የአሃዱ ሬዲዮ ጋዜጠኞች ለሰኔ 27 ተቀጠሩ

0
628

በሦስት የተለያዩ የክስ ይዘቶች የተከሰሱት የአሃዱ ሬዲዮ ጋዜጠኞች ዐቃቤ ሕግ ተጨማሪ ሰው ማስረጃ አለኝ ማቅረብ እችላለሁ በማለቱ ለሰኔ 27 ተቀጠሩ። የበረክ ወረዳ ፍርድ ቤትን ሥም አጥፍተዋል፣ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያምፅ አድርገዋል እና ሚዛናዊ ያልሆነና አድሏዊ ዜና አቅርበዋል በሚል በሰኔ 4/2011 ክስ የተጀመረባቸው አራቱ ጋዜጠኞች፤ ከዐቃቤ ሕግ ለቀረበው ማስረጃ አለኝ ጥያቄ የማቅረቢያ ጊዜ ለሰኔ 27/2011 ቀጠሮ ተሰጥቶታል።

በዚህም መሠረት የፍርድ ቤቱን ሥም ማጥፋትና ሕዝብ በመንግሥት ላይ እንዲያምፅ አድርጋችኋል በሚል የተነሳው ክስ በአራቱንም ጋዜጠኞች የሚመለከት ሲሆን፤ ሚዛናዊ ያልሆነ ዜና አቅርበዋል በሚል የቀረበው ክስ ግን አሃዱ ሬዲዮን ብቻ የሚመለከት እንደሆነ ታውቋል። በዚህም ረገድ ጥበቡ በለጠ በሥራ አስኪያጅነታቸው አሃዱ ሬዲዮን ወክለው ክስ የተመሰረተባቸው ሲሆን ተጨማሪ ሦስት ጋዜጠኞች ማለትም ሊዲያ አበበ፣ ሱራፌል ዘላለም፣ ታምራት አበራ ክስ በተመሰረተበት ጉዳይ ላይ በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ግንኙነት አላቸው የተባሉ ናቸው።

በሰኔ 12/2011 መልስ ይዘው እንዲቀርቡ በፍርድ ቤት ታዘዙት ጋዜጠኞች በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በረክ ወረዳ መልሳቸውን ይዘው መቅረባቸውን የጋዜጠኞች ጠበቃ አበባው አበበ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። ጠበቃው ጨምረው እንደገለፁት የፍርድ ቤቶችን ማቋቋሚያ አዋጅን መሠረት አድርገው ምላሽ የሰጡ ሲሆን፤ ከሳሽ በረክ ወረዳ ፍርድ ቤት ሆኖ በዛው ፍርድ ቤት ጉዳያችን ሲታይ ከአድልዎ ነፃ በሆነ መልኩ የሚካሔድ ፍርድ አይሆንም ማለታቸው ታውቋል። ከዚህም ጋር ተያይዞ አሃዱ ሬዲዮ የሚገኘው በፌደራል ስለሆነ ጉዳያችን በፌደራል መታየት አለበት ሲሉም ምላሻቸውን አሰምተዋል። በኹለተኛ ደረጃ ደግሞ ጋዜጠኛን ያለመከሰስ መብት አንስተው እንደተከራከሩ የሚገልፁት ጠበቃው ጋዜጠኞች በነፃነት የመሥራት መብት እንዳላቸውም ለፍርድ ቤቱ አንስተዋል።

የተከሳሾችን ምላሽ ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ ለሰኔ 19 ቀጠሮ ሰጥቶ አሰናብቷቸው ነበር። በቀጠሮው ቀን መገኘታቸውን ለአዲስ ማለዳ የገለፁት ጠበቃው ፍርድ ቤቱ በሰኔ 12 ያቀረቡትን ምላሽ ውድቅ ማድረጉን እና የእምነት ክህደት ቃላቸውን እንደተቀበላቸው ጨምረው ገልፀዋል። የተከሳሾችን ቃል ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ በዐቃቤ ሕግ በኩል የሰው ማስረጃ መኖሩ በመጠቀሱ ለሰኔ 27 እንዲያቀርብ የጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዚሁ ቀን በበረክ ወረዳ የተገኙት ተከሳሾች ፍርድ ቤቱ እያንዳንዳቸው በ5 ሺሕ ብር ዋስ እንዲወጡ የወሰነ ሲሆን በአጠቃላይ 20 ሺሕ ብር ከፍለው መውጣታቸውን ምንጮች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በተጠቀሰው ጉዳይ ለመጀመሪያ ጊዜ ግንቦት 16/2011 ታምራት አበራ የተባለውን የአሃዱ ሬዲዮ ባልደረባን ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ አባላት መሥሪያ ቤቱን በመክበብ ይዘውት መሔዳቸው ይታወሳል።

ቅጽ 1 ቁጥር 34 ሰኔ 22 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here