በእነዚህ ከፋፋይ የዘር ፖለቲካ አራማጆች ወይም በእነሱ ቡችሎች እየተመራ ነው። ስለዚህም ከኤርትራ ጋር እንደገና የተጀመረው ግንኙነት ዓለም ዐቀፍ ሕጎችን ተከትሎ የኹለቱንም አገሮች ጥቅም በሚያስጠብቅ መንገድ በሕግ እንዲመራ ማድረግን ይጠይቃል። አሁንም በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ግንኙነት ትልቁ ትኩረት ማግኘት ያለባቸው የጋራ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፣ የድንበርንም ጉዳይ መፍታት፣ የንግድ ትስስር ስምምነቶች፣ የመሰረተ ልማት ግንባታ ውሎች፣ እና የወደብ አጠቃቀም መርሆች ዓለም ዐዓቀፍ ሕጎችን ተከትለው በጥንቃቄ ሊከናወኑ ይገባል።

ኢትዮጵያን ጠንካራ ያደረጓትን ሁሉ በማንነት ፖለቲካ አማካኝነት እያሳጡን ነው። አሁን ደግሞ የእስላማዊ ባንክ ይመስረት ይሉናል። ከተቻለ ማፍረሱ፣ ያለዚያ ማድከሙ እንዲቀጥል። የእስላማዊ ባንክ ምስረታን መንግሥት እንደሚደግፍ ገልጿል። ለኢትዮጵያዊያን እስላም ወገኖቻችን ታስቦ ከሆነና ጥቅሙ ከጉዳቱ ካመዘነ ጥሩ ነው። እኔ እንደ አንድ ኢትዮጵያ ዜጋ ግን የአረቦችን እጅ አገራችን የሚያስገባና የብሔሩን ልዩነት ሳንወጣው ተጨማሪ የሃይማኖት ልዩነት መሠረት ያደረገ የኢኮኖሚና የሥልጣን ሽኩቻ የሚያስገባና ለአገር ኅልውናና አንድነታችን መደፍረስ መንስኤ የሚሆን ነገር ነውና ይታሰብበት እላለሁ። መንግሥትም ላለበት ጊዜያዊ ችግር መፍትሔ መፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ የሚያደርገው ውሳኔ የረዥም ጊዜ ውጤትን ማስላትም አለበት። ከዚህ አንፃር ስህተት የሠራ ለመሆኑ ጥርጥር የለውም። የእስላማዊ ባንክን መቋቋም የሚፈልጉ ሰዎች፣ የሚጽፉት ሁሉ ውሃ የማይቋጥርና የሚያቀነቅኑት ጉዳይ አገርን ከገባንበት የዘውጌ ፖለቲካ ተጨማሪ፣ የሃይማኖት መሠረት ያለው ፖለቲካ በአገር ላይ ለመጫን የታሰበ ነው። ይህንም የአረብ መንግሥታት ዓላማ፣ የኢራን ተፅዕኖ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ እንዳይሰፋ መከላከል እንጂ፣ የሃይማኖት እጅ የለም ብለው ይከራከራሉ። ይህ ዓይናችሁን ተጨፈኑ ላሞኛችሁ ካልሆነ ሌላ አይሆንም። እስላማዊ አገር እስልምናን መሣሪያ አድርጎ አይጠቀምም ብሎ መከራከር ጅልነት ነው። እንዲያውም ዋናው ግጭት መነሻ የሱኒና ሸአ እስልምና ልዩነትና የበላይነት ለመያዝ የሚደረግ እሽቅድድም ነው። ለአገር የሚያስብ ሁሉ ይህን ሒደት ሊቃወምና ከሚመጣው ችግር አገሩን ሊታደግ ይገባል። እስላሙ ወገናችንም ያለወለድ የሚያደርገውን የኢትዮጵያዊ ባንኮች መጠቀሙን መምረጡ የተሻለነው፤ ዛሬ የምናገኘው፣ ነገ ከምናጣው ይበልጣልና።

በተጨማሪም የሶማሌ ክልል አሁን ባለው ጂኦ-ፖለቲክስ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ክልል ነው። በተለይም በአሜሪካ የሚደገፈው የሳዑዲ፣ የግብፅ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬት፣ የባሕሬን ቡድን በራሺያ ከሚደገፈው የቱርክ፣ የኢራን፣ የካታር ቡድን ጋር ከሚያደርገው ሽኩቻ አንፃር በደንብ ሊታሰብበትና የመፍትሔ ሐሳቦች፣ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ሊዎጡለት ይገባል። የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠንከር፣ በፌዴራል መንግሥቱ ያላቸውን ተሳትፎ ማጠንከር፣ ኢሕአዴግና አጋር ድርጅቶች አንድ ወጥ ፓርቲ እንዲሆን መሥራት፣ የአገራችን ችግሮች ከምንፈታባቸው ቁልፎች ተጨማሪ ሆነው ሊያገለግሉ የሚችሉ መፍትሔዎች ናቸው። ሕገወጥ የመሣሪያ ዝውውርም የአገራችን አንድነት፣ ሰላምና ደኅንነታችን አንዱ አደጋ እየሆነ ነው። የመሣሪያው ምንጭ የራሳችን ሚሊታሪ፣ ከምሥራቅ አውሮፓና ከማይነር ኤዥያ(ቱርክ) መሆኑ እየተነገረ ነው። ስለዚህም መንግሥት ቁጥጥሩን ያጠንክር፣ የውጭ አገራትን የችግሩ መንስኤነት ያስቁም።

እነዚህን ችግሮች ለመፍታት በጥንቃቄ አስበን ካልተንቀሳቀስን፣ ለአገራችን ሰላምና አንድነት፣ ብሎም ዕድገቷ ጸር ሊሆኑ ስለሚችሉ፤ መደረግ ያለበትን እናድርግ።

መላኩ አዳል የዶከትሬት ዲግሪ በባዮ ሜዲካል ሳይንስ በማጥናት ላይ ናቸው።
በኢሜል አድራሻቸው melakuadal@gmail.com ሊገኙ ይችላሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here