ወንድነትስ?

0
601

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

ሴትነት ሴት መሆን ብቻ አይመስለኝም ወይም የስራዓተ ፆታ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ሴትነት በእናትነት ጸጋ ሰጪነት አቅሙ ሀሴትን፣ ደስታንና ሞገስን ከሚያጎናጽፍበት ጽንፍ ‘ፆታዊ ጥቃት’ ተብሎ እስከሚሽሞነሞነው አንገት አስደፊ ሸክምና ጭንቁ ድረስ መሃሉ እንደማይነገር ሰውነት ነው።

አዲስ ማለዳ በሰኔ 15/2011 በፊት ገጽዋ ላይ “ሴትነት’ን እንደ ሥራ ማስገኛ” በሚል ርዕስ ሰፋ ያለ ሐተታ ማስነበቧ ይታወሳል። በዚህም ባለታሪክ እህቶቻችን በሥራ ቦታቸው ይልቁንም የውጭ አገራት በሆኑ ድርጅቶች መደበኛ ሥራን ለማከናወን፣ ለዕድገት አልፎም ለቅጥር ሴትነታcው እንደተጠየቀ ነግረውናል።

ነገሩ በአገራዊና መንግሥታዊ ተቋማት ብቻ የሚሆን ይመስለን ነበር። ግን ከእነዚህ ሴቶች ታሪክ የምንረዳው፤ ወንዶች በተለይም በሥልጣንና በተቋማት ከፍተኛ የአመራር ቦታ ላይ ያሉት፤ የተማሩም ሆኑ ያልተማሩ፣ ፈረንጅ ሆኑ ሐበሻ ኀይላቸውን ሴትነትን ለመግዛት እንደሚጠቀሙ ነው።

እንግዲህ አገር የሚያጫርሰው በጅምላ መፈረጅ ነውና በጅምላ እየፈረጅሁ አይደለም። ነገር ግን ይህ በአብዛኛው እውነት ነው። ከዚህ ቀደም በዚሁ ዓምድ ላይ እንዳነሳነው፤ ጋቢናቸውና ገበናቸው የተለያየ፤ ነገር ግን በሴቷ ‘ቻይነት’ ጋቢናቸው ከብሮ ገበናቸው የተደበቀላቸው ብዙ በሥራቸው ‘ኃላፊ’ የተባሉ ወንዶች አሉ።

በምናውቀው የወንድ ዓለም፤ አንዲት ሴት እውቀትና ችሎታ ኖሯት፤ እንደውም ሊያንሳት እንጂ ሊበዛባት ለማይችል ሥራ፤ ብቁ አይደለሽም ልትባል ትችላለች። ሁሌም አንድ የሚቀድም ወንድ አይጠፋማ! እጅ መንሻ ሴትነቷን የሚጠይቅ። ጉዳዩ ለራስ በሚሰጥ ክብር እና ለተሻለ ኑሮ በሚደረግ ትግል መካከል ይወድቃል።

ይህ ፈተና በሥራ ቦታ ላይ ብቻ የሚያጋጥም አይምሰላችሁ። በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሴት ተማሪዎች ከአልጋ በላይና በታች፤ ኤ እና ኤፍ ተቀምጦላቸው ምረጡ የሚባሉበት ጊዜ ጥቂት አይደለም። ይህ ሴሰኛነት ይባላል። የሚፈልጉትን ጊዜያዊ እርካታ ለማግኘት አማራጭ ሳይጠፋ በሥራ ገበታ ካሉ ሴቶች ላይ የስኬት ጉርሻን መንጠቅ ደግሞ ክፋት ነው።

“ፈቃዴን ፈጽሚና…” ብለው ‘የእጅ መንሻ’ የሚጠይቁ ወንዶች ምን እያሰቡና ምን ዓይነት ስሜት እየተሰማቸው እንደሆን ማወቅ ከሰውነት ውጪ ሌላ ‘ፍጡር’ መሆን የሚፈልግ ይመስለኛል። እነዚህን ሰዎች “ሴት እናትህ፣ እህትህ፣ ልጅህ ናት” ብሎ ነገር አይመልሳቸውም።

ነፍስ ያለው ሕግ እንዲመዘገብና ተፈጻሚነቱም በተግባር እንዲታይ ፍትሕ አካላትን እንጠይቃለን፤ የበደለ እንጂ የተበደለ አንገት እንዳይደፋ። ሌላው ደግሞ ታሪካቸውን ለአዲስ ማለዳ እንዳጫወቷት እህቶቻችን ወርደው ሊያዋርዱ የሚሞክሩትን አደባባይ ማስጣት ነው። ከዛ በተረፈ ጥያቄያችን ይድረስ፤ “ወንድነት ይህ ነው?”

መቅደስ /ቹቹ/
mekdichu1@gmail.com

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here