ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ – የምንከፍለውን ዋጋ ለመቀነስ

0
917

በቅርቡ በአማራ ብሔራዊ ክልል የተካሔደውን “መፈንቅለ መንግሥት” መሰረት በማድረግ መንግሥት ተከታታይና ወቅታዊ መረጃ መስጠት አለመቻሉ ሐሰተኛ መረጃዎች እንዲስፋፉ በማድረግ ወደ ብጥብጥና አለመረጋጋት ሊያመራ ይችላል የሚሉት ቤተልሔም ነጋሽ፥ ኮሽ ባለ ቁጥር ኢንተርኔትና ማኅበራዊ ሚዲያን መዝጋት እስከ መቼ መፍትሔ ይሆናል ሲሉም ይጠይቃሉ።

“የመሪዎቻቸው ሥራ ከእነርሱ ተደብቆ፣ የሕዝቦች ነፃነት በምንም መልኩ የተረጋገጠ አይሆንም” ፓትሪክ ሄንሪ
ባለፈው ቅዳሜ የተፈጠረውን የአገራችንን ታላላቅ ሰዎች ያሳጣ ድርጊትና ያንን ተከትሎ የተፈጠረውን የሐዘንና ግራ መጋባት ሳምንት ችላ ብሎ ስለሌላ ነገር መፃፍ አልሆነልኝም። ፈረንጆች the elephant in the room እንደሚሉት ትልቅ ዱብ ዕዳ ተከስቶ ምንም እንዳልተፈጠረ ቆጥሮ ስለሌላ ጉዳይ ማንሳት ይከብዳል። ጉዳዩን ማየት የምፈልገው ግን ከወጡት እና ካልወጡት መረጃዎች አንፃር አሁንም የጠራ ነገር አለመኖሩ፣ ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ሊሰጥ አለመቻሉ ትክክለኛ ያልሆነ መረጃ እንዲሰራጭ የሴራ ትንተና እንዲስፋፋ ማድረጉን ይህም አሁንም ለመረጃ አሰጣጥ የምንሰጠው ቦታ ዝቅተኛ እንደሆነ እንደሚያሳይ ነው።

ኢትዮጵያ ከጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሟ፣ ከባለአራት ኮኮቡ ጀኔራል ሰዓረ መኮንን እስከ ተራ ወታደሮቿ፣ ከርዕሰ መስተዳድር አምባቸዉ መኮንን (ዶ/ር) እስከ እዘዝ ዋሴና ምግባሩ ከበደ፣ ከአማራ የሰላምና የደኅንነት ኀላፊ ከብርጋዴየር ጄኔራል አሳምነው ፅጌ በጡረታ እስከ ተገለሉት ሜጀር ጄኔራል ገዛኢ አበራ በአንድ ቀን አጥታለች። እንደ አገር ምናልባት በአንድ ቀንና መንግሥት እንደሚለው በተያያዘ፣ በተቀናበረ ሁኔታ ይህን ያህል ማዕረግ ያላቸውን ሰዎች ስናጣ ቢያንስ ባለፉት 40 ዓመታት የመጀመሪያው ይመስለኛል። አገራችን እነኝህን ለማፍራት ስንት ዘመን ጠበቀች?

ከኢንተርኔት መዘጋት፣ በተወሰኑ አካባቢዎች መብራት መጥፋት ጋር ተያይዞ መረጃ እንደልብ አለመገኘት አብዛኛውን ሕዝብ በጨለማ አቆይቶት እንደነበር መናገር ይቻላል። ማኅበራዊ ሚዲያው እስከተቋረጠበት ቅዳሜ ምሽት (ሌሊት) ድረስ በተለይ በፌስቡክ ይለቀቅ የነበረው መረጃ ሁኔታውን ከማብራራት ይልቅ የሚደናግር ነበር። ሌሊት ላይ ተሰጠ በተባለው መረጃ የሆነው ሲታወቅ፣ አራቱ ከፍተኛ ወታደራዊ አመራሮችና የአማራ ክልል ባለሥልጣናት እንደሞቱ ሲሰማም ጉዳዩን ወደ ሴራ ትንተና ለማሳደግ የሚያደርሱ ብዙ ግራ መጋባቶች ነበሩ፤ በመንግሥት አካላትም በኩል የሚሰጡ መግለጫዎች እርስ በእርሳቸው የሚቃረኑ፣ አንድ ጊዜ የተሰጠውን መረጃ የሚያፈርሱ (የጄኔራል ሰዓረን ገዳይ ጉዳይ እዚህ ማንሳት ይቻላል፣ ተገደለ፣ ራሱን አጠፋ ከዚያም በሕይወት አለ ተብሏል) ናቸው። በበኩሌ በተለይ በአማራ ክልል ባለሥልጣናት፣ በኋላም ከክልሉ የኮሙኒኬሽን ኀላፊ የሰማኋቸው መረጃዎች ተዓማኒነት የሚጎድላቸው፣ አላስፈላጊ ዝርዝር ድረታ የበዛባቸው፣ አንዳንዶቹም እርስ በእርስ የሚቃረኑ ናቸው። ዝርዝር ሲበዛና የማይመስል ነገር ሲደጋገም በግድ እመኑ ወይም ላሞኛችሁ የተባለ ያህል ለማመን የሚከብድ ይሆናል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እስከ ቃል አቀባያቸዉ፣ ከክልል አስተዳዳሪዎች እስከ መገናኛ ዘዴዎቻቸው ቅዳሜ በባሕር ዳርና መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮ ከሽፏል። የጠቅላይ ሚንስትር ጽሕፈት ቤት የፕሬስ ሴክሪታሪያት መሥሪያ ቤት ኀላፊ ንጉሱ ጥላሁን ድርጊቱ ተፈፀመ ከተባለበት ሰዓት ጥቂት ቆይቶ ስቱዲዮ ተገኝተው ነገሩን የተደራጀ፣ የተቀናጀ እና በዕቅድ የተመራ ሴራ ብለውታል። ሌሎች መገናኛ ብዙኀን “መፈንቅለ መንግሥት” ከማለት ይልቅ መንግሥት “መፈንቅለ ያለው” ማለትን መርጠዋል። ሌላው ቀርቶ የአማራ ክልል መገናኛ ብዙኀን የፌስቡክ ገጽ ሳይቀር “መፈንቅለ መንግሥት” እያለ በትምዕርተ ጥቅስ ውስጥ ማስቀመጥን መርጦ ነበር። ሸገር ሬዲዮ መፈንቅለ መስተዳድር ሲል ተደምጧል።

ሚዲያው የሐዘን እንጉርጉሮ ከማሰማት መንግሥት ያለውን ከማስተጋባት ውጪ እንዴት ሲል ሲጠይቅ አላየንም። አሁንም ያረጀ ያፈጀ ያንኑ የመንግሥት መግለጫ ደጋግሞ ማሳየት ነው እያየን የነበርነው። በቀብሩ የቀጥታ ሥርጭት ወቅትም አላስፈላጊ የሆኑ ዝርዝሮችና የግል ወሬዎች (ለምሳሌ በአማራ ክልል ባለሥልጣናት የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ) ሲገቡ፣ ሐዘን ላይ ያሉ ቤተሰቦች በጣም ተጋላጭ በሆኑበት ሁኔታ ላይ እያሉ የማሳየት ነገር ታይቷል። ‘ኮመን ሴንስ’ የምንለው እንዲህ አይደረግም የሚለውን የሰውን ክብር መጠበቅ የሚባል ነገር ጋዜጠኞቻችን የረሱበት ሁኔታም ይታያል።

ረቡዕ፣ ሰኔ 19/2011 “በባሕር ዳርና በአዲስ አበባ በግፍ የተገደሉትን ከፍተኛ አመራሮች በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስተላለፉት የሐዘን መግለጫ” የሚል ርዕስ ያለው ባለ ሦስት ገጽ መግለጫ ከጠዋቱ አራት ሰዓት አካባቢ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይፋዊ የፌስቡክና ትዊተር ገጽ ሲለቀቅ ባለኝ መረጃ መሠረት መላው አገሪቱ በኢንተርኔት መዘጋት ውስጥ ነበረች። ኢንርተርኔት ከሚሠራባቸው ጥቂት መሥሪያ ቤቶችና ኤምባሲዎች ውጪ ይሔ መግለጫ ለሰፊው ሕዝብ ተደራሽ አልነበረም።

ከዚያ በፊት “በአገራችን ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተሰጠ መግለጫ” በሚል በማኅበራዊ ሚዲያው አንድ ገጽ አማርኛና ኹለት ገጽ እንግሊዝኛ ጽሁፍ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይፋዊ ገፆች ላይ ወጥቶ የነበረ ሲሆን አሁንም በግሌ ባለኝ መረጃ በኹለቱ መግለጫዎች መካከል ጽሕፈት ቤቱ በማኅበራዊ ሚዲያ ሕዝቡን ለመድረስ አልሞከረም።

ከመግለጫዎቹ በፊትም ቢሆን መንግሥት በቃል አቀባዩ ንጉሡ ጥላሁን በኩል ሙሉ መረጃም ባይሆን መፈንቅለ መንግሥት ተሞክሮ ስለመክሸፉ የቆሰሉ ሰዎችም ስለመኖራቸው ተናግሮ ዝም ባለበት ከሌሎች አካላት መረጃዎች እየወጡ የአማራ ክልል ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስለመገደላቸው፣ ጄነራል ሰዓረ መኮንን ስለመገደላቸው ቀድሞ መረጃ የወጣ ሲሆን የወጣውም ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት አይደለም። ለምሳሌ የዶቸ ቬሌን አንድ ዜና ብናይ
“ጄነራል ሰዓረ መኮንን መገደላቸውን ሕወሓት አረጋገጠ” ይላል ከዚያም፤

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ሰዓረ መኮንን እና ሜጀር ጄነራል ገዛኢ አበራ መሞታቸውን የድምፀ ወያኔ ቴሌቪዥን ጣቢያ አስታወቀ። የጄነራል ሰዓረ እና የሜጀር ጄነራል ገዛኢን ሞት ተከትሎ የሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ዛሬ ንጋት ለስብሰባ ተቀምጠው እንደነበር የዶይቼ ቬለ የመቀሌ ወኪል ሚሊዮን ኀይለሥላሴ ከስፍራው ዘግቧል።

ስብሰባውን ያካሔዱት የሕወሓት ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት ናቸው። ሕወሓት በትግራይ ክልል ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ዛሬ ጠዋት ባሰራጨው መግለጫ በኹለቱ ከፍተኛ ወታደራዊ ሹማምንት ላይ “በቅጥረኞች ግድያ ተፈጽሞባቸዋል” ብሏል። ”

በተጨማሪም ቅዳሜ ማምሻውን የተለያዩ መረጃዎች ሲወጡ ትንታኔዎች ሲሰጡ ቆይተዋል። በዚህ ረገድ ከላይ የጠቀስኩትን ዜናና ሌሎች መረጃዎችን በማየት መናገር የሚቻለው መንግሥትን የወጡት መረጃዎች ቀድመውታል። ከቅዳሜ ሌሊቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የቪዲዮ መልዕክት በፊትም ይሁን በኋላ መረጃዎች ከመንግሥት አካላት መሰጠት ሲጀምሩም ከላይ እንደጠቀስኩት የጄኔራል ሰዓረ ገዳይ ዕጣ ፈንታ ዓይነት አሳሳች እርስ በእርሳቸው የሚጋጩ በመሆናቸው ተዓማኒነቱ ላይ ጥላ ጥሏል። ይህም ከድርጊቱ ጋር ተደምሮ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል።

ማኅበራዊ ሚዲያን በተዘጋበትም ወቅት ጭምር በመስኮት እናይ ለነበርነው፣ በተለይ ዳያስፖራ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የተሞላው ከቅዳሜ ወዲህ ያለው ቆይታው የሚያሳየው መንግሥት እየሰጠ ያለው መግለጫ ለመታመን ብዙ ተግዳሮት የገጠመው መሆኑ ነው። ሕዝቡ መንግሥት በተለያየ አካላትና ባለሥልጣናት በኩል የሚሰጠው መረጃ ተዓማኒነት እንደሌለው ብቻ ሳይሆን በየጊዜው ሲለዋወጥ የነበረውንም መረጃ እየመዘገበ ልብ ይባል ሲል ከርሟል። ገፍቶም የጄኔራል ሰዓረ ገዳይ “መያዙንም ሆነ መሞቱን እንደገና ከሞት መነሳቱን” በሚነግረን የፖሊስ ኀይል እምነት የለንም የተጣራ እውነት ከገለልተኛ አካል እንጠብቃለን እያለም ነው።

ምናልባትም የመንግሥትን ተዓማኒነት ካለ ለማስቀጠል፣ ከሌለ እንደገና ማስመለስ የሚቻለው ከተለያዩ አካላት የተውጣጣ ቡድን ተቋቁሞ መረጃ ማሰባሰብና በዚያ ላይ ተመስርቶ እውነቱን ማሳየት ሲችል ነው።

ካልሆነ ግን ኮሽ ባለ ቁጥር ኢንተርኔትና ማኅበራዊ ሚዲያን መዝጋት እስከ መቼ መፍትሔ ይሆናል የሚለው ትንሽ አሳሳቢ ነው። ተከታታይና ትክክለኛ ወቅታዊ መረጃ መስጠት አለመቻል ሐሰተኛ መረጃዎች እንዲስፋፉ በማድረግ ወደ ብጥብጥና አለመረጋጋት ሊመራ ይችላል፤ የሚያስከትለው ዋጋም ቀላል አይደለም። ከዚህም በላይ በተለይ ለውጪው ማኅበረሰብ በርን ክፍት አድርጎ መረጃ አንዲገኙ ካልተደረገ፣ ቃለ መጠይቅና የመረጃ ጥያቄም ሲኖር መንግሥት መግለጫ መስጠት ሲፈልግ ብቻ ሳይሆን በማንኛውም ሰዓት መልስ መስጠት ይኖርበታል። ካልሆነ ግን ኢትዮጵያ ሦስት ወር ቆይቶ የሔደ ፈረንጅ ሳይቀር የመረጃ ምንጭና በኢትዮጵያ ጉዳይ ተንታኝ ሆኖ ይቀጥላል።

የማጠቃለያ ቃል ከቶማስ ጀፈርሰን
“ሰዎች በቂ መረጃ ሲያገኙ በመንግሥት ላይ ያላቸው አመኔታ ይጨምራል። ነገሮች ወዳልታሰበ መጥፎ አቅጣጫ ቢያመሩ እንኳን፣ መንግሥት እንደሚያስተካክለው ይተማመኑበታል።”

ቤተልሔም ነጋሽ የፖለቲካ ተግባቦት ባለሙያ ናቸው።
በኢሜይል አድራሻቸው
bethlehemne@gmail.com ይገኛሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here