የሚዲያው ዘውጌ’ነት …!?

0
807

ቁምላቸው አበበ በኢትዮጵያ የሚገኙ በተለይ በፌደራል መንግሥቱም ሆነ በክልል መንግሥታት ሥር የሚተዳደሩት መገናኛ ብዙኀን ዘውገኝነት የተጠናወታቸው በመሆኑ ከተቋቋሙለት ዓላማ ማለትም ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማጎልበት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ከማቅረብ አፈንግጠው ጥላቻን፣ ልዩነትንና አክራሪ ብሔርተኝነትን በመቀስቀስ አገሪቱን ወደለየለት የቀውስ ቁልቁለት እያንደረደሯት ይገኛል ሲሉ ይሞግታሉ። በመሆኑም መገናኛ ብዙኀኑ ከማንነት፣ ከጎሳ፣ ከዘውግ አሰላለፍ ራሱን ነፃ በማድረግ የአገሪቱን መፃኢ ዕድልና ፖለቲካዊ ሐቲት መበየን ላይ ማተኮር ይጠበቅባቸዋል በማለት በዓለማቀፍ ደረጃ ያለውን ተሞክሮን በተለይም የአፍሪካዊቷን ሩዋንዳ እንደአብነት በማሳያነት አንስተዋል።

እንደ ማንኛውም ሙያ ጋዜጠኝነት ዘር፣ ጎሳ፣ ዘውግ፣ ብሔር፣ ዜግነት፣ ሃይማኖት፣ ጾታ የለውም። ጥቁር፣ ነጭ፣ ስፓኒክ፣ ቢጫ፣ ቡናማ፣ ኤስያ፣ ጋዜጠኝነት የለም። ክርስቲያን፣ እስላም፣ ይሁዲ፣ ሒንዱ፣ ቡድሀ፣ ሽንዙ፣ …፤ ጋዜጠኝነት የለም። ወንድ፣ ሴት፣ ፍናፍንት ጋዜጠኝነት የለም። አዎ! ጋዜጠኝነት ሁለንተናዊ ነው። አዎ! ጋዜጠኝነት ሰውነት፣ ጋዜጠኝነት እውነት ነው። ሆኖም በዓለማችን፣ በአሕጉራችን፣ በአገራችን ዘውግን፣ ዘርን፣ ጎሳን …፤ መሰረት አድርገው የተቋቋሙ፣ የሚሠሩ ሚዲያዎች ግን እንደ አሸን እየፈሉ፣ አሳሳቢ እየሆኑ መጥተዋል።

የነፃነት፣ የዲሞክራሲ ከፍታ ተምሳሌት ሆና በምትታየው አሜሪካ ሳይቀር የጥቁር፣ የነጭ አክራሪ፣ የስፓኒክ፣ የአይሁድ፣ የድሃ፣ የመካከለኛ ገቢ፣ የባለፀጋ ወገንተኝነት የሚታይባቸው መደበኛና ማኅበራዊ ሚዲያዎች አሉ። እነዚህ ሚዲያዎች ዜናዎቹን፣ ፕሮግራሞቹን፣ የሕዝብ አስተያየቶችን፣ ርዕሰ አንቀፆችን፣ ትንታኔዎችን፣ አቋማቸውን …፤ የሚቀርፁት፣ የሚያስመለክቱት ከእውነትና እውነት አንፃር ብቻ ሳይሆን ከቆሙለት ማንነት ጥቅምና ፍላጎት አኳያም ጭምር ነው። ሲኤንኤን፣ ኤንቢሲ፣ ኤቢሲ፣ ፎክስ ኒውስ፣ ኒው ዮርክ ታይምስ፣ ዋሽንግተን ፖስት፣ ፖሊቲኮ፣ ኤፒ ዜናን፣ ኹነትን የሚያሳዩበት መንገድ ከቆሙለት ማንነት፣ መደብ፣ ፖለቲካ ኢኮኖሚ ወይም ለእውነት ካላቸው ውግንና አልያም ለዜጋ፣ ለአገር ካላቸው ጥብቅና ሊነሳ ይችላል።

አንድ ሰሞነኛ አስረጅ እናንሳ፦ ዶናልድ ትራምፕ በ2016 ምርጫ ሂላሪን ለማሸነፍ ከሩሲያ ጋር በማሴርና የፍትሕ ሒደትን በማደናቀፍ ተጠርጥረው፤ በሮበርት ሙለር የሚመራ ልዩ ምክር ቤት ተቋቁሞ ላለፉት 22 ወራት ምርመራ ሲያደርግ ቆይቶ ሰሞኑን ይፋ ያደረገውን ድምዳሜ፤ ፎክስ ቴሌቪዥን የምርመራ ውጤቱን ለትራምፕ፣ ለሪፐብሊካኖችና ለደጋፊዎች ከሰማይ እንደ ወረደ ድልና ነፃነታቸውንም ያረጋገጠ አድርጎ ሲዘግበው፤ ሲኤንኤን ግን ምርመራው የደረሰበትን ውጤት ግልፅነት የጎደለውና አወዛጋቢ አድርጎ ለማሳየት ጥረት እያደረገ ነው።

በተመሳሳይ ሁኔታ በዓለማችን ላለፉት ኹለት ዓመታት ዋና መነጋገሪያ ሆኖ የዘለቀው እንግሊዝ ከአውሮፓ ሕብረት የመውጣት፣ የመነጠል ጉዳይ ብሬግዚትን፤ ቢቢሲ እና ስካይ ኒውስ፤ ዴሊ ቴሌግራፍ፣ ዴሊሜል፣ ዘ ጋርዲያን እንዲሁም የአሜሪካ ሚዲያዎች የዘገቡበት አግባብ፤ ከግራ ዘመም እና ከቀኝ አክራሪ ወይም ከሌበር እና ከቶሪ ፓርቲ አልያም ከሉላዊነት እና ከሕዝበኝነት ከፍ ሲልም ከኹለትዮሽ ከዚህ በላይ multilateral የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ አንፃር በመቃኘት ነው።
የኅትመትም ሆነ የማኅበራዊ ሚዲያ አተያይም ከፍ ሲል የተመለከትነውን አሰላለፍ የሚከተል ሆኖ እናገኘዋለን።

ሁሉም ዓለማቀፍ ሚዲያዎች በሚያስብል ሁኔታ የእስራኤልንና የፍልስጤምን ጉዳይ የሚዘግቡት ከየአገራቱ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ፣ ከሚከተሉት ዕምነት እና ከሚያራምዱት ርዕዮተ ዓለም አኳያ መሆኑን መናገር የአዋጁን በጆሮ ያደርገዋል። እነ አል ጃዚራ፣ ፕረስ ቲቪ፣ ቲአርቲ ወርልድ በአንድ በኩል እነቢቢሲ፣ ሲኤንኤን፣ ስካይ ኒውስ፣ ኤንቢሲ ተመሳሳይ በሆነ የእስራኤልና የፍልስጤም ጉዳይ፣ ኹነት የሚዘግቡበት አግባብ ፍፁም የተለያየ ነው። ከላይ የተመለክትናቸው የእስልምና አገራት የቴሌቪዥን ጣቢያዎችም ሆኑ ሌሎች ሚዲያዎች በፍልስጤም ጉዳይ አንድ ሆነው ሲያበቃ የሽያና የሱኒ ጉዳይ ሲዘግቡ ደግሞ ሆድና ጀርባ ሆነው ያርፉታል፤ ወደ የሃይማኖት ፈለፈላቸው (shell) ይገባሉ።

እነዚህ አብነቶች ሚዲያዎች እውነትንና እውነትን ብቻ አልያም የተመልካች፣ አድማጭና አንባቢ ፍላጎትን ብቻ እንደማያንፀባርቁ ያሳያሉ። ከዚህ ይልቅ ለየራሳቸው ፖለቲካል ኢኮኖሚ፣ ለባለቤቶቻቸው ፍላጎት የመገበር አባዜ እንደሚስተዋልበቸው ያረጋግጣል። የእነዚህ ሚዲያዎች ባለቤት ግራ ዘመም፣ ቀኝ አክራሪ፣ ሕዝበኛ፣ ጥቁር፣ ሽያ፣ ሱኒ፣ ዘረኛ … ፤ ከሆነ የየሚዲያዎች አርትዖት የሚከተለው ይሔንኑ ፈለግ ነው። ለዚህም ነው የሚዲያዎች ነፃነት፣ ገለልተኝነት አወዛጋቢና አንፃራዊ የሚሆነው። ሆኖም ሚዲያዎች ፈር ሲስቱ፣ ከሙያው ሥነ ምግባር ሲያፈነግጡ፤ የሚተቹ፣ አደብ የሚያሲዙ፣ የሚገስፁ፤ ጠንካራ የሙያ ማኅበራት፣ የሕግ ስርዓት፣ አሰላሳዮች፣ ከሁሉም ሚዲያዎች እርስ በርስ የመተራረም፣ የመተቻቸት ባሕል ማጎልበታቸው ችግሮች ከአቅም በላይ እንዳይሆኑ አስችሏል።

በምዕራባውያን ዘንድ ይህ የሚዲያዎች የአሰላለፍ ህፀፅ፣ ነውር ከዚህ አልፎ በሕዝቡ አስተሳሰብ ላይ አሉታዊም፣ አዎንታዊም ተፅዕኖ የሚያስከትል ከሆነ፤ መንግሥቶቻቸው ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቋማት እንዲሁም ሕግ አውጭውን፣ ተርጓሚውንና አስፈፃሚውን አሠራር መቆጣጠሪያና ሚዛን ጠባቂ (Check and balance) ስላለው የሚፈጥረው ጫና ያን ያህል ነው።

በማደግ ላይ ባሉ አገራት በተለይ በአሕጉራችን ቅኝ ገዥዎች ከፋፍሎ ለመግዛት ያመቻቸው ዘንድ በጎሳዎች/በዘውጎች ፣ በሃይማኖቶች መካከል የተነዙት የልዩነት፣ የጥላቻ ትርክት፤ እዚህ ላይ ጣሊያን በአገራችን አማራውን ከትግሬ፣ ኦሮሞውን ከአማራው፣ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ከእስልምና፣ ለመነጠልና ለመከፋፈል የሔደበትን እርቀት ያስታውሷል። ከነፃነት በኋላ የአፍሪካውያኑ ሆኑ የሌሎች ቅኝ ተገዥ አገራት ልኂቃን፤ ወደ ሥልጣን ለመውጣትም ሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ የበላይነታቸው በማስጠበቅ አገዛዝ ላይ ለመቆየት፤ የቅኝ ገዥዎችን ከፋፍሎ የመግዛት ስልት በመጠቀም ይቆጣጠሯቸው በነበሩ ሚዲያዎች ሕዝባቸውን ለመለያየት ለመከፋፈል ተግተዋል።

የጀርመንና የቤልጂየም ቅኝ ገዥዎች ከፋፍሎ ለመግዛት እንዲመቻቸው በሩዋንዳና በብሩንዲ በሚኖሩ በብዙኀኑ የሁቱ፣ በህዳጣኑ የቱትሲና የታዋ ጎሳዎች መካከል የዘር ልዩነትን ሰብከዋል፤ ሁቱዎችን ከእናንተ ይልቅ ከግብፅና ከአብሲኒያ እንደ መጡ የሚነገርላቸው ቱትሲዎች እና ታዋዎች በውበትም በአስተሳሰብም ይበልጧችኋል ይሏቸው ነበር፤ ሁቱዎችም የበታችነት ስሜት ተፈጠረባቸው፤ እያደር ይህ ስሜት ወደ ጥላቻ፣ ወደ ቂም አደገ። በተለይ ቤልጂየም በዚህ ሳታበቃ የሕዝብ ቆጠራ በማካሔድ ዘውግን የሚገልፅ መታወቂያ በማደል ልዩነቱን ተቋማዊ፣ ስርዓታዊ አደረገችው፤ ይሄን ተከትሎ በሦስቱ ጎሳዎች መካከል ለ60 ዓመታት ገደማ የተሰበከው ጥላቻ፤ ከ2ኛው የዓለም ጦርነት በኋላ፤ በ20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በዓለማችን እጅግ ዘግናኝ ለሆነው ለ1986 የሩዋንዳ ዘር ፍጅት አንዱና ዋነኛው መግፍኤ ሆኖ ይጠቀሳል። በዚህ 800 ሺሕ ቱትሲዎችና ለዘብተኛ ሁቱዎች በግፍ ተጨፍጭፈዋል። በዚህ የዘመኑ ዘግናኝ የዘር ጭፍጨፋ አክራሪ የሁቱ ሚዲያዎች በዕቅድ፣ በስልት ከፊት ሆነው ተሳትፈዋል። በተለይ አንዳንዶቹ ጭፍጨፋው በመተፈፀመባቸው ተከታታይ 100 ቀናት በቀጥታ ስርጭታቸው፤ “መቃብሩ ገና አልሞላም ፣ ይቀረዋል። እነዚህን በረሮዎች (ቱትሲዎች) ከእነግብረ አበሮቻቸው (ለዘብተኛ ሁቱዎችን መሆኑ ነው፤) መጨረስ ይገባል” ሲሉ ቀስቅሰዋል።

በተለይ አርቲኤልኤም (RTLM) እና ራዲዮ ሩዋንዳ በቱትሲዎችና በለዘብተኛ ሁቱዎች የጥላቻና የዘረኝነት መልዕክቶችን በማስተላለፍ የዘር ማጥፋቱን አነሳስተዋል፤ መርተዋል፤ አስፈፅመዋል። እዚህ ላይ ሳይነሱ መታለፍ የሌለባቸውን ኹለት የታሪክ ጠባሳዎችን ላንሳ። አፈር ይቅለላቸውና የመጀመሪያው በኮፊ አናን ዋና ፀሀፊነት ይመራ የነበረው፤ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤቱም ሆነ የሰላም አስከባሪ ጭፍጨፋውን ማስቆም እየቻለ፤ አይቶ እንዳላየ፣ ሰምቶ እንዳልሰማ ማለፉ፤ ጅብ ከሔደ ሆነ እንጅ፤ ኮፊ አናን ጭፍጨፋውን ለማስቆም የመንግሥታቱ ድርጅት በቂ ጥረት አለማድረጉ የአመራራቸው ትልቁ ጥፋት አርገው ከመቀበል አልፈው፣ ሁል ጊዜ እንደሚፀፀቱ ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይናገሩ ነበር። ዓለማቀፉ ሚዲያውም የዘር ማጥፋት ዘመቻውን ቀድሞ ለመከላከልም ሆነ ለማስቆም ግንዛቤ ለመፍጠር፣ ለማስጠንቀቅ፣ …፤ ያደረገው ጥረት እዚህ ግባ የማይባልና ደካማ ከመሆኑ ባሻገር፤ ግጭቱ በኹለት ተመጣጣኝ ጎሳዎች መካከል እንደሚካሄድ ተራ የእርስ በእርስ ግጭት አድርጎ አዛብቶ አሳይቷል። ለዚህ ነው በተለይ ሩዋንዳውያን ዛሬ ድረስ፤ የወቅቱ የአፍሪካ አንድነት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅቶችን ጨምሮ፤ እንዲሁም ዓለማቀፉ ማኅበረሰቡ፣ ሚዲያው፣ ምዕራባውያን “ከድተውናል!” ሲሉ የሚደመጡት፤ በአንድ አገር፣ መንግሥት፣ ዜጋ፣ …፤ ሚዲያ የሚጫወተውን የማይተካ ሚና ለመግለፅ 4ኛው መንግሥት በመባል ይታወቃል። ከአሜሪካ ቀደምት ፕሬዝዳንቶች አንዱ “…ሚዲያ ከሌለው መንግሥት ይልቅ፤ መንግሥት የሌለው ሚዲያ ይሻለኛል።” ማለታቸው፤ ሚዲያ ከመንግሥት የሚመረጥበት፣ የሚበልጥበት አጋጠሚም እንዳለ ያሳያል። ሚዲያዎች ለዴሞክራሲያው ስርዓት ግንባታ ይሔን ያህል የማይተካ ሚና እንዳላቸው ቢታመንም፤ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሚዲያዎች በሕዝቦች፣ በአገራት፣ በጎሳዎች መካከል ጥላቻን፣ ልዩነትን በማራገብ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባትንም ሆነ አገርን አደጋ ላይ በመጣል ይከሰሳሉ፤ እዚህ ላይ በ1998 በኬኒያ የተካሔደውን ድኅረ ምርጫ አገራዊ ቀውስ በዋቢነት ማንሳት ይቻላል።

በራይላ ኦዲንጋ፣ ሎውና በሞይ ኪባኪ ኪኩዩ ጎሳዎች መካከል ግጭቱን ያባብሱ የነበሩት፤ የእነዚህን መሪዎች ጎሳ ተገን አድርገው የተቋቋሙ ሚዲያዎች እንደ ነበሩ ይወሳል። የፖለቲካ መሪዎች የየጎሳዎችን ድምፅ ለማግኘት እነዚሁን ሚዲያዎች መጠቀማቸው በእንቅርት ላይ እንዲሉ ሆኗል። በመጨረሻ ፖለቲካውም ፣ ሚዲያውም ዘውጌያዊ ሆኖ አረፈውና ጎረቤታችን ኬኒያ ማጣፊያው ሲያጥራት ከአንድ ኹለት ሦስቴ በላይ ተመልከተናል።

የአገራችን ሚዲያ ጉዳይ?!
ዛሬ በአገራችን ሰማይ ሥር ያንዣበበው የሥጋት ዳመና የራሱ ዓውድ ያለው ቢሆንም ከሞላ ጎደል ከኬኒያ ጋር ተመሳሳይነት አለው። ባለፈው አንድ ዓመት የፖለቲካ ምኅዳሩን መስፋት ተከትሎ፤ በሐሳብ፣ በርዕዮተ ዓለም ከተመሰረተው የፖለቲካ እንቅስቃሴ ይልቅ፤ በማንነት፣ በዘውግ ላይ የተመሰረተው ፖለቲካ፣ ማንነትን እየተላበሰ በመጣው መደበኛና ማኅበራዊ ሚዲያ እየታገዘ አገሪቱን ወደ ለየለት ቀውስ እንዳይዘፍቃት ያሰጋል። በተለይ የሚዲያዎች ፖለቲካ ኢኮኖሚ፤ በማንነት፣ በዘውግ ማጠንጠኛነት መዋቀር ከጊዜ ወደ ጊዜ አደጋውን አሳሳቢ አድርጎታል። በተለይ የየክልሎችን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ለማጎልበት በአፍ መፍቻ ቋንቋዎቻቸው (vernaculars) የተመሰረቱ ሚዲያዎች፤ ከተቋቋሙለት ዓለማ በማፈንገጥ፤ ባለፈው አንድ ዓመት ራሳቸውን ወደ ዘውግ፣ ማንነት ሚዲያነት ቀይረው ጥላቻን፣ ልዩነትን፣ አክራሪ ብሔርተኝነትን፣ ማንአህሎኝነትን፣ እብሪትን፣ ግጭትን፣ በመለፈፍ፣ በመስበክ፣ በመቀስቀስ አገሪቱን ወደ ለየለት የቀውስ ቁልቁለት እያንደረደሯት ይገኛል። የጋዜጠኝነት የማዕዘን ራስ የሆነው ለእውነት የመወገን፣ ለዜጋ ተጠያቂ የመሆን፣ የጋዜጠኝነት መሰረታዊ አላባውያን፣ …፤ ተረስተው፤ ሚዲያው በማንነት ላይ የተመሰረተውን፣ የተቃኘውን ፖለቲካ ተከትሎ ዘውጌያዊ መሆኑ አሁን አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

የኦሮሞ፣ የአማራና የትግራዋይ ማንነቶች ላይ የተንጠለጠሉ ሚዲያዎች እንደ አሸን እየፈሉ ነው። ዛሬ እውነትን፣ የአገርን፣ የዜጋን ጥቅም፣ የሙያውን ሥነ ምግባር ከማስቀደም ይልቅ ጎሳን፣ ማንነትን በማጉላት በገዥው የፖለቲካ ግንባርም ሆነ በአጋር ድርጅቶች መካከል መጠራጠርን፣ ደባን፣ ሴራን ከማንበር፣ ከመጎንጎን አልፎ በዜጎች መካከል ግጭትን እያቀጣጠሉ አገሪቱን ወደ ለየለት ቀውስ እየገፏት ነው።

አንዳንድ የግል ሚዲያዎችም ገለልተኛና ነፃ መሆን ሲገባቸው የተቃዋሚ፣ የተፎካካሪ ፖለቲካ ጭፍራ መሆናቸው ሳያንስ ዘውጌያዊ መሆናቸው ችግሩን አሳሳቢ ያደርገዋል። የፌደራል መንግሥቱ ሚዲያዎች ገለልተኛ ሆነው ለአገር፣ ለዜጋ፣ ለእውነት፣ … ፤ጥብቅና በመቆም ተመራጭ፤ ለክልሎችም ሆነ ለግል ሚዲያዎች አርዓያ መሆን ሲገባቸው፤ በተለይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ኢቢሲ) የአርትዖት ኮሚቴ ስብሰባዎች፣ ውሳኔዎች ሳይቀሩ ከጋዜጠኛው ማንነት እና ከሚደግፈው የፖለቲካ ድርጅት አንፃር እየተቃኙ መሳሳቦች፣ አለመግባባቶች መኖራቸውን ስንሰማ መደንገጣችን አልቀረም። ክፍፍሉ የኢሕአዴግ አባል ድርጅቶችን ማንነት የተከተለ መሆኑን በዚያ ሰሞን ለንባብ በበቃ አንድ ጋዜጣ ላይ ተመልክተናል። በኤዲቶሪያል ስብሰባዎች የአንድ ዜና፣ ኹነትና ዝግጅት የሚመዘነው በጋዜጠኝነት መሰረታውያን ሳይሆን ከጋዜጠኛው የማንነት አሰላለፍ አንፃር እስከ መሆን መድረሱ በእጅጉ ሊያሳስበን ይገባል።

የየክልሎች የሚዲያ አጠቃቀምም ከዚህ የከፋ ነው ማለት ይቻላል። ቀደም ሲል የሶማሌ እና የኦሮሚያ መገናኛ ብዙኀንና ቃል አቀባዮቻቸው ይለዋወጧቸው የነበሩ መወነጃጀሎችን፤ የትግራይ እና የአማራ ቴሌቪዥኖችን ከእነቃል አቀባዮቻቸው የሚያስተላልፏቸውን ብሽሽቆች፤ የኦቦ ጃዋሩ ኦኤምኤን የሚያስተላልፋቸው ዋልታ ረገጥ ሐሳቦችና ከኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት አቀንቃኞች ጋር የገባው እልህ፤ ይሔን ከእግር ከእግር እየተከታተለ ለማቃናት የሚታትረውን ኢሳት እንደ አብነት መውሰድ ይቻላል። ወደ ፋና ቴሌቨዥን ስንመጣ ግን የዘውጌያዊነት አሰላለፉ በግልፅ የሚታይ ባይሆንም ከዚህ ክስ ግን ነፃ ነው ማለት አይደለም።

ጋዜጠኛ ተመስገን ገብረሕይወትን ከኦሮሚያ አምጥቶ ከሾመ በኋላ በዚያ ሰሞን በተለይ የኦዴፓን አመራሮች፣ የኦሮሞኛ ተናጋሪ የፌደራል የሥር ኀላፊዎችን ብቻ እየመረጠ ቃለ መጠይቅ ማድረጉ፤ አንድ ጓደኛዬ የሚያነሳውን ጥያቄ እንድጋራ አስገድዶኛል። “ኦዲፒ በፋና ጽሕፈት ቤቱን ከፈተ እንዴ!?” መልሱን ለፋና ትቸዋለሁ፤ ሆኖም ይህ የሚዲያ የዘውጌያዊነት አባዜ፣ አደጋ ያላንኳኳው የፌደራል፣ የክልል ሚዲያ የለም ለማለት ማረጋገጫ ጥናት ቢጠይቅም ወረርሽኙ በፍጥነትና በሥፋት እየተዛመተ መሆኑን ግን መካድ አይቻልም ።

ሚዲያው ከዚህ የዘውጌያዊነት አደጋ እንዲወጣ፤ በድፍረት፣ በሃቀኝነት፣ በሚዛናዊነት፣ በገለልተኝነት፣ በተጨባጭነት ላይ ተመሰረቶ የሕዝቡን ጉድፍ፣ ህፀፅ ማሳየት፣ መንቀስ፤ የመወያያ፣ የመነጋገሪያ አጀንዳ መቅረፅ፣ መድረክ መፍጠር፤ መንግሥትን ተጠያቂ ማድረግ እና የሕዝብ ድምፅ ለመሆን የሚያስችለውን መደላድልና አሰራር በባለድርሻ አካላትና በራሱ በጋዜጠኛው ትብብር ሊያበጅ ይገባል።

ሚዲያው ከማንነት፣ ከጎሳ፣ ከዘውግ አሰላለፍ ራሱን ነፃ በማድረግ የአገሪቱን መፃኢ ዕድልና ፖለቲካዊ ሐቲት መበየን ላይ ማተኮር ይጠበቅበታል። ይህን ኀላፊነቱን ለመሸከም የሚያስችለውን የአቅም ግንባታ ሥራ፤ በተለይ ግጭትን በመከላከልና በመፍታት ላይ አትኩሮ ሥልጠናዎችን ማዘጋጀት እና ውስጣዊ አሰራሩን ለመቆጣጠር የሚያግዙ ስልቶችን መንደፍ ይጠበቅበታል።

የፖለቲካ ፓርቲዎችን የሚዲያ አጠቃቀም የሚወስን አንቀፅ ባለፈው ከስንት ውርክብ በኋላ በተፈረመው ቃል ኪዳን ሰነድ እንደተካተተው ሁሉ ሚዲያውን ከዘውጌያዊነት፣ ከዘረኝነት የሚታደግ አንቀፅ እየተሻሻለ ባለው የፕሬስ ሕግ በግልፅና በማያሻማ ሁኔታ ማካተት ይገባል።

ከዚህ ጎን ለጎን በቅድሚያ የመንግሥትን በማስከተል የግል ሚዲያዎችን ኀላፊዎችና ጋዜጠኛው እንዲሁም የሥራ አመራር ቦርድ ከማንኛውም ተፅዕኖ ነፃ ማድረግ ያስፈልጋል።

ከሁሉም በላይ ግን በቀጣይ፣ በሒደት የፖለቲካ ፓርቲዎች ከማንነት፣ ከዘውጌ ፖለቲካ ወደ ርዕዮተ ዓለም ልዕልና የሚሸጋገሩበትን መንገድ መምራት፣ ማመላከት ላይ በትጋት መሥራት የግድ ነው።

ቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን) በጋዜጠኝነት ሙያ ላይ የተሰማሩ ባለሙያ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው fenote1971@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here