የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር 5 ሺህ ቤቶችን አፈረሰ

0
748
  • በተያያዘም 5 የፖሊስ አባላት በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ታውቋል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሕገወጥ መንገድ በዘመቻ የተሠሩ 5 ሺሕ ቤቶች በ15 ቀናት ውስጥ መፍረስ ካልቻሉ አፍራሽ ግብረ ኀይል በማሰማራት እርምጃ እንደሚወሰድ ባስታወቀው መሰረት፣ ቤቶቹ መፍረሳቸውን ከመስተዳድሩ ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።

በከተማዋ ዳግመኛ ሕገ ወጥ ግንባታ እንዳይከናወን እየተሠራ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ያስታወቁት የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ፌቨን ተሾመ፣ ባለፉት ጥቂት ወራት ፖለቲካዊ ይዘት የነበራቸው የዘመቻ የቤት ግንባታዎች በሰፊው እንደነበሩ አስታውሰዋል። ከእነዚህ ሕገወጥ ገንቢዎችና አንቀሳቃሾች መካከል የነበሩ 5 የፖሊስ አባላትም በቁጥጥር ሥር ውለው ጉዳያቸው በሕግ እየታየ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

ከሕገ ወጥ ግንባታው በስተጀርባ በስውር ተሳትፈዋል የተባሉ ባለሀብቶች፣ የፖለቲካ ሹመኞች፣ እንዲሁም በክፍለ ከተማና ቀበሌዎች ሐሰተኛ የይዞታ ካርታ እየሠሩ የሚሸጡ ግለሰቦችን ከተማ አስተዳደሩ ግብረ ኀይል አቋቁሞ የመለየት ሥራውን እየሠራ መሆኑን ፌቨን ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ የከንቲባ ጽሕፈት ቤቱ የሰጠውን ማብራሪያ ዋቢ አድርጋ በሰኔ 1 ዕትሟ በርካታ ባለሀብቶች ሕገ ወጥ የመሬት ወረራዎችን በመፈፀም እና አነስተኛ ቤቶችን በጭቃ እና በላስቲክ በመገንባት አቅመ ደካሞችን እና ሕፃናትን እንዲኖሩበት በማድረግ እና መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ እንዳይወስድ እንቅፋት መፍጠራቸውን መዘገቧ ይታወሳል።

ከዚህም ጋር ተያይዞ የማጣራት ሥራዎች በተከናወኑበት ወቅትም ሕገወጥ ናቸው በተባሉት ቤቶች ውስጥ የሚኖሩትን ነዋሪዎች ግብረ ኀይሉ ያነጋገረ ሲሆን፤ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች በቀጥታ ገንብተው የገቡ ሳይሆኑ ባለሀብቶችና ሹመኞች ገንብተው ለመሬት መያዣነት ያስቀመጧቸው ሰዎች መሆናቸውን ማረጋገጡን ይፋ አድርጓል።

አብዛኞቹን ቤቶች ሰው የሚኖርባቸው አለመሆናቸውን ያስታወቁት ፌቨን፣ እነዚህን ቤቶች ገንብተውና እራሳቸውን ደብቀው የሚኖሩት ባለሀብቶች፣ አንዳንድ የወረዳና ክፍለ ከተማ ሹመኞችና የጸጥታ አካላት ጉዳዩን ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ ሕገ ወጦቹ ቤቶች እንዳይፈርሱ ትልቅ ዘመቻ አድርገው እንደነበር ይናገራሉ።

ፌቨን እንዳሉት፣ በዚህ ሕገወጥ ድርጊት የተሳተፉ የጸጥታ አካላት ተይዘዋል፤ ባለሀብቶችና ሹመኞችም ጉዳያቸው ተጣርቶ ለሕግ የሚቀርቡ ይሆናል።

ኅብረተሰቡ የእነዚህን አካላት ድብቅ አጀንዳ በመረዳት፣ ወንጀለኞችን ማጋለጥ እንዳለበት ያሳሰቡት ፌቨን፣ እነዚህ ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸው ከመሮጥ ባለፈ ለኅብረተሰቡ የሚፈይዱት አንዳች ነገር አለመኖሩን ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here