በዐቃቤ ሕግ የሚቋረጡ ክሶችን የሕግ ባለሙያዎች ተቃወሙ

0
825

የመንግሥትን ሥራ በማያመች አኳኋን በመምራት በመንግሥት ላይ ከ11.9 ሚሊዮን ብር በላይ ጉዳት በማድረስ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ከአንድ ዓመት በፊት ተመሥርቶባቸው የነበሩት የቀድሞ የአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፀዳለ ማሞን ጨምሮ የአራት ኀላፊዎች ክስ ተቋርጦ ከእስር የተፈቱት ኅዳር 2011 ነበር።

ተከሳሾቹ ፀዳለ ማሞ፣ የጽሕፈት ቤቱ የሎጂስቲክስ አስተዳደርና ፋይናንስ መምሪያ ኀላፊ የነበሩት የማነ ፀጋዬ፣ የመሬት ዝግጅት መሠረተ ልማትና ዲዛይን መምርያ ረዳት መምርያ ኀላፊ የነበሩት ሳባ መኮንንና የፕላንና ዶክመንቴሽን አገልግሎት ኀላፊ የነበሩት ሽመልስ ዓለማየሁ ናቸው።

ተጠርጣሪዎቹ የጽሕፈት ቤቱ የማኔጅመንት ኮሚቴ አባል ሆነው ሲሠሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የዕቃና አገልግሎት ግዥ መመርያ ቁጥር 4/1991 አንቀጽ 6(2) እና አንቀጽ 25 በመተላለፍ ከተፈቀዱ የግዥ ዘዴዎች ውጪ እንዲፈጸም ጨረታ ማውጣታቸውን ዓቃቤ ሕግ በፍርድ ቤት የመሠረተባቸው ክስ ያስረዳል።
በመሆኑም የማይገባ ጥቅም ለማግኘት በማሰብ ከየማነ ግርማይ ጠቅላላ ሥራ ተቋራጭ ጋር በመመሳጠር፣ የአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን ያወጣውን ጨረታ እንዲያሸንፍና ግዥው እንዲፈጸም በማድረግ ጉዳት እንዲደርስ ማድረጋቸውንም ክሱ ያብራራል። ለአፈር ቆርጦ መጣል፣ ለገረጋንቲ ማጓጓዣና ለገረጋንቲ መሙላት 33,384,526 ብር ግዥ መፈጸሙንም ጠቁሟል። ይኼ ዋጋ የተከፈለው ሌሎች ተጫራቾች ካቀረቡት ዋጋ በላይ እጅግ በተጋነነና ከ80 እስከ 120 በመቶ ጭማሪ በማድረግ መሆኑንም አክሏል።

በአጠቃላይ ተከሳሾቹ የ11,979,848 ብር ጉዳት በመንግሥት ላይ አድርሰዋል በማለት ዓቃቤ ሕግ ክስ መሥርቶባቸውና ዋስትና ተከልክለው ሲከራከሩ የከረሙ ቢሆንም፣ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ክሳቸውን ኅዳር 19/2011 እንዳቋረጠላቸው ይታወቃል።

ዓቃቤ ሕግ በወቅቱ በሰጠው መግለጫ ክሱን ያቋረጠላቸው ተከሳሾቹ በመንግሥት ላይ ያደረሱትን 11,979,848 ብር በመክፈላቸው መሆኑን ገልጿል። ዓቃቤ ሕግ ክሱን ማቋረጡን ያስታወቀው በሌሉበት ክስ ተመሥርቶባቸው ጥፋተኛ በተባሉት የማነ አብርሃ፣ ወንድወሰን ደምረውና ሲሳይ በቀለን ጨምሮ ቢሆንም፣ የሦስቱን ተከሳሾች ክስ መቋረጥ ፍርድ ቤቱ አልተቀበለውም ነበር። ዓቃቤ ሕግ ክስ የማቋረጥ ሥልጣን ቢኖረውም ከፍርድ በፊት መሆኑን ጠቁሞ፣ በሦስቱ ላይ የጥፋተኝነት ፍርድ በመሰጠቱ እንደማይችል በመጠቆም ቅጣት ጥሎባቸዋል። በመሆኑም እያንዳንዳቸው በስድስት ዓመታት ጽኑ እስራትና 20,000 ብር እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል። የፌዴራል ፖሊስም ፍርደኞቹን አፈላልጎ በመያዝ ለማረሚያ ቤት እንዲያስረክብ ትዕዛዝ መሰጠቱም ይታወሳል።

በተመሳሳይ በሐምሌ 2009 በቁጥጥር ሥር ከዋሉ በኋላ ከባድ የሙስና ወንጀል ክስ ቀርቦባቸው ለ17 ወራት በእስር ላይ ሆነው ሲከራከሩ የከረሙት፣ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣንና የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን የተለያዩ የሥራ ክፍል ኀላፊዎች የነበሩ 16 ግለሰቦች ክስ ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ የተሰጠው በያዝነው ዓመት ጥር 2011 ነበር።

ክሳቸው ተቋርጦ ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ የተሰጠላቸው የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር በነበሩት ዚያድ ወልደ ገብርኤል መዝገብ የተካተቱት (የዚያድ ክስ ቀደም ብሎ መቋረጡ ይታወሳል) አብዶ መሐመድ፣ በቀለ ንጉሤ፣ ገላሶ ቦሬ፣ ያንግ ሬንኋ (ያልተያዙ)፣ ኬን ሮበርትስ (ያልተያዙ)፣ ከበደ ወርቅነህ፣ እስክንድር ሰይድ፣ አማረ አሰፋ፣ ደረጀ ኪዳኔ (ያልተያዙ)፣ ገብረአናንያ ፃድቅ ናቸው። ከኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ደግሞ የመተሐራ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ዘነበ ይማም፣ እንዳልካቸው ግርማ፣ ሀየሎም አብዶና በለጠ ዘለለው ናቸው።

ክሱ እንዲቋረጥ የጠየቀው የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6(3ሠ) በተሰጠው ክስ የማቋረጥ ሥልጣን ሲሆን፣ ክሱን ሲመረምርና ሲያከራክር ለከረመው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ ፍርድ ቤቱ የክርክር ሒደቱ እንዲቋረጥ ትዕዛዝ ሰጥቷል። ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክሱ እንዲነሳ ተወስኗል›› በማለት በምክትል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ገለታ ሥዩም ፊርማ በቀረበ ጥያቄ ክሱ ተቋርጦላቸው ከእስር እንዲፈቱ ትዕዛዝ ተሰጥቷል።

ተከሳሾቹ ከመንገድ ግንባታ፣ ከሕገወጥ ጨረታ፣ ከሕገወጥ ግዥና ከሌሎች የወንጀል ድርጊቶች ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ጉዳት በሕዝብና በመንግሥት ላይ አድርሰዋል ተብለው ዝርዝር የክስ ሒደት ቀርቦባቸው እንደነበር ይታወሳል።

ይሁን እንጂ፣ በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው የተከሰሱ ግለሰቦች ገንዘብ ተመላሽ በማድረጋቸው ብቻ ክስ ማቋረጥ አግባብ እንዳልሆነ የህግ ባለሙያዎች ይሞግታሉ።
የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሕግ ጥናት ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት ዐቃቤ ሕግ የሆኑት ሳምሶን ተገኔ፣ የወንጀል ሥነ ሥርዓት ሕጉ ለዐቃቤ ሕግ ክስ የማቋረጥ ስልጣን እንዳልሰጠው በመግለጽ፣ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ ዐዋጅ 943 አንቀጽ 6 ንዑስ አንቀጽ ሰ ላይ ዐቃቤ ሕግ ክስ ማቋረጥ እንዲችል ስልጣን እንደሰጠው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ይሁን እንጂ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ‹‹ለየትኛው ጥቅም?›› የሚለው በግልጽ አለመቀመጡን አውስተው፣ ሕጉ ግልጽ ስላላደረገው በክስ መዝገቦቹ ላይ በመመርኮዝ ክሶቹ እንደሚቋረጡ ተናግረዋል። ዐቃቤ ሕግ ክሱ ይቋረጥ ሲል ፍርድ ቤት የሚቋረጥበት ምክንያት ይብራራልኝ ብሎ የመጠየቅ መብት እንደሌለውም አክለው ገልጸዋል።

ሳምሶን፣ የሙስና ወንጀሎች ላይ የፍርድ ውሳኔ እንዲሰጥ የማድረግ፣ ክስ የማቋረጥና የተመዘበረ ሀብት እንዲመለስ ማድረግ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የተሰጠ ስልጣን እንደሆነ ገልጸዋል።

ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ዐቃቤ ሕግ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የሚቋረጡ አንዳንድ ክሶች የሕዝብንና የአገርን ሀብትና ደህንነት አደጋ ውስጥ የሚጥሉ ናቸው። በዚህም ሳቢያ በርካታ ዐቃቤ ሕጎች ቅሬታ እያሰሙ መሆናቸውንና አንዳንዶቹም ከስራ መልቀቃቸውን ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህሩ ስሜነህ ኪሮስ፣ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ህዝብን የሚጠቅም ውሳኔ የማሳለፍ ስልጣን ቢኖረውም፣ ውሳኔዎቹ ህዝቡ ላይ የተዛባ አመለካከት እንዳይፈጥሩ በግልጽ ማሳወቅና በጥንቃቄ ተግባራዊ ማድረግ እንዳለበት መክረው፣ አንዳንድ ማስተማሪያ የወንጀል ክሶችን ማቋረጥ መማሪያነታቸውን እንደሚያሳጣቸው ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

በተመሳሳይ ጥር 17/2011 ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በቁጥር አ.አከፅ/01/01/42 በተጻፈለት ደብዳቤ፣ የአዲስ አበባ ግብር ከፋይ ሆነው ጉዳያቸው በፖሊስና በአቃቤ ሕግ እጅ የሚገኙ ክሳቸው እንዲቋረጥ፤ ፍርድ የተሰጠባቸውም በምህረት እንዲለቀቁ በማለት የ1640 ግብር ከፋዮች ዝርዝር ቀርቦለት ከነዚህ ውስጥ 1077ቱን እንዲቋረጥ ማድረጉ ይታወሳል።

ተከሳሾቹ መደበኛ የኮንትሮባንድ ወንጀሎች ማለትም፣ ደረሰኝ ሳይዙ ወይም ዲክላራሲዮን ሳይኖራቸው የተለያዩ ዕቃዎች በንግድ ሱቃቸው የተገኘባቸው ናቸው። በተጨማሪም፣ የባለሥልጣኑን ሥራ ማሰናከል ወንጀልና ከሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ አድራሻ ጋር የተፈጸሙ ጥፋቶች መሆናቸውንም የክስ መዝገቡ ያትታል።
ዐቃቤ ሕግ እነዚህ ወንጀሎች ከአፈጻጸማቸው፣ ከያዙት የገንዘብ መጠን አነስተኛ መሆን፣ እንዲሁም ከተያዘው የኢኮኖሚና የታክስ ሪፎርም እና ከግለሰቦቹ የኢኮኖሚ አቅም አንጻር በምርመራም ሆነ በፍርድ ቤት ደረጃም ያሉ በሙሉ እንዲቋረጡ ወሰኗል።

‹‹በመንግስትና በሕዝብ ጥቅም ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዝቅተኛ በመሆኑ ክሳቸው ተቋርጦ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ቢገቡ ለመንግስትና ለሕዝብ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ያቀረባችሁትን ጥያቄ በመቀበል ክሳቸው እንዲቋረጥ ወስነናል›› ሲል ክሱን ማቋረጡ ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ መምህር የሆኑት ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር) ክስ የማቋረጥ ተግባር በሌሎችም ሀገራት የተለመደ ተግባር መሆኑን በመግለጽ፣ ክስ ማቋረጡ ላይ ሳይሆን ችግሩ ያለው በአፈጻጸሙ ላይ ጭፍን ሂደቶች እንደሚስተዋሉ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

<<20 ባንክ የዘረፉ ወንበዴዎች በሽምግልና እየተለመኑ፣ ግብር አልከፈልክም የተባለን ነጋዴ በእስር ወህኒ በሚወርድበት ሥርዓት ላይ፣ ዐቃቤ ሕግ ለሕዝብ ጥቅም ሲባል የነእከሌን ክስ አቋረጠ የሚል ፖለቲካዊ እንደምታ ያላቸው ውሳኔዎችን መስማት የተለመደ ሆኗል>> ሲሉ ደረጄ ይተቻሉ። አሁንም ሥጋቱ ክስ ማቋረጡ ሳይሆን፣ ይህንን የሚተገብረው አካል የአሰራር ባህል መሆኑንም አክለው ገልጸዋል።

አሁንም በኢህአዴግ ውስጥ ፖለቲካዊ ባህላችንና ድርጅታዊ አስተሳሰባችን አልተቀየረም የሚሉት ደረጀ፣ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ጉዳት በሕዝብና በመንግሥት ላይ አድርሰዋል ተብለው ዝርዝር የክስ ሒደት የቀረበባቸውን ባለስልጣናትና ነጋዴዎችን ክስ ዐቃቤ ሕግ ሲያቋርጥና ‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ክሱ እንዲነሳ ተወስኗል›› ማለቱን ስናይ ስሜት አልባነቱን አመላካች ነው ብለዋል። የሕዝብን ንብረት ዘርፎ ለሕዝብ ጥቅም ማለት የማያስኬድ መሆኑን በማመላከት።

እንደ ስሜነህ ገለጻ፣ መንግስት የወንጀል ሕግን እንደመጨቆኛ መሳሪያነት ሲጠቀምበት ኖሯል፤ ጸረ ሙስና፣ ጸረ ሽብር እና ሌሎች መሰል ሕጎችንም ሲያወጣ ለራሱ በሚመቸው መንገድ ጭካኔ የተሞላባቸው ሕጎች አድርጎ ቀርጿቸው ነበር፤ እነዛ ሕጎች ሕዝቡን ሲጎረብጡት ኖረዋል። አሁንም ብዙ ሥልጣን ያለው አቃቤ ሕግ የሚፈጽማቸው ክስ የማቋረጥ ሂደቶች ፖለቲካዊ ናቸው ሲሉ ያስረዳሉ።

ለዓመታት ሲመዘብሩ ነበር ተብለው የሚጠረጠሩ አካላት በዚህ መንገድ ነጻ ከመሆናቸው ይልቅ የፍርድ ሂደቱ ቀጥሎ ውሳኔ ማግኘት እንደነበረባቸው የሚገልጹት ስሜነህ፣ ህብረተሰቡም የሚፈልገው ሚዛናዊ የሆነ የፍርድ ውሳኔ እንደሚሆን ተናግረዋል።

ስሜነህ እንደገለጹት፤ በክስ መዘገቦች ላይ ጥልቀት ያለው ምርመራ በማድረግ፣ ተገቢውን ፍትህ መስጠትና ለህዝብ በግልጽ ማሳወቅ የፍትህ ስርዓቱ ላይ ታማኝነት እንዲጎለብት ማድረግ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።

ደረጀ (ዶ/ር)፣ በአሁኑ ወቅት የፍትህ ስርዓቱ ክስ ለማቋረጥ የሚያስችል ቁመና እንደሌለው በመናገር፣ የፍትህ ስርዓቱ ላይ እየተደረጉ ያሉ ለውጦች መሰረት ሳይዙ ክስ ማቋረጥ ተገቢ አለመሆኑን ጠቅሰዋል። ሕብረተሰቡ በፍትህ አካላት ላይ እምነት እንዲያሳድርና አዎንታዊ አመለካከት እንዲያዳብር ወቅቱ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ በዚህ ረገድ ሊሰራ እንደሚገባ አስታውቀዋል።

በደረጀ (ዶ/ር) ሀሳብ የሚስማሙት ስሜነህ፣ በክስ ሂደት ላይ ያሉ ከባድ ክሶችን እንዲቋረጥ ከማድረግ ይልቅ፣ የዋስትና መብት ማስጠበቅና መዝገቦች ላይ በጥልቀት ምርመራ ማድረግ የተሻለ እንደሚሆን ጠቁመው፣ በሙስና ወንጀል ላይ ተገቢውን ፍትህ መስጠት ሙስናን ለመከላከል እንደሚያግዝና ሕዝቡ በፍትህ ስርዓቱ ላይ እምነት እንዲያሳድር እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

‹‹ለሕዝብ ጥቅም ሲባል›› የሚለውን ማብራራት አልቻልንም የሚሉት ስሜነህ፣ አንድ ተጠርጣሪ ክሱ ተቋርጦ ቢፈታ ለሕዝብ የሚያመጣው ጥቅም፣ የጤና ችግር ካለበትና ሌሎችም ነገሮች ክስን ለማቋረጥ በምክንያትነት ሲቀመጡ፣ የሕዝብ ጥቅም የሚለው ግልጽ ማብራሪያ እንዳልተበጀለት በማውሳት፣ አሁንም ግልጽ የሆነ፣ ፍትሃዊ የሆነ ማብራሪያና ትርጉም እንደሚያስፈልገው ይናገራሉ። ጊዜ ሳይሰጠው ትርጉም ሊሰጠው እንደሚገባ በማስታወቅ።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ጥር 17/2011 ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽሕፈት ቤት በቁጥር አአ/ከፅ/01/01/42 በተጻፈለት ደብዳቤ፣ የአዲስ አበባ ግብር ከፋይ ሆነው ጉዳያቸው በፖሊስና በአቃቤ ሕግ እጅ የሚገኙ ክሳቸው እንዲቋረጥ፤ ፍርድ የተሰጠባቸውም በምህረት እንዲለቀቁ በማለት የ1640 ግብር ከፋዮች ዝርዝር ቀርቦለት ከነዚህ ውስጥ 1077ቱን እንዲቋረጥ ማድረጉ ይታወሳል።

ተከሳሾቹ መደበኛ የኮንትሮባንድ ወንጀሎች ማለትም፣ ደረሰኝ ሳይዙ ወይም ዲክላራሲዮን ሳይኖራቸው የተለያዩ ዕቃዎች በንግድ ሱቃቸው የተገኘባቸው ናቸው። በተጨማሪም፣ የባለሥልጣኑን ሥራ ማሰናከል ወንጀልና ከሽያጭ መመዝገቢያ መሳሪያ አድራሻ ጋር የተፈጸሙ ጥፋቶች መሆናቸውንም የክስ መዝገቡ ያትታል።

ዐቃቤ ሕግ እነዚህ ወንጀሎች ከአፈጻጸማቸው፣ ከያዙት የገንዘብ መጠን አነስተኛ መሆን፣ እንዲሁም ከተያዘው የኢኮኖሚና የታክስ ሪፎርም እና ከግለሰቦቹ የኢኮኖሚ አቅም አንጻር በምርመራም ሆነ በፍርድ ቤት ደረጃም ያሉ በሙሉ እንዲቋረጡ ቢደረጉ በመንግስትና በሕዝብ ጥቅም ላይ የሚያደርሱት ጉዳት ዝቅተኛ በመሆኑ ክሳቸው ተቋርጦ ሙሉ በሙሉ ወደ ስራ ቢገቡ ለመንግስትና ለሕዝብ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ያቀረባችሁትን ጥያቄ በመቀበል ክሳቸው እንዲቋረጥ ወስነናል ሲል ክሱን ማቋረጡ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here