የመጨረሻው ስንብት

0
1093

“አንድ ቀን ልዑሌን አገኘዋለሁ፤ አባቴ ግን ሁል ጊዜም ንጉሤ ነው” የሚል ጥቅስ ያረፈበት እና መዓዛ አምባቸው መኮንን ከአባቷ ጎን የሚታዩበት ምሥል አዲስ አበባ፣ ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ የሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ሳሎን ቤት መግቢያ በግራ በኩል አነስ ባለች ፍሬም ቢቀመጥም ከሩቁ ዓይን ውስጥ ይገባል። ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ አመሻሽ ላይ ሕይወታቸው ያለፈው የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኹለተኛ ልጅ መዓዛ ወላጅ አባቷን ጓደኛዬ ስትል ትጠቅሳቸዋለች።

የሕክምና ትምርቷን በመተው እንደ ወላጅ አባቷ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ምሩቅ የሆነቸው መዓዛ አባቷ በሕይወት እያሉ ወደ አማራ ክልል ለሥራ ሊሔዱ እንደሆነ ስታውቅ ይህንን ሐሳባቸውን ትተው እንዲቀሩ እንደለመነቻቸው እና እሳቸው ግን በዚህ ሐሳብ ሳይስማሙ መቅረታቸውን ትናገራለች። የአምባቸው የቅርብ ወዳዶች እንደሚሉትም በሕይወት እያሉ መዓዛን በተለየ ዓይን እንደሚያዩአት እና “አንድ ቀን ታያቷላችሁ” ከማለት ውጪ ግን ዝርዝር እንደማይናጋሩ ያወሳሉ።

ከአምስቱ ልጆቻቸው የመጀመሪያ ልጃቸው የሆነችውን ነፃነትን በያዝነው ዓመት የዳሩት አምባቸው፥ የሰባተኛ ክፍል ተማሪ ወንድ ልጅ እና ኹለት ታናናሽ ሴት ልጆችም አሏቸው።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም በስሜት በተሞላው እና በሽኝት ሥነ ስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግራቸው ከአምባቸው ጋር ሕይወታቸው ያለፈውን የምግባሩ ከበደ እና የእዘዝ ዋሴን ቤተሰቦች ጨምሮ የመንከባከብ ግዴታ አለብን ሲሉም አሳስበዋል።

አምባቸው መኮንን ማን ነበሩ?
ስለ አምባቸው ማንነት አዲስ ማለዳ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ያነጋገረቻቸው ግለሰቦችም ሆኑ በአደባባይ የተሰጡ ንግግሮች እንደሚያስረዱት አምባቸው ከምንም በላይ ፈገግታቸው፣ ጨዋታቸው እና ሰው አክባሪነታቸው ይነሳል። በደቡብ ጎንደር ጋይንት ወረዳ በ1962 የተወለዱት አምባቸው የልጅነት ጓደኛ እና እስካሁንም የቅርብ ወዳጃቸው የነበሩት አንዳርጌ እንደሚሉት የአምባቸው ባሕርይ ከልጅነታቸው ጀምሮ ያልተለወጠ መሆኑን ነው።

በሥልጣን ዘመናቸው ላይ ሆነው በሰጧቸው ቃለ ምልልሶች ላይም ለገጠሪቷ ኢትዮጵያ ያላቸውን ፍቅር ደጋግመው ከመግለጽ ባሻገር “አሁንም ቢሆን የከተማ መዝናናትን አልወደውም ጊዜ ሳገኝም የድሮ ትዝታዎቼን እያነሳሁ መጫወት ነው ፍላጎቴ” ሲሉም ይደመጡ ነበር። ወዳጆቻቸውን ሁሉ በአንድ ቃል “ወንድም ዓለም፣ እህት ዓለም” ብለው የሚጠሩት አምባቸው በስርዓተ ቀብራቸው ላይም ብዙዎች “ወንድም ዓለም” ብለው ሲዘክሯቸውም ተሰምቷል።

አሁን በሕይወት ከሌሉት እና አምባቸው እጅግ አጥብቀው ከሚወዷቸው መኮንን ሲሳይ እና በሐዘን በተጎዳ ድምፃቸው ልጃቸውን ደጋግመው በቀብሩ ሥነ ስርዓት ላይ ሲጣሩ ከነበሩት ከእናታቸው አማን ይቺን ዓለም ተቀላቀሉ። የአምባቸው የአክስት ልጅ እና የልብ ወዳጅ የነበሩት አንዳርጌ እንደሚሉትም አምባቸው እና ወላጅ አባታቸው በተለይ በፈገግታቸው እንደሚመሳሰሉ እና የመጀመሪያ ልጃቸው የቀለበት ሥነ ስርዓት ላይ መዓዛ የአባታቸውን ምሥል የያዘውን የእጅ ንድፍ ውጤት አጥብቀው እንደሚወዱት የሚገልጹ ሲሆን ይህ ንድፍም በሳሎናቸው ግድግዳ ላይ ተንጣሎ ይገኛል።

አርሶ አደር ቤተሰቦቻቸው የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ ወደ አቄቶ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተላኩት አምባቸው ሦስት ጊዜ ‘ደብል’ በመምታት የነበራቸውን አቅም አሳይተዋል፤ ዘጠነኛ ክፍል እሰኪደርሱ በከፍተኛ ውጤት ተማሪ ነበሩ። በወታደራዊው አገዛዝ እና በተቃዋሚዎቹ መካከል የነበረው ፍትጊያ በመጨመሩ ትምህርት ቤታቸው በመዘጋቱ እና እሳቸውም የትጥቅ ትግሉን በ1982 በቀድሞው ኢሕዴን በአሁኑ አዴፓ ውስጥ ተቀላቀሉ።

ትግሉ መጠናቁን ተከትሎም በተለያዩ የመንግሥት ሰዎች ውስጥ የተቀላቀሉት አምባቸው ከወራት በፊት ከእንግሊዝኛው ካፒታል ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ እንደገለጹት በሜክሲኮ የርቀት ትምህርት በመማር እና በትምህርት በሬዲዮ በመታገዝ የኹለተኛ ደረጃ እና የመሰናዶ ትምህርታቸውን አጠናቀዋል።

በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በ1990 በኢኮኖሚክስ ትምህርት ያጠናቀቁት አምባቸው፥ በልጅነታቸው መምህር መሆን ይፈልጉ እንደነበርም የቅርብ ጓደኞቻቸው ከእሳቸው ባለፈ ምስክር ናቸው። የማስተርስ ዲግሪያቸውን በሰሜን ኮሪያ በኢኮኖሚክስ ትምህርት ያጠናቀቁት አምባቸው ከ11 ዓመታት በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ ካገለገሉ በኋላ ወደ እንግሊዝ አገር በማቅናት የዶክትሬት ዲግሪ ዕድል አግኝተው ማቅናታቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያስረዳል።

ለሦስተኛ ዲግሪ ነጻ የትምህርት ዕድል የተጣቸው ኬንት ዩኒቨርሲቲ ለኹለተኛ ዲግሪያቸው ሌላ ዕድል በመስጠት ተቀበላቸው።
አምባቸው በእንግሊዝ ቆይታቸው ብዙ ጓደኞቻቸውም ሆኑ እሳቸው አይረሱትም። ትምርታቸውን መከታተል ከጀመሩ በኋላ ከመንግሥት ጥለው እንዲመለሱ ትዕዛዝ የደረሳቸው ሲሆን እሳቸው ግን አሻፈረኝ በማለት ትምህርታቸውን ራሳቸውን በመደጎም እና ወዳጆቻቸውም ከአገር ውስጥ ሆነው በሚያዋጡት ገንዘብ ተከታትለው አጠናቀቁ።

በኢኮኖሚክስ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከያዙም በኋላም በተለያዩ የፌደራል የሥራ ኀላፊነት ላይ የነበሩት አምባቸው፥ በያዝነው ዓመት በየካቲት ወር ገዱ አንዳርጋቸውን በመተካት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በመሆን ሕይወታቸው ከኹለት የሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር እስካለፈበት ጊዜ ድረስ በማገልገል ላይም ነበሩ።

አምባቸው በኢሕአዴግ ውስጥ ለመጣው ለውጥም ከፍተኛ ተጋድሎ ማድረጋቸውን ወዳጆቻቸው ይናገራሉ። በተለይም የአማራ እና የኦሮሚያ ክልል ወጣቶች ለሰላማዊ ሰልፍ ወጥተው መገደል የለባቸውም በማለት በማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባዎች ላይ አንዳንዴም ሕይወታቸውን ለአደጋ ጥለውም ጭምር ሲታገሉ እንደነበር የቅርብ ወዳጆቻቸው ያክላሉ።

የአምባቸው ሴት ልጅ መዓዛ ስለአባቷ ስትናገር የአባቷ የቅርብ ጓደኛ እና ከዓመት በፊት ሕይወታቸው ስላለፈው ተስፋዬ ጌታቸው አክላ ነበር። “ተስፋዬ ነው ያሳደገኝ፣ እኔ ጀግና ነኝ እነሱ አይሞቱም ሥማቸው ይበቃናል” ስትል ተደምጣለች።

መዓዛ በግጥም፦
“ባሕር ዛፍ ቢቆረጥ ያበቅላል ቁጥቋጦ
ከዛም እየቆየ ለምልሞና አጊጦ
አምሳሉን ይተካል አይቀርም ተቆርጦ” በማለት ሟቾችን ሥም በመጥራት አውስታለች።
አምባቸውም በሕይወት እያሉ ከወራት በፊት ለካፒታል ጋዜጣ በሰጡት ቃለ ምልልስ ላይ ይህ ትግል ስላመጣው ለውጥ እና ስለቅርብ ወዳጃቸው ሟች ተስፋዬ ጌታቸው ሲናገሩ በእንባ ሳግ ተውጠው ነበር።

በወቅቱ አምባቸው እምባ እየተናነቃቸው ሲናገሩ “የእነብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌን ጨምሮ በኦሮሚያ እና በመላው አገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች የታገለላቸው ሰዎች ተፈተው በነጻነት ሳያያቸው መሞቱ ያሳዝነኛል” ብለው ነበር።

ከአምባቸው ጋር በተመሳሳይ ቀን በላሊበላ ከተማ የቀብር ሥነ ስርዓታቸው የተካሔደው አሳምነው ፅጌ መርተው እና አስተባብረውታል በተባለው ጥቃት አምባቸው በሚመሩት የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣኖች በተገኙበት ስብሰባ ቅዳሜ ከቀኑ 11 ገደማ ሰዓት መጀመሩን ሕይወታቸው የተረፉ የኮሚቴው አባላት ይናገራሉ።

በተመሳሳይ በክልሉ የፖሊስ ኮሚሽን ቅጥር ግቢ ውስጥ ግድያዎቹን አስተባብሯል የተባሉት ብ/ጄኔራል አሳምነው ሌላ ስብሰባ ጠርተዋል። እዛም የክልሉን የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርን ጨምሮ የተለያዩ የፀጥታው ዘርፍ አመራሮች ተሰብስበው ባሉበት እንደተቆለፈባቸው እና የፖሊስ ኮሚሽኑም የመጀመሪያው ዒላማ ሆኖ ጄነራሉ አሠማርተዋቸዋል በተባሉ የልዩ ፖሊሶች ተከቧል።

በመቀጠልም የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት ተከቦ ከባድ የተኩስ ድምፅ መሰማት መጀመሩን ተከትሎ በስብሰባው ላይ የነበሩት አመራሮች በተለያየ አቅጣጫ ከአደጋው ለመራቅ ጥረት ቢያደርጉም ጥረታቸው ሳይሳካ ቀርቶ አምባቸውን እና አማካሪያቸውን እዘዝን ፀሐይ ሳትጠልቅ አሰቃቂ በሆነ ግድያ አጡ።

ከዛም በያዝነው ሳምንት ሰኞ፣ ሰኔ 17 በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ምግባሩ ከበደ ሕይወታቸው ማለፉ ታውቆ በሰዓታት ልዩነት የጥቃቱ አቀነባሪ እና መሪ የተባሉት ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ ከፀጥታ ኀይሎች በተከፈተ ተኩስ ሕይወታቸው አለፈ።

ምግባሩ ከበደ ማን ነበሩ?
በደቡብ ጎንደር አስተዳዳር ዞን ደራ ወረዳ ከአባታቸው ከከበደ እውነቱ እና ከእናታቸው ከየሺ ውበቱ በ1966 የተወለዱት ምግባሩ፥ ልክ እንደ አምባቸው ሁሉ በጣም ባጠረ ጊዜ ትምርታቸውን መጨረስ ችለዋል። የሕይወት ታሪካቸው መዝገብ እንደሚያስረዳው ከሆነ የሕግ የመጀመሪያ እና ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማግኘት ችለዋል።

በተለያዩ ደረጃዎች በዐቃቤ ሕግነት እና ከ1998 ጀምሮ ረዘም ላሉ ጊዜያት በምሥራቅ ጎጃም አስተዳደር ዞን በተለያዩ የመሪነት ቦታዎች ያገለገሉት ምግባሩ፥ በ2008 የክልሉ ርዕሰ መስተዳድሩ አማካሪ ሆነው ተሹመዋል። ቀጥሎም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሆነው በማገልገል ላይ እያሉ በተፈፀመው ጥቃት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን ሰኔ 19/2011 ከአጋሮቻቸው ጋር በባሕር ዳር ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ስርዓተ ቀብራቸው ተካሒዷል። የሦስት ወንድ እና የኹለት ሴት ልጆች አባት የሆኑት ምግባሩ ከተወለዱ በ45 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

በቀብር ሥነ ስርዓቱ ላይም ልጃቸው ሥነ ምግባሩ አባቷ በሕይወት ዘመኗ ሁሉ ለሕዝብና ለአገር ሲሉ ይኖሩ የነበሩ እንደነበሩ እና መኖሪያ ቤት እንኳን እንደሌላቸው ገልጻለች። ምግባሩ በተለይም በፖለቲካ ትንታኔ አቅማቸው እና በአመራር ክኅሎታቸው እንደሚታወቁ ባልደረቦቻቸው ምስክርነት ሰጥተዋል።

እዘዝ ዋሴ ማን ነበሩ?
በደቡብ ጎንደር ዞን እስቴ ወረዳ በ1957 ከአባታቸው ከዋሴ መንግሥቱ እና ከእናታቸው የውብዳር ቢወጣ የተወለዱት እዘዝ እስከ 1982 ድረስ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ቆይተው ከጓደኞቻቸው ጋር ደርግን በመቃወም ወደ ትግል ገቡ። ከትግሉ በኋላም በተለያዩ ወረዳዎች የሰላም እና የመረጋጋት ሥራዎች በብቃት መምራታቸውን የሕይወት ታሪካቸው ያትታል።

እዘዝ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ ማኔጅመንት እና የማስተርስ ዲግሪያቸውን በቢዝነስ አድሚንስትሬሽን አጠናቀዋል። የኹለት ሴት እና የሦስት ወንድ ልጆች አባት የነበሩት እዘዝ፥ ከ1998 እስከ 2002 ድረስ የእስቴ ወረዳ ሕዝብን በመወከል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አገልግለዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞንን በዋና አስተዳዳሪነት በመሩበት ወቅትም የራሳቸውን አሻራ አሳርፈዋል።

አራቱም ከፍተኛ የክልል ባለሥልጣናት ምንም እንኳን ሕይወታቸው ያለፈው በተለያየ ሰዓት ቢሆንም ላይመለሱ በየፊናቸው በሕዝቡ ተሸኙ ባንዲራ ለብሰውም ወደ አፈር ገቡ።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here