የክልል የመሆን መብት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚና

0
1247

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቀርቡ የዓመቱን የሥራ አፈፃፀም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበትና ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡትን ማብራሪያ መነሻ በማድረግ የሲዳማ ዞን ጨምሮ በደቡብ ክልል የሚገኙ ዐሥር ዞኖች ያነሱትን በክልል የመደራጀት መብት ከኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እና ሌሎች የአገሪቱን ሕጎች መሰረት በማድረግ ማርሸት መሐመድ ጉዳዩን መርምረውታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የመንግሥታቸውን የ2011 አፈጻጸም ሪፖርት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡበት ወቅት ከምክር ቤቱ አባላት ከቀረቡላቸው ጥያቄዎች አንዱ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል በሚገኙ ዞኖች እየቀረቡ ያሉ የክልልነት አደረጃጀት ጥያቄዎችን የተመለከተ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩም መንግሥት የክልልነት ጥያቄዎችን መቀበሉን ገልጸው አፈጻጸሙን በተመለከተ የምርጫ ቦርድ በአግባቡ እስኪ ደራጅ እየተጠበቀ መሆኑን ከገለጹ በኋላ የቀረቡ ጥያቄዎችን መንግሥት በሕጋዊ መንገድ እንደሚያስተናግድ፣ ነገር ግን ከሕጋዊ አግባብ ውጪ የሚደረጉ ማናቸውንም እንቅስቃሴዎች ላይ መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አጽኖት ሰተው ሲናገሩ ተደምጠዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያ በግልጽ ባይጠቅስም ትኩረቱ በተለይ በሲዳማ ዞን ሐምሌ 11/2011 ክልልነትን በራስ ለማወጅ በብሔሩ ተወላጆች እየተደረገ የሚገኘውን ዝግጅት የተመለከ እንደሚሆን መገመት ይቻላል። የሲዳማ ብሔር ተወላጆች፣ አክቲቪስቶች እንዲሁም አንድ አንድ የዞኑ መንግሥት አስተዳደር አባላት፣ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር ጨምሮ፣ በተለያዩ መድረኮች እንደሚገልጹት በዞኑ እና ክልሉ ምክር ቤቶች ውሳኔ መሠረት ሕዝበ ውሳኔ እስከ ሐምሌ 11/2011 መካሔድ እንዳለበት የሚከራከሩ ሲሆን፤ ነገር ግን ሕዝበ ውሳኔው በተባለው ጊዜ ውስጥ ባይከናወን ዞኑ የራሱን ክልል የማወጅ መብት እንዳለው እየተከራከሩ ይገኛሉ።

ታሪካዊ ዳራ
ኢትዮጵያ ከሦስት ሺሕ ዓመታት በላይ ታሪክ ባለቤት እና በተለያዩ ዘመናት የተፈራረቁ መንግሥታት በየራሳቸው ሥርዓት ያስተዳድሯት አገር ናት። በመንግሥት ስርዓት ታሪክ እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ድርስ ያልተማከለች ሆና፤ ለማዕከላዊ ንጉሠ ነገሥት የሚገብሩ ጠንካራ ሊባሉ የሚችሉ ክልላዊ ገዢዎች ወይም ንጉሦች በተለያዩ የአገሪቱ ግዛቶች የነበሩ ነበሩ። በንጉሠ ነገሥቱና በክልላዊ ገዢዎች መካከል የነበረው ግንኙነትም በጣም የላላ ነበር። አሁን የማዕከላዊውን (የፌደራሉን) መንግሥት እጅ ከሚያዩ ክልሎች በተቃራኒው ያኔ የነበሩ ክልላዊ ገዢዎች ለማዕከላዊው ንጉሠ ነገሥት ግብር የሚያስገቡ፣ በጀት ደጓሚዎች ነበሩ ቢባል ማጋነን አይሆንም። ያልተማከለ መንግሥታዊ ሥርዓት ለረዥም ዓመታት የቆየ ቢሆንም በተለይ ከዘመነ መሳፍንት ምስቅልቅል በኋላ የተነሱ ንጉሠ ነገሥቶች ክልላዊ ገዥዎችን አዳክመው፣ በአፄ ኀይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት ከ1923 ጀምሮ የስርዓቱን ግብዓተ መሬታቸው ተፈጽሟል። ከ1923 ሕገ መንግሥት ከታወጀ በኋላ የአገሪቱ አስተዳደር ሙሉ በሙሉ የተማከለ ሆኖ የክልል ገዢዎችም በንጉሠ ነገሥቱ በተሸሙ አገረ ገዥዎች ቀስ በቀስ እየተተካ መጣ። ዘውዳዊ ሥርዓቱን ያስወገደው ደርግም አሃዳዊውን የተማከለ ሥርዓት እስከ 1983 አስቀጥሏል።

ከደርግ በትረ ሥልጣኑን የነጠቀው ሕወሐት/ኢሕአዴግ “በኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ለመክፈት” በሚል መሪ ሐሳብ የመንግሥት ሥርዓቱ የሚመሠረተው “የሁሉም ሕዝችን የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት” መርህ ላይ እንደሆነ በ1983 ባወጣው የሽግግር ወቅት ቻርተር አወጀ። አዋጁን ተከትሎ በወጣው “ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን” ማቋቋሚያ አዋጅ (ቁጥር 7/1984) መሠረትም በወቅቱ ዕውቅና ያገኙ 65 ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ባልተማከል አስተዳደር በ14 ከልሎች ተዋቀሩ። ከአዲስ አበባ እና ሐረር ከተሞች በቀር 12ቱ ክልሎች የተዋቀሩ ባብዛኛው በብሔር መሠረት ላይ እንደሆነ አዋጁ ያመለክታል። ከተቋቋሙት 14 ክልሎች መካከል አምስቱን ክልሎች (ከክልል 7 -11 ያሉት) የያዙት ደግሞ አሁን በደቡብ ክልል ሥር የተዋቀሩት ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ነበሩ።

የሽግግር ወቅት ብሔርን መሠረት ያደረገ የክልል አወቃቀር እና ስርዓት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትም በአብዛኛው የቀጠለ ሲሆን፤ ከአወቃቀር አንጻር የተቀየረ ነገር ቢኖር የክልሎችን ቁጥር ወደ ዘጠኝ ዝቅ ማድረግ ነው። በቅነሳውም በሽግግር ወቅት በ5 ክልሎች ተዋቅረው የነበሩ በደቡቡ የአገሪቷ ክፍል የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች “ተደምረው” አንድ “የደቡብ ብሔር, ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” ክልልን ሲመሰርቱ፣ አዲስ አበባ ከክልልነት ዝቅ ተደርጋ በከተማ አስተዳደርነት እንድትቀጥል ሆኗል።

ክልል የማቋቋም መብት
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የክልሎችን ቁጥር በ9 ቢወስንም፣ ነገር ግን በክልሎቹ ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸው ይደነግጋል (አንቀጽ 47(2))። ሁሉም ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ያለአንዳች ገደብ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው። ሕገ መንግሥቱ “ለብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ” ግልጽ ትርጉም ባይሰጥም፤ ትርጓሜው ምንም ቢሆን ግን ክልል የማቋቋም መብት ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። የብሔር፣ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ኢኮኖሚያዊም፣ ፖለቲካዊም ሆነ አስተዳደራዊ አቅም እንዲሁም ሌሎች አገራዊ እሳቤዎች ከግምት አይገቡም።
በሽግግር ወቅት አስተዳደር ጊዜ የተወሰኑ ብሔረሰቦች በወረዳ ደረጃ እና ከዚያ በላይ ያሉ አስተዳደራዊ መዋቅር ማቋቋም አይችሉም ነበር፤ ለምሳሌ፡ ኩናማ፣ ሺናሻ፣ ዘይሴ፣ ጊዶሌ፣ ቦዲ፣ ፀማይ፣ ሚኒት፣ ወዘተ። በወቅቱ እነዚህ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች ወይም ሕዝቦች የራሳቸውን አስተዳደራዊ መዋቅር እንዳያቋቁሙ ሙሉ በሙሉ መከልከላቸው ከመብት አንጻር ጥያቄ ሊነሳበት ይችላል። ነገር ግን ምንአልባትም ክልከላው በወቅቱ እነዚህ ማኅበረሰቦች የነበሩበትን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ አስተዳደራዊ እና ፖለቲካዊ የዕድገት ደረጃ ታሳቢ እንዳደረገ መገመት ይቻላል።

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ሁሉም ብሔርና ብሔረሰብ የራሱን ክልል የመመሥረት መብት ማጎናጸፉ በመርህ ደረጃ ተገቢ ነው ቢባል እነኳን፣ ለመብቱ አፈጻጸም የተቀመጠው ሥነ ስርዓት ልልነት እና ጥያቄው የብሔሩ ወይም ብሔረሰቡ ጉዳይ ብቻ ተደርጎ መቀመጡ እና አገራዊ እሳቤዎች ሙሉ በሙሉ ወደ ጎን መደረጋቸው እንደ ሕገ መንግሥት ክፍተት ሊታይ ይችላል። ይህ ማለት ግን ክልል የመሆን ጥያቄ በጥብቅ ገደቦች ይታጠር ማለትም አይደለም። አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ክልል ለመሆን መብቱ ቢሆንም፤ ነገር ግን ከሀገራዊ ጥቅም እና ተገቢነት አንጻር ደግሞ ለክልልነት መሟላት ያለባቸው objective መስፈርቶች መኖር አለባቸው
ክልል የማቋቋም ጥያቄ እና ሒደቶቹ
የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት የክልልነት ጥያቄ በጠያቂው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ምክር ቤት በኹለት ሦስተኛ ድምጽ ሲጸድቅ፣ በጽሁፍ ለክልሉ ምክር ቤት መቅረብ አለበት ይላል (አንቀጽ 47 (3ሀ))። የክልሉ ምክር ቤት ደግሞ ጥያቄው በደረሰው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስት ሕዝበ ውሣኔ ያደራጃል። ክልል የመመስረት ጥያቄው በብሔሩ፣ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ሕዝበ ውሳኔ በአብላጫ ድምጽ ሲደገፍ እና የክልሉ ምክር ቤት ክልልነት ለጠየቀው ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ሥልጣኑን ሲያስረክብ አዲሱ ክልል ወደ ፌደራሉ አባል ክልሎችን ያለ ቅድመ ሁኔታ ይቀላቀላል።

ብሔሩ ወይም ብሔረሰቡ የሚገኝበት ክልልም መንግሥትም ሆነ የፌደራሉ መንግሥት ሕዝበ ውሳኔ በማደራጀት ሒደቱን ከማስተባበር ባለፈ በውሳኔ ሰጪነት መሳተፍ አይችሉም። የዚህ ሕገ መንግሥታዊ ሥነ ስርዓት ጉድለት በፌደራል መንግሥት እንዲሁምን አገሪቷ ላይ በአጠቃላይ የሚኖረው ተጽዕኖ በጥልቀት የታሰበበት አይመስልም። በሌላ በኩል፣ ወረዳ እና ዞን መዋቅር ጥያቄ ተገቢነቱ ተጠንቶ እና ጥያቄው የቀረበለት ክልል ምክር ቤት ተወያይቶበት በሚወሰንበት አገር፤ የክልል ጥያቄ ያለምንም ክልላዊ ወይም አገራዊ ምዘና በጠያቂው ብሔር ወይም ብሔረሰብ ሕዝበ ውሳኔ ብቻ እንዲጸድቅ ማድረግ ምክንያታዊነቱ ግልጽ አይደለም።

ይህ ማለት ግን ክልል የመሆን ጥያቄ በጥብቅ ገደቦች ይታጠር ማለትም አይደለም። አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ክልል ለመሆን መብቱ ቢሆንም፤ ነገር ግን ከሀገራዊ ጥቅም እና ተገቢነት አንጻር ደግሞ ለክልልነት መሟላት ያለባቸው objective መስፈርቶች መኖር አለባቸው። አለበለዚያ ግን እያንዳንዱ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ በጠየቀ ቁጥር ክልል ከተሰጠው፣ ከሁሉ በላይ ጉዳቱ ለሀገሪቷ መሆኑን ለመገንዘብ ከባድ አይሆንም።

ክልልነት እና የሕዝበ ውሳኔ ቀነ-ገደብ
ሕገ መንግሥቱ የክልልነት ጥያቄ የቀረበለት የክልል ምክር ቤት ጥያቄው በደረስ በአንድ ዓመት ጌዜ ውስጥ ሕዝበ ውሣኔ ያደራጃል ይላል። በዚህም መሠረት ሕዝበ ውሳኔ የሚደረግበት ጊዜ ገደብ መቆጠር የሚጀምረው ጥያቄው ለክልሉ ምክር ቤት ከደረሰበት ቀን ጀምሮ እንጂ የክልልነት ጥያቄው በብሔሩ፣ ብሔረሰቡ ወይም ሕዝቡ ምክር ቤት ከጸደቀበት ቀን ጀምሮ አይደለም።

እዚህ ጋር የሲዳማን ብሔር የክልልነት ጥያቄ እና ከሕዝበ ውሳኔ መዘግየት ጋር ተያይዞ በብሔሩ ልኂቃን ሕዝበ ውሳኔ ባይካሔድም ብሔሩ በሐምሌ 11/2011 የራሱን ክልልነት እንደሚያውጅ እየቀረበ ያለውን ሐሳብ በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ አንጻር እንመልከት። የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ በብሔሩ (በዞኑ) ምክር ቤት የጸደቀው በሀምሌ 11/2010 ነው። ጥያቄውን የደቡብ ክልል ምክር ቤት ተቀብሎ ያጸደቀው በጥቅምት 23/2011 ሲሆን ምክር ቤቱ ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሔድ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ያቀረበው ደግሞ በሕዳር 12/2011 ነው።

እንግዲህ ከላይ በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ አንጻር የሲዳማ ክልልነት ጥያቄ ላይ ሕዝበ ውሳኔ መካሔድ ያለበት የደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄውን ተቀብሎ ካጸደቀበጽ ከጥቅምት 23/2011 ጀምሮ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ፣ የብሔሩ ተወላጆች የሕዝበ ውሳኔው ቀን በሐምሌ 11/2011 እንደሚያበቃ በመጥቀስ እያቀረቡ ያሉት መከራከሪያ ሕገመንግሥታዊነት ጥያቄ የሚነሳበት ነው።

ክልልነት ጥያቄ ላይ የሚቀርቡ ቅሬታዎች መፍቻ መንገዶች
አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ የክልልነት ጥያቄ በራሱ ምክር ቤት በ2/3ኛ ድምጽ አስወስኖ ለክልሉ ምክር ቤት ቢያቀርብም፣ ጥያቄው ግን በክልሉ ምክርቤት ባግባቡ ሳይፈጸም ቀርቶ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ፣ ሕዝበ ውሳኔው በተባለው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ባይከናወን፣ የተካሔደ ሕዝበ ውሳኔው ላይ ማንኛውም ዓይነት ቅሬታ ቢኖር፣ የክልሉ ምክር ቤት ሥልጣን ለጠያቂው ብሔር ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ባያስረክብ፣ ወዘተ.
ለእነዚህ ጥያቄዎች በሕገመንግሥቱ የተቀመጠው መፍትሔ አቅጣጫ ቅሬታውን ወደ ፌዴሬሽን ምክር ቤት መውሰድ ነው። የፌዴሬሽን ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄም ሆነ ሌሎች የራስን ዕድል በራስ የመወሠን መብትን በተመለከተ ለሚነሱ ጥያቄዎች ሁሉ በሕገ መንግሥቱ መሠረት መርምሮ እንዲወስን ሥልጣን ተሰቶታል (አንቀጽ 62 (3))።

መታወስ ያለበት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ሚና
የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ለማጠናከርና ሥልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በወጣው አዋጅ ቁ.251/2001 መሠረት የክልልነት ጥያቄ አፈጻጸም ላይ ያለ ቅሬታ በሁለት ዓይነት መንገድ ይስተናገዳል። የመጀመሪያው አጠቃላይ የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን የሚመለከት ሲሆን፣ ኹለተኛው ሕዝበ ውሳኔን በተመለከተ የሚነሳ ቅሬታ የሚፈታበት ነው።

ክልልነትን ከመመስረት መብት ጋር ተያይዞ የሚነሳ ማናቸውም ቅሬታ (ሕዝበ ውሳኔን ከሚመለከቱ በቀር) በመጀመሪያ መቅረብ ያለበት በክልሉ በራሱ ለሚገኙ የተለያዩ የመስተዳድር እርከኖች ነው (አንቀጽ 20)። እዚህ ጋር አዋጁ የትኛው መስተዳድር እርከን ላይ ቅሬታው መቅረብ እንዳለበት እንዳለበት ዝርዝሩ ክልሉ በሚያወጣው ሕግ ይወሰናል በሚል ያለፈዋል። የሆነው ሆኖ ጥያቄው የቀረበለት ክልል ጉዳዩን በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መወሰን ይኖርበታል። የቀረበው ጥያቄ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ውሣኔ ካልተሰጠው ወይም በተሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታ ካለ ግን ጉዳዩ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሊቀርብ ይችላል። የፌዴሬሽን ምክር ቤትም በይግባኝ የቀረበለትን ቅሬታ በኹለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይኖርበታል። ይህ ሒደት የክልል ማቋቋምን በተመለከት የሚነሳ ቅሬታ ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ከማቅረቡ በፊት ክልላዊ መፍትሔ አሟጦ መጠቀም እንደሚያስፈልግ ያመለክታል።

ሕዝበ ውሳኔት በተመለከተ፣ ሕዝበ ውሳኔ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ካልተካሔደ ይህ በራስ የሕገ መንግስት ጥሰት ነው። ነገር ግን በዚህ ምክንያት ቅሬታ ካለ፣ በሕዝበ ውሳኔው በሚካሔድበት ሒደት ላይ ወይም በውጤቱ ላይ ቅሬታ ካለ ቅሬታው ክልልነት ጥያቄ ባቀረበው የብሔረሰብ ምክር ቤት በኩል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት በጽሑፍ ሊያቀርብ ይችላል (አንቀጽ 20(2))። የዚህ ዓይነት ቅሬታ ለፌዴርሽን ምክር ቤት በማንኛውም ጊዜ ሊቀርብ የሚችል ሲሆን፣ ምክር ቤቱም ቅሬታው ላይ በኹለት ዓመት ጊዜ ውስጥ ውሣኔ የመስጠት ግዴታ አለበት።

መደምደሚያ
ሕገ መንግሥቱ የራስን ዕድል በራስ መወሰን መብትን፣ የራስን ክልል የማቋቋም መብትን ጨምሮ፣ ለሁሉም ብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝብ በእኩልነት ያረጋግጣል። የክልል ጥያቄ አፈጻጸም በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ ያስቀመጠው ሥነ ስርዓት አገራዊ ሁኔታዎች ታሳቢ የሚደረጉበትን ሁኔታ ወደጎን በመተው ክልል ጠያቂውም፣ ውሳኔ ሰጪውም ብሔሩ ወይም ብሔረሰቡ ብቻ እንዲሆን መደረጉ ሕገ መንግሥታዊ ክፍተት ነው። ይህም ሆኖ ግን፣ የክልልነት ጥያቄን በተመለከተ በሕገ መንግሥቱ እና ሕገ መንግሥቱን መሠረት መሠረት በማድረግ በወጡ ዝርዝር ሕጎች የተቀመጡ ሕጋዊ ስርዓቶችን አክብሮ መሔድ የሁሉም ግዴታ ይሆናል።

ክልል ከማቋቋም መብት ጋር ተያይዞ የሚኖር ማንኛውም ጥያቄ፣ በተለይ ከሕዝበ ውሳኔ መዘግየት ወይም አካሔድ ጋር የሚነሳ ቅሬታ፣ ቢኖር በሕገ መንግሥቱ መሠረት ጉዳዩን የማየት እና የመወሰን ሥልጣን ለተሰጠው አካል – ለክልል ምክር ቤት ወይም ለፌደሬሽን ምክር ቤት – ቀርቦ መወሰን ይገባዋል። ከዚህ ውጪ አንድ ብሔር፣ ብሔረሰብ ወይም ሕዝብ ቅሬታውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሳያቀርብ ወይም ጉዳዩ ውሳኔ ሳያገኝ የክልልነት ጥያቄው በጊዜ አልተመለሰም ወይም ሕዝበ ውሳኔ በተቀመጠው ጊዜ አልተካሔደም በሚል መነሻ በራሱ ውሳኔ የራሱን ክልል የማደራጀት ወይም የማወጅ ሕጋዊ ሥልጣን የለውም፤ ቢያደርግም ሕገመንግሥታዊ ተቀባይነት አይኖረውም። ለዚህም ይመስላል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የክልልነት ጥያቄን አስመልክቶ ሕጋዊ ሥርዓቱን ሳይጠበቅ በደቦ ወይም በአመጽ የሚከናወን ማንኛውም ሒደት በሕጋዊ አግባብ እርምጃ እንደሚወስዱ ያስታወቁት።

ማርሸት መሐመድ ሐምዛ የሕግ መምህርና ተመራማሪ ሲሆኑ በኢሜል አድራሻቸው marishetm@yahoo.com ይገኛል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here