የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ የሙከራ ጊዜን ወደ ሦስት ወር ከፍ አደረገ

0
613
  • በስድስት ወራት ውስጥ ስምንት ቀናት ማርፈድ ከሥራ ያሰናብታል
  • በወሲዊ ትንኮሳ ምክንያት የሥራ ውላቸውን የሚያቋርጡ ሰዎች የስንብት ክፍያዎች ተጠቃሚ አይሆኑም

ለኹለት ዓመታት የተለያዩ ክርክር ሲደረግበት ቆይቶ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተላከው ረቂቅ የአሠሪ እና የሠራተኛ አዋጅ ቀደም ሲል የነበረውን የሙከራ ጊዜ ገደብ ከ45 ቀናት ወደ 60 የሥራ ቀናት ከፍ አደረገ። የሕግ ለውጡ ቀደም ሲል የነበረውን የአንድ ወር ተኩል የሙከራ ጊዜ እጥፍ በማድረግ ወደ ሦስት ወር ገደማ ያሳደገ ነው።

ለማሻሻያው እንደ ምክንያትነት የሚጠቀሰውም በርካታ አሠሪዎች እንደዓላማው የሠራተኞችን አቅም ለማወቅ በቂ ጊዜ ባለመስጠቱ አዲስ ሠራተኞች ቋሚ ሆነው ከመቀጠራቸው በፊት ብቃታቸውን ለማወቅ የማያስችል እንደሆነ በተደጋጋሚ በመግለፃቸው ነው። በተለይም ወደ ኢንዱስትሪው ዘርፍ በሚደረገው ሽግግር በርካታ የሥራ መደቦች በባለሞያዎች የሚያዙ ሲሆን አዲስ ሠራተኞ ለሥራ መደቡ ያላቸውን ተስማማነት ከማወቅ ባሻገር ለሠራተኞቹ ክትትል እና ድጋፍ በማስፈለጉ መሆኑንም የሕግ አርቃቂውን ሐሳብ የያዘው ማስታወሻ ማብራሪያ ያትታል።

የዓለማቀፉ የሠራተኞች ድርጅት ባወጣው መለኪያ መሰረት ማንኛውም የሙከራ ጊዜ ከ6 ወራት ሊበልጥ እንደማይችል ያስቀመጠ ሲሆን የሥራ መደቡ ከፍተኛ ብቃትን የሚጠይቅ ሲሆን ግን እስከ 12 ወራት ከፍ ሊል እንደሚችል ይደነግጋል። በአሰሪና ሠራተኛ ሕጎች እና መብቶች ላይ ዓለማቀፍ ገዢ የሆነው የድርጅቱ ሕግ መደበኛው የሙከራ ጊዜ 60 ቀን እንደሆነም ያስቀምጣል።

በተመሳሳይ የጸደቀው አዋጀ አንድ ሠራተኛ ያለበቂ ምክንያት ከሥራው በስድስት ወር ውስጥ ስምንት ጊዜ ካረፈደም ከስራው ያለማስጠንቀቂያ ሊሰናበት እንደሚችል የሚደነግገው ረቂቅ አዋጁ በስድስት ወር ውስጥ በተከታታይም ሆነ በተለያየ ጊዜ ከሥራ መቅረት ለአሠሪው ተመሳሳይ መብት ይሰጣል።

ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የማብራሪያ ማስታወሻ እንደሚያስዳው ያለፈው አዋጅ አምስት ተከታታይ የሥራ ቀናት ከሥራ ገበታው ላይ ያልተገኘን ሠራተኛ ያለማስጠንቀቂያ ለመሰናበት የተቀመጠው አገላለፅ ከሥራ መቀረትን የሚያበረታታ ሆኖ በመገኘቱን ያብራራል። በተለይም አንዳንድ ሠራተኞች ለአራት ተከታታይ ቀናት ከሥራቸው በመቅረት በአምስተኛው ቀን በመመለስ የሕጉን ክፍተት ለመጠቀም መሞከራቸው የሥራ ዲሲፕሊን መጓደል እንዲያጋጥም ምክንያት መሆኑን ይገልፃል።

በተጨማሪም አዋጁ ለመጀመሪያ ጊዜ የዝቅተኛ የደሞዝ ወለልን በመወሰን አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱን በማብራራት በመንግሥት የሥራ ዘርፍ የተቀመጠውን የዝቅተኛ የደሞዝ ወለል ወደ ግል ዘርፍም እንዲመጣ መወሰኑን ያትታል። ከነፃ ገበያ መርሆች አንፃር ለረጅም ዓመታት በተለይ ኢንዱስትሪዎች መስፋፋት እና የዝቅተኛ ደሞዝ ተከፋይ የግሉ ዘርፉ ተቀጣሪዎች ቁጥር ማሻቀብን አስመልክቶ የዝቅተኛ ደሞዝ ሕግ ያስፈልጋል ወይም አያስፈለግም የሚሉ ክርክሮች ሲደረጉ መቆየታቸው ይታወሳል።
በጉዳዩ ላይም ባለሞያዎች እና በምክር ቤቱ መካከል ሰፊ የሐሳብ ልውውጥ መደረጉንም የአዋጁ ማብራሪያ ያስረዳል። ዝቅተኛ የደሞዝ መጠን ከተለዋዋጭነት አንፃርም ወደፊት በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚያወጣው ደንብ በሚቋቋም ኮሚቴ እንደሚወስን እና ኮሚቴውም በያጊዜው በባለሞያዎች በማስጠናት በየወቅቱ ዝቅተኛ የደሞዝ መጠንን ያስተካክላል።

አዋጁ ከዚህ ቀደም በቅነሳ ወቅት ለነፍሰጡር እናቶች የሚደረገውን ጥበቃ በማስፋት ጥበቃው ለሕጻናትም እንደሚያስፈለጉ በማመን አንድ እናት ከወለደችበት እስከ አራት ወር ባለው ጊዜ የሚደረግ የሥራ ቅነሳ በሚኖርበት ወቅት የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች እንዲከበርላቸውም ይደነግጋሉ።

በጨማሪም የወሊድ እረፍትን ወደ 4 ወር ከፍ ያደረገው አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ዘንድ የተፈፃሚነት ጥያቄ ተነስቶበታል። የወሊድ ዕረፍቱ ተከታታይ በሚል የተሸሻለ ሲሆን ይህም ከዚህ ቀደም የበዐል እና የዐረፍት ቀናትን የማይቆጠር ሲሆን አዲሱ አዋጅ ተከታታይ ቀናት ብቻ ማለቱ ከተወካዮች ዘንድ ተቃውሞን አስተናግዷል።
አዋጁ ለፅንስ መቋረጥ ፍቃድ ዕውቅና በመስጠት “ማንኛዋም ነፍሰጡር ሠራተኛ የፅንስ ማቋረጧን በሐኪም ማስረጃ ሲረጋገጥ በሚሰጣት የሕክምና ላይ በአዋጁ መሰረት የተቀመጡት የደመወዝ ቅነሳ አይመለከተታቸውም” በማለት በፈቃዱ ጊዜ ሙሉ የደመወዝ ክፍያ እንዲያገኙ በግለፅ ያስቀምጣል።

ወሲባዊ ትንኮሳን በግልፅ ማመልከቱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ማንኛውም ሠራተኛ ወሲባዊ ትንኮሳ ከደረሰበት ምንም ዓይነት ማስጠንቀቂያ መስጠት ሳይጠበቅበት ሥራውን መልቀቅ እንደሚችል በግልጽአመልክቷል። በወሲዊ ትንኮሳ ምክንያት የሥራ ውላቸውን የሚያቋርጡ ሰዎች የስንብት ክፍያዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑም ይደነግጋል።

ለአዋጁ መሻሻል እንደምክንያት የተቀመጠውም አገሪቱ እያስመዘገበችው ካለው ለውጥ አንፃር እና ከተነደፉ የልማት ፖሊሰዎች ጋር አብሮ የሚራመድ ሕግ በማስፈለጉ እንደሆነ ለሕዝብ እንደራሴዎቹ የቀረበው የውሳኔ ሐሳብ ያስረዳል። የአሰሪና ሠራተኛ የሥራ ላይ ግንኙነት ከሽኩቻ የፀዳ እና ሰላማዊ እንዲሆን ታስቦ ተዘጋጀ እንደሆነ እና ይህም ሠራተኛው በሙሉ አቅሙ እና ፍላጎቱ ሥራው ላይ በመሆን ትርፋማነቱን እንዲያሳድግ ታስቦ መሆኑን ይገልፃል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here