ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ የጎዳና ተዳዳሪዎችን ስራ ማስያዝ ጀመረ

0
674
  • ወጣቶቹ ከ1700 ብር እስከ 11000 ብር ደሞዝ መቀጠራቸውም ታውቋል

የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በመልሶ ማቋቋም ያሰለጠናቸውን 155 የጎዳና ተዳዳሪዎች ከ1700 ብር እስከ 11000 ብር ደሞዝ በተለያዩ ድርጅቶች ማስቀጠሩን አስታወቀ። በስልጠና ላይ ያሉ 1000 ወጣቶችም ሥራ እንደተዘጋጀላቸው ተናግሯል፡፡

የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የጎዳና ልጆችን መልሶ የማቋቋም ሥራ ከጀመረ ረጅም ወራት ቢቆጠሩም፣ ክልሎች ቃል በገቡት መሰረት መቀበል ባለመቻላቸው፣ በራሱ ማደራጀት መጀመሩን የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ የሙያ ስልጠና ክትትልና ድጋፍ ቡድን መሪ ትሁት ተፈራ፣ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል፡፡

ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በላይ የሆናቸውን በመልሶ መቋቋም ውስጥ የተካተቱ የአማራ፣ የኦሮሚያና የደቡብ ክልል ወጣቶችን በቴክኒክና ሙያ ስልጠና በልብስ ስፌት፣ በቆዳ ሥራ፣ በወለል ንጣፍ፣ በጂፕሰም ሥራ፣ በቀለም ቅብ፣ በብረታ ብረት ሥራ፣ በእንጨት ሥራና መንጃ ፍቃድ በማውጣት ወደ ሥራ እንዲሰማሩ መደረጉን ትሁት አስታውቀዋል፡፡

የጎዳና ልጆችን ወደስ ባማስገባት እንቅስቃሴ ውስጥ ከቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ጋር በመተባበር በልዩ ድጋፍ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተደረገ ባለው እንቅስቃሴ ውስጥ ስልጠናውን ጨርሰው የሥራ ዕድል የተመቻቸላቸው ወጣቶቹ፣ በአዲስ አበባ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን፣ አዲስ አበባ ቄራ ሥራዎች ድርጅት፣ ኮካ ኮላ ኢስት አፍሪካ ግሩፕና አጋር የጥበቃ ስራዎች ድርጅት ውስጥ እንዲቀጠሩ መደረጉን ከአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

በትምህርታቸው እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸውን ተማሪዎች አፍሪካ ቤዛ ኮሌጅ እንደቀጠራቸው ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት ትሁት፣ እድሜያቸው ለሥራ ያልደረሱትንና በየክልሉ ቤተሰብ እንዳላቸው ላስታወቁት ልጆች ወደ ቤተሰቦቻቸው እንዲቀላቀሉ መደረጉን አክለው ገልጸዋል፡፡

እንደትሁት ገለጻ፣ ተቋቋሚዎቹ ወደ ክልላቸው ሲሄዱ ሙሉ አልባሳት፣ የትራንስፖርት 1000 ብርና መቋቋሚያ 4000 ብር ለእያንዳንዳቸው ተሰጥቷቸዋል፡፡ የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይም ክልሉ ድረስ በመውሰድ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘታቸውን አረጋግጦ ተመልሷል፡፡

ፕሮጀክቱ በመጀመርያው ዙር አምስት ሺሕ ዜጎችን ለማንሳት ዕቅድ ይዞ 3,147 የጎዳና ተዳዳሪዎችን፣ የአዕምሮ ሕሙማንን፣ አረጋውያንን፣ ሠርቶ ማደር የማይችሉ አካል ጉዳተኞችንና የመሳሰሉትን ስምንት ማዕከላት ውስጥ ማስገባቱ የሚታወስ ነው፡፡

ጎዳና ላይ የወደቁና በአስከፊ ድህነት ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን በቀጥታ ድጋፍ የማደራጀት ዕቅድ የወጣው፣ ከሁለት ዓመታት በፊት በዓለም ባንክ የከተማ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ሥር እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የመስራት አቅም ኖሯቸውና ስልጠና ወስደው ለስራ ዝግጁ የሆኑ ወጣቶችና ተመራቂ ተማሪዎች የሆኑት ወጣቶችን ፍላጎት ተጠይቆ ወደ ክልላቸው ለመመለስ የሚፈልጉ ኦሮሚያ ክልል 277፣ አማራ ክልል 269፣ ደቡብ ክልል 384፣ ትግራይ ክልል 26፣ ድሬዳዋ 2፣ ሐረሪ 3፣ አዲስ አበባ 25፣ ቤኒሻንጉል 3፣ ድሬዳዋ 2፣ አፋር 1፣ ሶማሌ 1 ቢኖሩም የነዚህን ወጣቶች ፍላጎት ተቀብሎ ጥሪ ያቀረበው ክልል የትግራይ ክልል ብቻ እንደነበር አዲስ ማለዳ መዘገቧ ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here