13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ለግድብና መስኖ ፕሮጀክቶች ተመደበ

0
718

የኢፌዲሪ መንግሥት ለሚቀጥለው በጀት ዓመት በግንባታ ላይ ለሚገኙ እና አዳዲስ ግድብና መስኖ ፕሮጀክቶች የ13 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በጀት መመደቡ ታወቀ። ለቀጣዩ በጀት ዓመት 2012 የተመደበው በጀት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለውይይት በቀረበበት ወቅት እንደተገለፀው፤ በመገንባት ላይ ለሚገኙ አምስት ግድብ፣ መስኖና ተፋሰስ ፕሮጀክቶች 7 ነጥብ 7 ቢሊዮን ብር በጀት እንደተያዘላቸው የተገለፀ ሲሆን፤ በተጨማሪም በተማሩ ወጣቶች ለሚሠሩ መስኖ ልማት እና ለመስኖ ልማት ቅድመ ዝግጅት ተብሎ በድምሩ 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ተበጅቶላቸዋል።

በጀት ከተያዘላቸው በመሠራት ላይ ያሉ እና ገና ወደ ግንባታ ይገባሉ ተብለው የታሰቡ ግድብ፣ መስኖና ተፋሰስ ፕሮጀክቶች ለዛሬማ ሜይዴይ ግድብ ግንባታ 2 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር፣ ለአርጆ ዴዴሳ ግድብና መስኖ ፕሮጀክት 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር፣ ለመገጭ ግድብና መስኖ ፕሮጀክት 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ብር፣ ለኢትዮ ናይል መስኖና ተፋሰስ ፕሮጀክት 792 ሚሊዮን ብር እና ለጊዳቦ ግድብና መስኖ ፕሮጀክት 651 ነጥብ 2 ሚሊዮን በጀት መያዙን ለማወቅ ተችሏል። ከዚህም በተጨማሪ በቀጣይ በተማሩ ወጣቶች ለሚሠሩ የመስኖና ልማት ብር 2 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር የተበጀተ ሲሆን፤ ለመስኖ ልማት ቅድመ ዝግጅት ተግባራት የሚሆን 1 ቢሊዮን ብር ተደግፏል።

ለመስኖ ልማትና ግድብ ሥራዎች፣ ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ ለተፋሰስ ጥናትና ልማት፣ ለከርሠ ምድር ውሃ ጥናትና ልማት እንዲሁም ለኢነርጂ ልማት ከመንግሥት ግምጃ ቤት በ2011 ከፀደቀው በጀት ብር 5 ነጥብ 6 ቢሊዮን ብር ጭማሪ የገንዘብ ጭማሪ በማድረግ 15 ቢሊዮን ብር ደርሶ፤ ከአጠቃላይ የገንዘብ ምንጮች ግን 17 ቢሊዮን ብር ድጋፍ ተደርጓል። ለቀጣዩ በጀት ዓመት ከተያዘው በጀት በተጨማሪ በመጠጥ ውሃ አቅርቦት ፕግራም በተመለከተ በሥሩ ለሚካሄዱ የተለያዩ ፕጀክቶች ማስፈፀሚያ 1 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል።

የግብርናውን ዘርፍ በመስኖ ልማት ለመደገፍ በአነስተኛ ይዞታ ባላቸው አርሶ አደሮች ለሚካሄድ የተቀናጀ አነስተኛ የመስኖ ልማት ፕሮጀክት በልዮ ሁኔታ 500 ሚሊዮን ብር በጀት ተይዞለታል። በስተመጨረሻም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው እና በሕዝብ እንደራሴዎች ውይይት የተደረገበት 386 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ይሆናል ተብሎ የታሰበው የቀጣዩ ዓመት በጀት ለተጨማሪ ማብራሪያ ለመንግሥት በጀትና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here