የጀነራሎቹ ስንብት

0
970

ቅዳሜ፣ ሰኔ 15/2011 ለኢትዮጵያ መልካም ቀን አልነበረም። ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት መናገሻ ከሆነችው ባሕር ዳር እስከ ኢትዮጵያ መዲና አዲስ አበባ ሰሚን የሚያደነዝዝ ዜና በአገሩ ናኘ። ሰባት የአማራ ክልል ቁንጮ ባለሥልጣናት ስለ ክልሉ መፃኢ እና ነባራዊ ሁኔታ እየመከሩ ባሉበት ወቅት ባመኑትና እነሱን ብቻ ሳይሆን ክልሉንም በፀጥታውና ደኅንነቱ ረገድ ይደግፋል ባሉት የሥራ ባልደረባቸው የክልሉ የሰላምና ደኅንነት ቢሮ ኀላፊ ብርጋዴር ጀነራል አሳምነው ፅጌ ፊት አውራሪነት የተቀነባበሩ የተባሉ ጥቃቶች ተሰንዝረውባቸዋል። የነገዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት አንገታቸውን ደፍተው ሥራ ላይ የነበሩ የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር አምባቸው መኮንንን (ዶ/ር) ጨምሮ ሦስት የሥራ ባልደረቦቻቸው አሻግረው የተመለከቷትን የተስፋዋን ምድር ኢትዮጵያን በርቀት እንደተመለከቱ ሳይረግጧት እስከ ወዲያኛው አሸልበዋል።

ከባዱ ሐዘን በባሕር ዳር ብቻ የተገደበ አልነበረም። ከባሕር ዳር 525 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኘው የአፍሪካ መዲና አዲስ አበባ ላይም በተመሳሳይ ቀን አመሻሽ ላይ በቅርብ በሚያውቋቸው ጭምቱ፣ ጀግና ተዋጊው እና አዋጊው፣ በሰንደቅ ዓላማው እና በአገሩ የማይደራደረው በመከላከያ ሚኒስቴር ጦር ኀይሎች ኢታ ማዥር ሹም ጀነራል ሰዓረ መኮንን ከልጆቻቸው ለይተው በማያዩት የቅርብ የጥበቃ ጓድ መኖሪያ ቤታቸው ከባልንጀራቸው ጡረተኛ ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ጋር እየተጨዋወቱ ባሉበት ወቅት ግድያ ተፈፅሞባቸዋል።

ሰዓረ መኮንን ይመር ማን ናቸው?
“አባቴ ከልጆቹ እና ከትዳሩ አስበልጦ አገሩን የሚወድ ጀግና ነበር” ይላሉ የጀነራል ሰዓረ ልጅ ማኣሾ ሰዓረ። በዐሥራ ስድስት ዓመታቸው በ1969 ነበር “ኧረ ጥራኝ ጫካው፣ ኧረ ጥራኝ ዱሩ” ብለው ወታደራዊ አገዛዙን ለመፋለም የታላላቆቻቸውን ፈለግ ተከትለው ደደቢት ላይ የከተሙት። የያኔው አፍላ ወጣት ሰዓረ የጀመረው የትጥቅ ትግል ሕይወቱ ከአጋዚ ኦፕሬሽን እስከ ዘመቻ ዋለልኝ፣ ከዘመቻ ቴዎድሮስ እስከ ሰርዶ ኦፕሬሽን ያልመሩትና ያልተሳተፉበት ዓውደ ውጊያ አልነበረም። ጀነራል ሰዓረ ከደርግ ውድቀት በኋላ መደበኛ መከላከያ ሠራዊት ምሥረታ ወቅት በ1988 የሙሉ ኮሎኔልነት ማዕረግ አግኝተው ምሥራቅ ዕዝን በመምራት ምሥራቃዊውን የኢትዮጵያ ክፍል ናኝተውበታል።

ጀነራል ሰዓረ በ1991 በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የቡሬ ግንባር አዛዥ በመሆን እና ሠራዊቱን በመምራት ከዓመታት በኋላ ደማቅ ድልን ያስመዘገቡበት ዓውደ ውጊያ ነበር። ጀነራሉ ከ1997-2006 የሰሜን ዕዝ ዋና አዛዥ በመሆን ለዘመናት የጥይት ተኩስ ሳይሰማበት የማያድረውን የሰሜን ድንበር ለአፍታ ዓይናቸውን ሳይከድኑ በንቃት ጠብቀው እና አስጠብቀው ግዳጃቸውን የተወጡ ዕንቁ የኢትዮጵያ ልጅ ነበሩ። “ወላድ በድባብ ትሒድ እንጂ…” ተብሎ የማይኮራበት በሕይወት ዘመን አንድ ጊዜ የሚፈጠር አስገራሚ ጭምትነት ከተሟላ ወታደራዊ ክኅሎት ጋር የተላበሰ የኢትዮጵያ ዓይን ማረፊያ ነበሩ – ጀነራሉ። ‘አባ ሓዊ፣ አባ እሳቱ’ በመባል የሚታወቁት ጀነራል ሰዓረ የጀግንነትን ደረጃ አርቀው ሰቅለው ተተኪ የማግኘቱን ጉዞ አዳጋች እንዲሆን ያደረጉ ትጉህ ወታደር ነበሩ።

“ሰዓረ ማለት ወታደርነት ምን ማለት እንደሆነ ገና ከወጣትነት ዘመኑ ጠንቅቆ የተረዳ ጥንቁቅ የሕዝብ ልጅ ነበር” ይላሉ የቀድሞው ኢታ ማዥር ሹም ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገብረተንሳይ ሐዘን ባጠላበትና በተሰበረ ልብ ውስጥ ሆነው ስለ ጀግናው የትግል ጓዳቸው እና ታዛዥ ወታደራቸው ምስክርነታቸውን ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ። በሌላ በኩል ደግሞ ከግድያው አንድ ሰዓት አስቀድሞ በሥልክ ማውራታቸውን ከገቡበት ድንጋጤና ግራ መጋባት በወጉ ያልወጡት የቀድሞው አፈ ጉባዔ አባዱላ ገመዳ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ጀነራል ሰዓረ ከራስ ዳሽን ተራራ እስከ ዳሎል ረባዳ መሬት፣ ከጋምቤላ ጫፍ እስከ ሱማሌ አሸዋማ መሬቶች ደረታቸውን ለጦር እግራቸውን ለእሾህ ገብረው ሰንደቅ ዓላማዋን አንግበው በርካታ ገድሎችን መፈፀማቸውን በመዋዕለ ዜናቸው ተከትቧል። ይሁን እንጂ በሐሩር እና በቁር እየተጠበሱ ከደማቸው እና ከላባቸው እያጠቀሰ ደማቅ ታሪክ የጻፉላት ኢትዮጵያ ብድሯን በሞት ከፈለቻችው፤ ጀነራል ሰዓረ ወደ ማይቀርበት ሔደዋል። የግድያቸው ዜና ከተሰማበት ደቂቃ አንስቶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዳር እስከ ዳር በሐዘን ተመትቷል።

የቀብር ሥነ ስርዓታቸው በትግራይ ክልል መቀሌ ከተማ ስለሚከናወን የመሐል አገር አፍቃሪያቸውም ሐዘኑን ይገልጽ ዘንድ በሚሊኒየም አዳራሽ አስከሬን ሽኝት በመንግሥት ተዘጋጅቶ ነበር። ከረፋዱ 5፡30 ገደማ ላይ በኢትዮጵያ ተራሮችና ሸንተረሮች ላይ እልፍ ወታደሮችን እየመሩ የተንጎማለሉት ልበ ሙሉው ጀነራል ሰዓረ “በሞቴም አትለየኝ” ያሉ ይመስል ዘመናቸውን ኹሉ በተዋደቁላት ሰንደቅ ዓላማ ተሸፍነው ባልደረቦቻቸው ተሸክመዋቸው ወደ አዳራሹ ገቡ። ይህን ጊዜ ምድር ቀውጢ ሆነች፣ እምባ እንደጎርፍ ፈሰሰ፣ በአዳራሹ ውስጥ የነበሩት የመከላከያ ሠራዊት አባላት እምባ ጨርሰው ደም እያነቡ እንደ ወንድም የሚወዱትን መሪያቸውን ቆመው ተሰናበቱ። ጀነራል ሰዓረ ከኹለት ልጆቻቸው ባለፈ የትግል ጓዳቸውን፣ የኑሮ አጋራቸውን፣ የልጆቻቸውን እናት ኮሎኔል ፅጌ ዓለማየሁን ጥለው ተሰናብተዋል። አርያም ድረስ በሚሰማ ድምፅ ኮሎኔል ፅጌ የባለቤታቸውን ሥም እየጠሩ ሕዝቡን በእምባ ያራጩበት ሁኔታ ልብን የሚነካ ነበር።

ጀነራል ሰዓረ ከወታደራዊ ሳይንስ ባሻገር ከአገረ እንግሊዝ ግሪንዊች ዩኒቨርሲቲ በሥራ አመራር የኹለተኛ ዲግሪያቸውን በላቀ ውጤት በማጠናቀቅ ከውትድርናውም ባለፈ በሲቪል ትምህርት ግንባር ቀደም እንደሆኑ አሳይተዋል። ይህ ሁሉ ግን ጀነራሉን ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ ከመሆን አልከለከላቸውም – ሰኔ 15 /2011 በዱር በገደሉ አፍንጫው ሥር ሔደው ምንም ያላላቸው ሞት አርፈው ከተቀመጡበት መኖሪያ ቤታቸው ድረስ ሰተት ብሎ መጥቶ አገኛቸው። ጀነራል ሰዓረ ብዙ በሚሠሩበት እና ከራሳቸው በላይ ለሚወዷት ኢትዮጵያ ያሰቡላትን ሳያደርጉ በ57 ዓመታቸው ለኢትዮጵያ ሰቀቀናቸውን አሸክመው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ ደስታ
የሥራ ባልደረቦቻቸው ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራን “የመከላከያ የሎጂስቲክ አባት” ይሏቸዋል። በ1953 በአክሱም ገጠራማ ቀበሌ የተወለዱት ሜጀር ጀነራል ገዛኢ እንደ አብዛኞቹ የዛ ዘመን እኩዮቻቸው አጥንታቸው ሳይጠነክር ነበር ነፍጥ በማንገብ ደደቢትን ተቀላቅለው ከደርግ መንግሥት ጋር ፍልሚያ ውስጥ የገቡት። በትጥቅ ትግሉ ወቅት የሠራዊቱ ኢኮኖሚ ክፍል ኀላፊ በመሆን የኀላፊነት ሥራቸውን የጀመሩት ጀነራል ከደርግ ውድቀት በኋላ መደበኛ የሠራዊት ግንባታ ወቅት የመከላከያ ሠራዊት የሎጀስቲክ ኀላፊ በመሆን አገልግለዋል። ከአሜሪካን አገር በሎጅስቲክ የመጀመሪያና ኹለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙት ሜጀር ጀነራል ገዛኢ፤ በ1990 በመከላከያ ውስጥ የሎጀስቲክ ዳታ አሰጣጥ ሥልጠና ተግባራዊ በማድረግ ትልቅ ሚና የተጫወቱ ጉምቱ የወታደራዊ መኮንን ነበሩ።

“ከገዛኢ አጠገብ ተቀምጦ አለመሳቅ አይቻልም” የሚሉት ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገብረተንሳይ፥ መከላከያ አሁን ለደረሰበት የሎጅስቲክ ደረጃ የገዛኢ አሻራ በጉልህ እንደሚታይ አይካድም ሲሉም አክለዋል።

ገና ወደ ትግል ጎራው በተቀላቀሉበት የለጋነት ዕድሜያቸው ላይለያዩ እና ላይከዳዱ ጓዳዊ ጥብቅ መሐላ ነበራቸው እና ሞታቸውም ከሕይወት ዘመን ጓዳቸው፣ የትግል አጋራቸው፣ ወንድማቸው ጀነራል ሰዓረ ጋር በአንድ ቅፅበት ሆነ። ሞትም የኹለቱን መሐላ አለማክበር አልቻለም፤ ሊለያያቸውም አቅም አልነበረውም የሽራፊ ሰኮንዶች መቀዳደም እንጂ ምድር ላይ የነበረው አብሮነታቸው የዘላለም ጉዟቸውም ላይ አልተቀየረም። ሰርክ በባለእንጀራቸው ጀነራል ሰዓረ ቤት መገኘት የሚያዘወትሩት ጡረተኛው ጀነራል ሰኔ 15 ግን እንደሌላው ጊዜ አመሻሽተው በጨዋታ ረክተው ወደ መኖሪያቸው አልተመለሱም። በባልንጀራቸው የቅርብ ጠባቂ የሞትን ፅዋ ተጎንጭተው አምስት ልጆቻቸውን እና ባለቤታቸውን፣ የበርሃ ጓዳቸውን አበባ ዘሚካኤልን በወጉ ሳይሰናበቱ በጀነራል ሰዓረ ቤት አሸለቡ።

ገዛኢ አበራ እስከ ሕልፈተ ሕይወታቸው ድረስ በፐብሊክ ሰርቪስ ውስጥ በቦርድ አመራርነት በማገልገል ሕዝቡን ከትራንስፖርት እጦት እንዲገላገል የበኩላቸውን ጥረት በማድረግ እናት አገራቸውን ሲያገለግሉ የነበሩ የሩቅ አገር ተጓዥ ናቸው። ሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ በተወለዱ በ58 ዓመታቸው ከዚህ ዓመት በሞት ተለይተዋል።
የጀነራል ሰዓረ መኮንን እና የሜጀር ጀነራል ገዛኢ አበራ የቀብር ስነ ስርዓት በትግራይ ክልል መዲና መቀሌ ከተማ ቅዱስ ገብርኤል ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተፈፅሟል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here