መብረቁ ብልጭ ሲል ደማሚቱን ማፈንዳት! የጄኔራል ሰዓረ አሟሟት በቅጡ ይፈተሽ!

0
781

ቅዳሜ፣ ሰኔ 15 በባሕር ዳርና በአዲስ አበባ በሰዓታት ልዩነት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን(ዶ/ር)‘ን ጨምሮ ሌሎች ኹለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት እንዲሁም የጦር ኀይሎች ኤታ ማዥር ጀነራል ሰዓረ መኮንንና ሌላ አንድ ጡረተኛ ከፍተኛ የጦር መኮንን ግድያዎች ምክንያት በመላው አገሪቱን ሐዘንና ድንጋጤ ተፈጥሯል። የኹለቱ ግድያዎች ሴራ ጠንሳሽ አንድ ቡድን ነው ወይስ እንደ ሐዲስ ዓለማየሁ ልብ ወለድ መጽሐፍ በመብረቅ አስታኮ በደማሚት ውድመት የማድረስ ዘዴ ነው ሲሉ ግዛቸው አበበ ይጠይቃሉ።

ከክቡር ሐዲስ ዓለማየሁ ልብ ወለድ መጽሐፍት በአንዱ ላይ በመብረቅ አስታክኮ በደማሚት ውድመት የማድረስ ዘዴ ጥቅም ላይ የዋለበት አንድን የፈጠራ አጋጣሚ ያትታል። አንድን አካባቢ ለማሰልጠን ፍላጎት የነበረው ገጸ ባሕሪይ የአካባውን ማኅበረሰብ ቀፍድዶ የያዘውን ‘አጉል ዕምነት’ መዋጋት እንዳለበት ተገነዘበ። ይህን ለማድረግ ደግሞ የዚያ አካባቢ ኅብረተሰብ እንደ አምላክ የሚያየውን፣ ቅቤ እየቀባ የሚሰግድለትን፣ ለመለማመን የሚሰዋለትን ወዘተ… አንድ ግዙፍ ዛፍ ማስወገድ ተገቢ መሆኑ ታመነበት። ገጸ ባሕሪው ይህ ዛፍ ከተወገደ ኅብረተሰቡ ዐይኑን ይከፍታል፣ ስለዘመናዊ ትምህርትና ስለሥልጣኔ ጥቅም ግንዛቤ ያገኛል የሚል ዕምነት ቢያድርበትም ይህን እንደ አምላክ የሚታይ ዛፍ በቀጥታና በግላጭ ማውደም ከኅብረተሰቡ ጋር ከፍተኛ ግጭት ውስጥ የሚስገባው መሆኑን ስለተገነዘበ አንድ መላ መምታተት ነበረበት። እናም የመጣለት መላ አስገምጋሚ መብረቆች በሚበዙበት እንድን ምሽት ጠብቆ ዛፉን በደማሚት መበታተን ነው። ስለዚህ ደማሚቱን አጥምዶ የመብረቁን መከሰት በተጠባበቀበት አንድ ምሽት ከድምጽ የሚፈጥነው ብልጭታ እንደታየ፣ ድምጹ የሚሰማበት ቅጽበት ተጠብቆ ደማሚቱ እንዲፈነዳ ተደረገና ግዙፉ ዛፉ ብትንትኑ ወጣ። መብረቁ የሌላ ኀይል ጉዳይ ደማሚቱ የሌላ ዓላማ ጉዳይ ቢሆኑም ባለ ደማሚቱ በመብረቁ ሽፋን ቀጣይ ሥራዎችን በመሥራት ዓላማውን ለማሳካት ሞክሯል። ምክንያቱም የሴራው ሌሊቱ አልፎ ጸሐይ ሲወጣ የዛፉን መበታተን ካዩት በጣም ብዙዎቹ ዛፉ በመብረቁ መውደሙን አምነው ተቀብለው ነበረና።

በአማራ ክልል ተካሄሔደ የተባለው መፈንቅለ መንግሥት እና በአዲስ አበባ የተፈጸመው የኢታ ማዥር ሹሙ ግድያ የተለያዩ ኹለት አካላት፣ አንዱ የሌላውን ሴራ አስቀድሞ በመረዳቱ ወይም ዝግጅቱን አጠናቅቆ ምቹ ጊዜ ሲጠብቅ ቆይቶ ይህን አጋጣሚ በማግኘቱ፣ ጊዜው አሁን ነው ብሎ የፈጸመው የሌላ ሴራ ግብ ብቻ ሳይሆን የሌላ ቀጣይ ሴራ ጅማሮ ሊሆን ስለሚችል ነገሩን በጥልቀት መመርመርና አለመዘናጋት በጣም ተገቢ ነገር ነው። ኢትዮጵያችን በአሁኑ ጊዜ ወታደራዊ ተሞክሮና ልምድ ያላቸው የጦር መኮንኖች ብቻ ሳይሆኑ የጦር መኮንንነቱን በሽልማት ወይም በስጦታ መልክ ባገኙ መኮንኖች የሚመራ መከላከያ ያላት አገር ናት። ከለውጡ ጋር ናቸው ከሚባሉት መኮንኖች መካከል ከባለተሞክሮዎቹና ከተሸላሚዎቹ የትኞቹ እንደሚበልጡ ማሰብ ሥጋትን የሚጭር ይመስላል። በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ልምድ ያላቸው መኮንኖችን ማጣት ለውጡን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንም በእጅጉ ይጎዳታል።

አዲስ አበባውን ግድያ ፈጸመ የተባለው ሰው (ወታደር) ደግሞ በዕለቱ ሰኔ 15/2011 በአንድ ቤት ውስጥ ገብቶ ራሱን አጥፍቷል ተብሎ ሰኔ 16/2011 ሙሉ ቀን ሲነገር ከዋለ በኋላ በተመሳሳይ ቀን ከምሽቱ አንድ ሰዓት አካባቢ ጀምሮ ሞቷል የተባለው የጄኔራሎቹ ገዳይ አለመሞቱና በጽኑ ቆስሎ ሕክምና ላይ መሆኑ ተነግሯል። እዚህ ላይ ዝርክርክ ድራማ ሊኖር ይችላል የሚል ጥርጣሬ በነበሩት ጥርጣሬዎች ላይ ተጨምሯል። በፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ሞተ-ዳነ ያሉት ገዳይ፣ ግድያውን የፈጸመበትን ትክክለኛ ሰዓት ቢነግሩን ጥሩ ነበር። ባሕር ዳር ላይ ግድያ የተካሔደው ወደ ዐሥራ አንድ ሰዓት አካባቢ ሆኖ ከዚህ በኋላ ብዙም ሳይቆዩ ሴረኞቹ ተሳዳጅ ሆነው ነበረና የመከላከያ ኀላፊውን በመግደል ሴራቸው ሳንካ እንዳይገጥመው ለማድረግ ሞከሩ የመባሉ ሃቅነት ምን ያህል መሆኑን ለመመዘን ይረዳል።

በአንዳንድ ዜናዎች ጄኔራሎቹ በግል ጉዳያቸው በጄኔራል ሰዓረ ቤት ተገናኝተው ሲጫወቱ የተገደሉ መሆኑ ሲነገር በሌሎች ዜናዎች ደግሞ የባሕር ዳሩን አመጽ ለማክሸፍ በሥራ ላይ እንዳሉ መገደላቸው በመነገር ላይ ነው። ለመሆኑ የዚህ ዓይነቱን ዘመቻ የመምራት ሥራ ሲከወን ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩና ሌሎች ከፍተኛ የመከላከያ ሹማምንት እየተመካከሩ መሥራት አልነበረባቸውምን? ሥራውን መሥራት የሚገባቸውስ በመንግሥታዊ ቢሮዎቻቸው በአንደኛው ተገኝተው ሊሆን አይገባውምን? ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩም ከሚስቶቻቸው ወይም ከጓደኞቻው ጋር ሆነው እየተጨዋወቱ ነበር ዘመቻውን በተናጠል ይመሩ የነበረው? ባለሥልጣናቶቻችን ቀልዱን አቁመው ጉዳዩን በጥልቀት መመርመር ይገባቸዋል።

ከዚህ ሌላ፤ ማን ማንን ገደለ ወይም አስገደለ? ለምን ዓላማ? ባለሴራ ሆኖ የገደለው ወይም የሞተው ማን ነው? በአጋጣሚው ሰለባ የሆነ ወይም ጭዳ የተደረገው ወይም ምንጠራ የተካሔደበት ሰው ይኖራልን? የጄኔራሎቹን ገዳይ ማን ለሴራ አመቻቸው? የጄኔራሎቹ ትክክለኛ ገዳይ ማን ነው? የየትስ አካባቢ ሰው ነበረ? በዚህ ዓይነት የደም ባሕር ዋኝተው ዓላማ የሚያራምዱ ግለሰቦች ሊደርሱ የፈለጉት ወዴት ነው? የሚሉና የመሳሰሉት ጥያቄዎች ትንንሾቹን ሃቆች ይዘው ተቀምጠዋል።

በእርግጥ የጄኔራሎቹ ገዳይ ገድሎ ማምለጥ የሚችልበት ቀዳዳ እንደሌለ ያወቀ፣ ጄኔራሉን ገድሎ ለመሞት የተዘጋጀ ሰው ነበረ? የዚህ ሰው አሟሟት መጣራት ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው። ለመሆኑ መፈንቅለ መንግሥት የሚያደርግ ቡድን አባል ራሱን ለሹመትና ለሽልማት ያጫል ወይስ ሞቶ ለመቀበር?
የጄኔራሎቹ ግድያ ተራ ሞት ወይም አንድ ያልታሰበበት አጋጣሚ የፈጠረው ክስተት ሊሆን እንደማይችል የታወቀ ነው። ይህ ክስተት ገዥው ቡድን (እንበለ ኢሕአዴግ) የራሱን መሪና አመራር ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ላይ የጫነው መሪና አመራር ተገቢው ብቃትና ችሎታ፣ ተገቢው ቁርጠኝነትና ዲሞክራሲዊ ባሕሪይ ያለው መሆኑንና አለመሆኑን በግልጽ ሊመረምርና ሊገመግም እንደሚገባው የሚያሳስብ ደወል ነው። የለውጡ አመራር ደካማና ልምጥምጥ መሆኑ ገሃድ እየወጣ ነው። በተቃራኒው የለውጡ ጠላቶች፣ የኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ጠላቶች ትልቅ ድል አስመዝግበዋል፤ ትልቅ ግዳይ ጥለዋል። ከአዲሰ አበባ አንዳንድ ጭፈራ ቤቶች ጀምሮ በብዙ አጋጣሚዎች ቡረቃዎች ተስተውለዋል።

አገሪቱ እና ሕዝቦቿ ከሚገባው በላይ ዘርፈ ብዙ መከራና ችግር እያስተናገዱ ነውና ይህ ጉዳይ ለነገ ሊባል የሚገባው ነገር አይደለም። የሰኔ 15ቱ ፈጻሚዎች የከፍተኛ ባለሥልጣናትን በር ስላንኳኩ፣ ብዙ እየተባለላቸው የሚገኝ ቢሆንም እነዚህ ፈጻሚዎች በለውጡ ወቅት እንደተከሰቱ ብቸኛ አደጋዎች ተደርገው መወሰድ የለባቸውም። አገዛዙ የሚቆጣጠራቸው መገናኛ ብዙኀን ችላ ቢሏቸውም፣ የሃይማኖት መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች በዘመቻ ሚዲያ ላይ ቀርበው ዕንባ ባያፈሱባቸውም፣ የክልል እና የፌደራል ባለሥልጣናት እየተፈራረቁ መገናኛ ብዙኀን ላይ የሐዘን መግለጫና እንበቀላለን የሚል ዛቻ ባይሰነዝሩባቸውም፣ ኢትዮጵያችን በርካታ መከራዎችን እያስተናገደችና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሕዝቦች የትየለሌ ግፎችን እየተቀበሉ በመኖር ላይ መሆናቸው ሊረሳ ወይም ተቃልሎ ሊታይ አይገባውም። ገዥው ቡድን ራሱን መገምገምና መፈተሸ የሚገባው፣ ባለሥልጣናቱ ላይ ችግር ስለደረሰ ብቻ ሳይሆን ከዳር ዳር የኢትዮጵያ ሕዝብ ማባሪያ የሌለው የሚመስል ግፍና መከራ እየተሸከመ ስለሆነም ጭምር ነው።

የጄኔራሎቹ ግድያ፣ ለአገርና ለወገን የሞት ሞት የሚሆነው፣ ጄኔራሎቹን የገደሉ ወይም ያስገደሉ ወገኖች (ሴረኞች) ራሳቸውን ንጹሕ አድርገውና ለጄኔራሎቹ ተቆርቋሪዎች መስለው በመተወን ላይ ከሆኑ ነው። እነዚህ ወገኖች በዚህኛው ተንኮላቸው ላይ ተረማምደው ሌላውን መወንጀል ችለው ሌላ ሴራ፣ ሌላ ግጭት፣ ሌላ እልቂትና ውድመት ለማድረስ ከቻሉ በእርግጥም የሞት ሞት ይሆናል።

ሰኔ 15 የአንዳች ሴራ ፍንጭ ገሃድ የወጣበት እንጅ አንድ ችግር ተከስቶ መፍትሔ የተገኘበት ዕለት ላይሆን ይችላል። ሰኔ 15 የሴራ ፍንጭ የታየበት እንጅ የሴራው ምንነት፣ የሴራው ጠንሻሽና አራማጆች ማንነት ሙሉ በሙሉ ተለይቶ የታወቀበት ዕለት ነበረ ማለት ተገቢ ላይሆን ይችላል። በእርግጥ ብርጋዴር ጄኔራል አሳምነው ጽጌ የሴራ ባለቤት ነበሩ ወይስ የሌላ ባለ ሴራ ተባባሪ? በዚህ ሴራ ውስጥ በአንዱ ከተማ ወይም በኹለቱ ከተሞች ግድያዎች ጀርባ ተደብቆ ዓላማውን ሚያራምድ ጀብደኛ ግለሰብ ወይም ቡድን ይኖር ይሆን? እነዚህ ጥያቄዎች በጣም ወሳኝ እና አፋጣኝ ምላሽ የሚሹ፣ ሚስጢሮችን ሁሉ አምቀው የያዙ ናቸው።

በዚያም ሆነ በዚህ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መንግሥት ቸልተኝነት በመላ አገሪቱ ዘርፈ ብዙ ውንብድናዎችን ሲያስተናግድ ቆይቶ በዚህኛው አጋጣሚ ከፍተኛ ውርደት ወደ መከናነብ መሸጋገሩ ሊሰመርበት ይገባል። ለውጡ በማይወጣው አዘቅት ውስጥ እየገባም ሊሆን ይችላል። በግልጽ በተፈጸሙ ጉዳዮችም ሆነ በስውር ሴራወች ለደረሰው ጥፋት ተጠያቂ ለውጡን እመራለሁ ብሎ አራት ኪሎ የገባው ቡድን ነው። የዚህ ወገን ችላ ባይነትና የእነዚያ ትንንሸና ትልልቅ የለውጥ ጠላቶች ውንብድና በዚሁ ከቀጠለ ቀጣዩ ጉዳይ ውድቀት መሆኑን መጠራጠር አይገባም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንዳንድ ባለሥልጣናቶቻቸው አንድ ሰዓት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ግዳይ ጥለናል ብለው፣ በብ/ጄኔራል የአስከሬን ሳጥን ላይ ቁጭ ብለው፣ አለቀ ደቀቀ እያሉ እጆቻቸው አጣፍተው እፎይ ለማለት የፈለጉ ይመስላል፤ ይህ ካለፈው አለመማር ነው።

ለውጡና የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ቡድን ከሰኔ/2010 እስከ ሰኔ/2011 በቦምብና በጥይት ጥቃት ሲሰነዘርበት አይተናል። እነዚህ መሰል ጥቃቶች በመላ ኢትዮጵያ ሕዝብ ላይም እያሰለሱ ተሰንዝረዋል። ይህ አካሔድ በተንዛዛ ንግግርና በሚዲያ ላይ ድራማ ብቻ መፍትሔ የሚያገኝ አይደለም።

በእነዚህ ግርግሮች አገሪቱ ከዳር ዳር ዝርክርክ በሆነ አስተዳደራዊ ሁኔታ ውስጥ መሆኗን መረዳት ከባድ አይደለም። መንገዶች፣ ከተሞች፣ ወረዳዎች፣ መንደሮች ወዘተ የአደጋ ጠረን የሚሸትባቸውና ሰላም የራቃቸው ናቸው። የስፖርት ማዘውተሪ ስፍራዎችና ዩንቨርሲቲዎች ሳይቀሩ ለብጥብጥና ለኹከት የተጋለጡ ሥፍራዎች ሆነዋል።

ኮሎኔል መንግሥቱ በደጀን የመሸጉትን እነመለስ ዜናዊን እና በሳህል የመሸጉትን እነኢሳያስ አፈወርቂን ፈጽሞ ሊቆጣጠሯቸው እንዳልቻሉት ሁሉ እነዐቢይ መቀሌ ከተማ ውስጥ የሚንፈላሰሱትን እነደብረጽዮንን መቆጣጠርና ማዘዝ አልቻሉም። የእነጌታቸው አሰፋ ጉዳይማ አይወሳ! ለመሆኑ ጌታቸው አሰፋ………ነገሩ ይቅር በቃ! ነገር ግን የባሕር ዳሩና የአዲስ አበባ ግድያዎች አንድነት አላቸው ወይም የአንድ ባለ ሴራ ድርጊቶች ናቸው የሚሉ ወገኖች፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ይህ ሴራ ከብ/ጄኔራል አሳምነው ጽጌ ከፍ ያለ ሥልጣን፣ አቅምና ልምድ ባለው ግለሰብ ወይም ቡድን የተመራ ነው ብለውም ድምዳሜ ላይ ሊደርሱ ይገባል።

ለውጡ ተከስቶ ብዙም ጊዜ ሳይቆይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአሁን አሁን እነደብረጽዮን ምን ችግር ይፈጥሩ ይሆን ብሎ እየሰጋና እነዐቢይ ደግሞ ምን ያወሩ ይሆን ብሎ እየቆዘመ በዚህ ጊዜ ላይ ደርሷል። በዚህ ጊዜም ላይም ነው ከአዲስ አበባ እና በአማራ ክልል መዲና በባሕር ዳር ሴራ ወይም ሴራዎች መፈጸማቸው ቢሰማም በሕዝቡ ውስጥ የተከሰተው ድንጋጤ በቤተመንግሥት አካባቢ የተከሰተውን ያህል የተጋነነ አልሆነም። ሕዝብ ከዚህ የከፋ ብዙ ነገር ሊከሰት እንደሚችል ይጠብቃል።

በተለያዩ ስብሰባዎች ላይ፣ አዲስ ወግ በሚባለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጽሕፈት አማካኝነት በሚዘጋጅ የምክክር መድረክ ላይ ጭምር የሕግ የበላይነት ማረጋገጥ ተገቢ ስለመሆኑ፣ የሴራ ፖለቲካ አካሔዶችን ነቅቶ መጠበቅ እንደሚገባ፣ ከላይ እስከ ታች ያሉ መዋቅሮችን ማጥራት ችላ ሊባል እንደማይገባው ወዘተ ብዙዎች ብዙ ተናግረዋል። በየክልሉ፣ በየዞኑና በየወረዳው ሕዝብ አጋጣሚውን ባገኘ ቁጥር ለውጡ ወደ ታች አለመውረዱን፣ ከቀድሞው የሕወሓት-ኢሕአዴግ ዘመን የተለየ ነገር እንዳይመጣ ተግተው የሚሠሩ አመራሮችና ካድሬዎች በሰፊው መሰማራታቸውን ደጋግሞ ተናግሯል፤ ሰሚ ግን የለም። አለቀሳችሁብኝ፣ ግደል ነው እንዴ የምትሉኝ? መዋቅር በማጽዳ ሥም ስንት ሚሊዮን ሰው እያነሳሁ ልተካ ነው? የሚሉ መልሶች ተወርውረዋል። ምክር ለለገሱ ተሰብሳቢወች ‘ማንቁርት አንቆ የሚጥል ኀይል እየሰለጠነ ነው’ የሚል መርዶ ይሁን የምሥራች የተነገረበት ጊዜም አለ።

ያም ሆነ ይህ አስተዳራዊ ዝርክርክነቱ አድማሱን እያሰፋና እየከፋ በብዙ አገሪቱ ክፍል በሚገኙ ጥቂት በማይባሉ ቦታዎች መንቀሳቀስና በሰላም ወጥቶ መግባት አስቸጋሪ ሆኗል። ብዙ ሕይወት ተቀጥፏል፣ አካል ተሰንክሏል፣ ንብረት ተዘርፏል ወድሟልም። ይህ በተራው ሕዝብ ሕይወት፣ አካልና ንብረት ላይ ሲፈጸም የቆየ ችግር በዕለተ ቅዳሜ፣ ሰኔ 15 የአማራ ክልል አስተዳደር ባለሥልጣናትን ቢሮና የአገሪቱን ከፍተኛ የመከላከያ ባለሥልጣን ቤት በር አንኳክቷል፤ ውድ ሕይወትንም አስከፍሏል።

የዐማራ ክልል ባለሥልጣት በክልላዊ ቢሯቸው ውስጥ በተጠራ ስብሰባ ላይ መገደላቸው ሲሰማ፣ አዲስ አበባ ውስጥ የተገደሉት ጄኔራሎች ደግሞ በጄኔራል ሰዓረ በመኖሪያ ቤት ውስጥ፣ በጄኔራሉ የግል ጠባቂ መገደላቸው ተሰምቷል። ጠባቂያቸውን ማን ላከው? የሴራው ጠንሳሾች ናቸው የተባሉት የዐማራ ክልል አመጸኞች እንደምን ብለው የጄኔራሉን የቅርብ ጠባቂ እጅ ሊጠመዝዙ ቻሉ?

እስከ አሁን የታየውና በመላ አገሪቱ የተከሰተው አስተዳዳራዊ ዝርክርክነት ለውጡን እየመሩ ነው ለሚባሉት ሰዎች ይህን ውርደት አከናንቧል። የመብረቁና የደማሚቱ ዓይነት ድራማ ካለና የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር እስከ አሁን በነበረው አያያዝ ከቀጠለ ደግሞ ታላቁ ውድቀት አይቀሬ ነው!

በመጨረሻም ይህ አጋጣሚ የአሜሪካ ፕሬዘደንት የነበሩትን የኬኔዲን ገዳይ የሚያስውስ መሆኑን መጠቆማ ተገቢ ነው። ፕሬዘደንት የነበሩት ኬኔዲ በጠራራ ጸሐይ፣ በክፍት መኪና ላይ ሆነው ከባለቤታቸው ጋር በሕዝብ መካከል እየተጓዙ ቢገደሉም አሟሟታቸው ሚስጢር ሆኖ እስከ አሁኑ ዘመን ደርሷል። ብዙ ባይነገርም የኬኔዲ ወንድሞችም በተለያዩ ጊዜያት ተገድለዋል። ከተገደሉት ወንድምቸው አንዱ የአሜሪካ ፕሬዘደንት ለመሆን ፉክክር ውስጥ እንደገቡ ነበረ የተገደሉት። የአሁኑ የአሜሪካ ፕሬዘደንት ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን በያዙ ሰሞን የኬኔዲን አሟሟት በሚመለከት አንዳች ሚስጢር አወጣለሁ ብለው ዝተው ነበረ። ነገር ግን ይህ ነው የሚባል ሚስጢር አላወጡም፤ ነገር ግን ይህ ዛቻቸው የኬኔዲ አሟሟት የተደበቀ ሚስጢር አለው የሚለውን የቆየ አባባል ያደሰ ሆኗል። ፕሬዘደንት ኬኔዲ እንደተገደሉ አንድ ግለሰብ የኮምኒስቶች ተላላኪ ሆኖ ግድያውን ፈጽሟል በሚል ተወንጅሎ ወደ ፍርድ ቤት ተወሰደ። ይህ ግለሰብ በፖሊስ ተይዞ ከፍርድ ቤት በመውጣት ላይ እንዳለ በሌላ ሰው ተገደለ። የተጠርጣሪው ገዳይ ደግሞ እስር ቤት ውስጥ ራሱን አጠፋ ተብሎ ጉዳዩ ተድበስብሶ ቀረ። የኬኔዲ አሟሟት አስገዳዮቹ፣ ግፋ ካለም በየጊዜው አሜሪካ ፕሬዘደንት የሆኑ ግለሰቦች ብቻ የሚያውቁትና አፍነውም የሚያስቀሩት የአሜሪካ ከባድና ዕድሜ ጠገብ ሆኖ በመኖር ላይ ነው።

ይህን መሰል ገፍና ወንጀል መሸፋፈን በአገራችን ሊያጋጥም አይገባም። የኹለቱ የኢትዮጵያ ጄኔራሎች በተለይም ቤተሰብ ይበተናል እንጅ ኢትዮጵያ አትበተንም ብለው በመቆማቸው ጠላት ብዙ የሆኑት የጄኔራል ሰዓረ ገዳይና አስገዳዮች ተሰውረውና ከፍርድ አምልጠው ሊኖሩ አይገባቸውም። የእነዚህ የጄነራሉ ጠላቶች መታወቅና ለፍርድ መቅረብ ለጄኔራሉ እንደ ትንሳኤ፣ እንደ ዳግም ውልደት ይቆጠራል። የጄኔራሎቹ ገዳይ አሟሟት መብረቅ ፈጣሪ ሆኖ ሌላ ራሱ ያላወቀው ሰው ደማሚት አፈንጅ የሆነበት ሴራ ሆኖ ከቀረ ግድያዎች ሊቀጥሉ ይችላሉ። አንዱን ሚስጢር በሌላ ግድያ የመደበቅ አዙሪት ተፈጥሮ ችግሩ ከፍቶ ሊቀጥል ይችላል።

ግዛቸው አበበ መምህር ሲሆን በኢሜል አድራሻቸው gizachewabe@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here