“. . . ማስረጃ ሳንይዝ አናስርም” የት ገባ?

0
596

ሰኔ 15 የተሞከረውንና የአምስት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትን ሕይወት የነጠቀውን በአማራ ክልል የተካሔደውን “መፈንቅለ መንግሥት” ተከትሎ በተለይ በአማራ፣ በኦሮሚያና በአዲስ አበባ መንግሥት ጠርጥሪያቸዋለሁ ያላቸውን ግለሰቦች በጅምላ ማሰሩን በተመለከተ ተቃራኒ ሐሳቦችና አቋሞችን በዜጎችም በፖለቲከኞችም ዘንድ አሰናዝሯል።

የጅምላ እስራቱ በሕጋዊነት ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱትን የፖለቲካ ፓርቲዎች ጭምር ያካተተ በመሆኑ ተቃውሞም አስነስቷል። እንደማሳያም የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) አመራርና አባላት ላይ በክልላቸውና በኦሮሚያ ውስጥ መፈጸሙን በማንሳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የፈረሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች የቃል ኪዳን ሰነድ እየጣሱ ነው ሲሉ ከሰዋል። ንቅናቄው የሥራ አስፈፃሚ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ የሆኑት ክርስቲያን ታደለ አንድ ቀን ታስረው መፈታታቸውንም አስታውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በአንድ ወቅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተገኝተው ሪፖርት ባቀረቡበትና በምክር ቤት አባላት የተነሱላቸውን ጥያቄ መሰረት በማድረግ ምላሽ በሰጡት ወቅት ከዚህ በኋላ ያለበቂ ማስረጃና ምርመራ ሰዎችን ወደ እስር ቤት ማጋዝ እንደማይኖር የተናገሩትን መነሻ በማድረግ የሐሳብ ፍጭቶች ተስተናግደዋል።

በአንድ ወገን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቃላቸውን አጥፈዋል፤ ወደ አምባገነንነትም እየተንደረደሩ ነው ሲሉ የሚወቅሷቸው አሉ። በሌላ ወገን ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትሩና መንግሥታቸው እስከዛሬ ዳተኛ የሆኑበትን ሕግ የማክብርና የማስከበር፣ የሕግ ልዕልና የመጠበቅ የማያዳግም እርምጃ በመውሰድ እየተንደረደሩ ነው ሲሉ ያሞግሷቸዋል። እንደዚህ ዓይነት እርምጃ ቀደም ብለው ቢወስዱ ኖሮ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፈለውንና አሁን ደረስ የተንሰራፋውን ስርዓት አልበኛነት በእንጭጩ በቀጩት ነበር ሲሉም ተችተዋልቸዋል።

ደጋፊዎቻቸው በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰኞ፣ ሰኔ 24 የዓመቱን የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ከማቅረብ በተጨማሪ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ በሰጡበት ወቅት ከዚህ ቀደም አሳይተውት በማያውቁት ጠንካራ ድምፀትና ማስተንቀቂያ በኢትዮጵያ አንድነት የሚመጣ ካለ ግንባራችንን እንሰጣለን ሲሉ የተደመጡ ሲሆን ከእንግዲህ ወዲ የሕግ ሉዓላዊነትን በማስከበር ዙሪያ ያላቸውን እንደማይደራደሩ ያላቸው አቋም በግልጽ አንፀባርቀዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አቋምና ጠንከር ያለ ንግግር በአንዳንዶች ዘንድ “እንዲህ ነው እንጂ ቆምጨጭ ማለት!” የሚል ሙገሳን በሌሎች ዘንድ ደግሞ “በቃ አምባገነንነታቸው ለየላቸው!” አስብሎ በተቃራኒው አስቁሟል። በርግጥ የትኛው ትክክል ነው የሚለውን የሚመልሰው ጊዜ ይሆናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here