የአማራ ፖለቲካ ዥዋዥዌ

0
1079

ኢሕአዴግ በሚዘውረው ፖለቲካ ውስጥ የአማራን ሕዝብ እወክላለሁ የሚለውን ድርጅት ያህል የተሰቃየ የለም የሚሉት ይነገር ጌታቸው፥ የብሔር ድርጅትነቱን አስታውሶ እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ጥያቄ ሲያነሳ በትምክህተኝነቱ እንዳደላ ተደርጎ ይወቃሳል፤ ከዚህ ተግባር መንኖ አገራዊ አጀንዳን ሲያወሳ ደግሞ የሌሎች ተላላኪ በመባል ይወቀሳል ይላሉ። ይህ ደግሞ የትናንቱን ብቻ ሳይሆን የነገውንም አዴፓ መገዳደሩ የሚቀር አይደለም ሲሉ እንደመፍትሔ በክልሉም ሆነ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብታዊ ዕደገትና መዋቅራዊ ሽግግርን እውን የሚያደርግ ብቁ አመራር ከወዴት አለ ሲሉ ያጠይቃሉ።

ኢሕዴን – ብአዴን – አዴፓ የሚሉ ቃላት ካለመሰረታዊ የፖለቲካ ፍኖት ለውጥ ኅልው የሆኑ ናቸው። ከሕወሓት ቀጥሎ በኢሕአዴግ ቤት አንጋፋ የሚባለው የአማራ ፖለቲካ ተሳትፎ አሁንም ፌርማታው በውሉ አልታወቅም። ኢትዮጵያዊነቱን ሲያጎላ አማራነቱ ይደበዝዛል። አማራነቱን ሲያነግት ኢትዮጵያዊነቱ ይሟሽሻል። ይህ ዥዋዥዌ የትናንት ብቻ ቢሆን እንዴት መታደል ነበር፤ ግን አይደለም። የአባይ ማዶ ፖለቲካ ዛሬ ከትናንቱ የባሰ ቅርቃር ውስጥ ተወሽቋል። የክልሉን ርዕሰ መሰተዳድር ጨምሮ ሌሎችንም የሚበላ አብዮት ወደ መሆን መንደርደር ይዟል። ጥያቄው የሚቀዳውም ከዚህ እውነት ነው። ባሕር ዳርን የተንተራሰው የብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ወደቡ የት ነው?

ኢሕዴን አዴፓ – አዴፓ ኢሕዴን
ኢሕአዴግ በሚዘውረው ፖለቲካ ውስጥ የብአዴንን ያህል የተሰቃየ ድርጀት ያለ አይመስልም። የብሔር ድርጅትነቱን አስታውሶ እወክለዋለሁ የሚለውን ሕዝብ ጥያቄ ሲያነሳ ትምክህተኝነቱ እንዳደላ ተደርጎ ይወቃሳል። ከዚህ ተግባር መንኖ አገራዊ አጀንዳን ሲያወሳ የሌሎች ተላላኪ ይባላል። ይህ አጣብቂኝ ግብታዊ ሳይሆን ታሪካዊ ተቃርኖ የወለደውም ጭምር ነው። ኢሕአዴግ ውስጥ ካሉ አራት ፓርቲዎች ኹለቱ ገና ከመነሻቸው የአማራ ፖለቲካን ኮንነው የተነሱ ናቸው። ሕወሓት በድርጅቷ ምሥረታ ማንፌስቶ ላይ ይፋ እንዳደረገቸው የትግል ግቧ የአማራን ጭቆኝነት ማስወገድ ነው። የኦሕዴድ የፖለቲካ ሐዲድም መደራሻው ከዚህ የሚርቅ አይደለም። ኢሕአዴን/ብአዴን ከላይ በተጠቀሱት ችግሮች ብቻ የተተበተበ ፓርቲ አልነበርም። እራሱ የፈጠራቸው ተግዳሮቶችም በጊዜ ሒደት መላወሻ ሲያሳጡት ተመልክተናል።

ተለምዷዊ ከሆነው የኢሕዴን ብአዴን ዲስኩር አንፃር ነገሩን ለመመልከት እንሞክር። ኢሕአዴግ መንበረ ሥልጣኑን ተቆናጦ ብሔር ተኮረ ፌደራሊዝሙን ለመተግብር ሲንቀሳቀስ ከአማራ ፖለቲካ አንጻር ኹለት ፈተናዎች ገጥመውታል። የመጀመሪያው የአማራን ፖለቲካ የሚወክል ድርጅት ማግኘት ሲሆን ኹለተኛው አማራን እንደ ብሔራዊ ማንነት መፈጠር ነበር። መለስ ዜናዊ መራሹ ኀይል ለኹለቱም ችግሮች መፍትሔ ፍለጋን ሩቅ አልዳከረም። የኢሕአዴግ አባል የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ ወደ ብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ እንዲቀየር አደረገ። ለአማራ ሕዝብ እታገላለሁ የሚለው ድርጅት ኅልው ከሆነ በኋላም አማራዊ ማንነት ለመፍጠር ጥረት ተደረገ። በዚህ በኩል ብዙ ሥማቸው ሲጠቀስ ባይሰማም የቀድሞው አፈ ጉባኤ ዳዊት ዮሐንስ ቀዳሚውን ሚና ተጫውተዋል። ዳዊት አማራ ማነው? በብሔሩስ መደራጀቱ ምን ይፈይድለታል በሚል አጠር ያለ ጽሁፍን በማዘጋጀት የቀደማቸው አልነበርም።

የኢሕአዴጉ ሊቀመንበት መለስ ዜናዊ ስለአማራ ብሔረተኝነት ለካድሬዎቻቸው የሚሆን አጭር ጽሁፍ ሲያዘጋጁም ከሞላ ጎደል መነሻ ያደረጉት የዳዊትን ሐሳቦች ነበር። የኹለቱ ግለሰቦች እንዲህ ያለ አብርክቶ ግን በበርካታ ተንታኞች ምልከታ ፖለቲካዊ ስሌትን ያዘለ እንጅ የሕዝብ ተቆርቋሪነትን ያነገበ አልነበረም። በዚህ ምክንያትም ኢሕአዴጋዊ የሆነውን የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ እንደ አማራ ብሔርተኝነት መነሻ ማየት አልተለመድም። ይህ ደግሞ ነገሩን ከገዥው ግንባር ውጭ እንድንመለከተው ያስገድደናል። የአማራ ብሔርተኝነት አራማጆች የመንፈስ አባታችን ወደ ሚሏቸው አስራት ወለደየስ (ፕሮፌሰር) ፊታችንን እንድናዞርም ያደርገናል። አማራ ተወካይ የሌለው ሕዝብ ሆኗል የሚለው የድሬ ዳዋው አስራት ቁጭት በቁዘማ የሚቆም አልነበረም። በመሆኑም የመላው አማራ አንድነት ድርጅትን መሰረቱ። ታላቁ የሕክምና ባለሙያ በየአደባባዩ ስለአማራ ሕዝብ መብት ሲታገሉ አንዳርጋቸው ፅጌ የአማራ ማንነት ፈጠራውን ጽንሰ ሐሳባዊ መሰረት የሚያሲይዝ ሥራን ለአንባብያን አብቅተዋል።

የዛሬው የዜግነት ፖለቲካ አቀንቃኝ አንዳርጋቸው ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም፤ ያለው የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግሬ፣የወላይታ ….ወዘተ በሚል ሙግት ሰፋ ያለ ማብራሪያ አቅረበዋል። አማራም በማንነቱ ከመደራጀት ውጭ አማራጭ የለውም ሲሉ አትተዋል። እንዲህ ያለው የአንዳርጋቸው መከራከሪያ የዋለልኝ መኮንን ሌላ ገፅታ ተደርጎ የሚቆጠር ነው። ዋለልኝ “የብሔር ጥያቄ በኢትዮጵያ” በተሰኘ ጽሁፉ ኢትዮጵያዊ የሚባል ማንነት የለም እውነታው በኢትዮጵያዊነት ሥም የሰሜኑን ባሕል መጫን ነው የሚል አቋም ነበረው። የኢትዮጵያዊው ‘ፕሮቾስኮቫ’ም ሆነ ሌሎች የእሱ ዘመን ወጣቶች የአማራን ባሕል ከአገራዊ ማንነት የመነጠል እንቅስቃሴ በዚህ ሁኔታ ዳዴ ማለት ቢጀምርም ውጤት ግን ዘመናትን የወሰደ ነበር። ለዚህ ኹለት ምክንያቶችን መጠቀስ ያሻል። የመጀመሪያው የቅደመ ኢሕአዴግ አስተዳደራዊ ስርዓት አሃዳዊ ከመሆኑ ይቀዳል። እንዲህ ያለው እውነት ኢትዮጵያዊ ማንነትን ለሚያቀነቅነው የአማራ ሕዝብ ብሔርተኝነት ፈጠራ የሚረዳ አልነበረም። ኹለተኛው ጉዳይ የ1960ዎቹ ትውልድ ፖለቲካ አማራን በጨቋኝነት የፈረጀ በመሆኑ የአማራው ልኂቃን ትርክት ከዚህ በተቃራኒ መቆም ነበረበት። የአማራ ብሔርተኝነት ከላይ በተጠቀሱ መነሻዎች ለዘመናት ያንቀላፋ ቢሆንም በጊዜ ሒደት ግን ማንሰራራቱ አልቀረም።

ለዚህ ደግሞ የድኅረ 1983 የመንግሥትና ሕዝብ ግንኑኝነት ዝመና የጎላ ሚና ተጫውቷል። ሕወሓት መራሹ ኀይል ሥልጣን ሲረከብ የአስተዳደር ስርዓቱን ብሔር ተኮር ፌደራሊዝም ላይ እንዲመሰረት አድርጓል። የኢፌድሪ ሕገ መንግሥትም ብሔር ብሔረሰቦችን ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት እንዲሆኑ ፈቅዷል። ይህ የመንግሥትና ሕዝብ ግንኙነት አዲስ ማዕቀፍ የቀደመውን የመንግሥትና ሕዝብ ትስስር ያሻሻለ ቢመስልም ለአማራ ፖለቲካ ልኂቃን ግን የሚዋጥ አልነበርም። ነገሩን በውሉ ከተመለከትነውም የድኅረ 1983 አዲሱ የመንግሥት ስሪት የአማራን ፖለቲካ ተሸናፊ ያደረገ ነበር። እንዲህ ያለውን እውነት ሩቅ ሳንሔድ በራሱ በመንግሥትና ሕዝብ ግንኙነት ማዕቀፍ ውስጥ መመልከቱ መልካም ይመስላል።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ታሪክ ውስጥ የመንግሥትና የሕዝብን ግኑኝነት የሚወስኑት ጉዳዮች ኹለት ናቸው። አንደኛው ፖለቲካው ውክልና ሲሆን ኹለተኛው ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነት ነው። ከሕወሓት እስከ ኦነግ ነፍጥ አንገበው ጫካ የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች በንጉሡም ሆነ በደርግ ጊዜ ያለው ስርዓት እንታገልለታለን በሚሉት ሕዝብ ላይ የተጫነ መሆኑን በስፋት ለፍፈዋል። ሕዝባችን እውነተኛ ውክልና ባለገኘበት ሁኔታ የተፈጠሩ ስርዓቶችም ጨቋኝ የሚባሉ እንደሆኑ ሰብከዋል። ከዚህ አንጻር የእነሱ ትግል ከጭቆና የመላቀቅ መሆኑን በሰነዶቻቸው በስፋት አብራርተዋል። በዚህ አጣብቂኝ ውስጥ የወደቀችው ኢትዮጵያ በደርግ ሽኝት ዋዜማ 17 ከጭቆና መላቀቀን ዓላማ ያደረጉ ድርጅቶች የነበሩባት ናት። ይህ ሒደት ፍሬ አፍረቶም አራት ኪሎን ከአዲስ የአሰተዳደር ዘዬ ጋር አስተዋወቀ። እንዲህ ያለው የመንግሥት አስተዳደር ለውጥ ግን የኢትዮጵያን ሕዝብና መንግሥት ግኑኝነት ሙሉ በሙሉ የማስተካከል ጉልበት አልነበረውም። ከላይ ካነሳናቸው ኹለት መመዘኛዎች አንጻር ከተመለከትነውም አማራ የውክልናም ሆነ የምጣኔ ሀብታዊ ጠቃሚነቱን በሌሎች ልክ አላስጠበቀም።

ዛሬ ላይ በስፋት የሚቀነቀነው አማራ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ አልተወከለም የሚለው ሙግት መሰረታዊ መነሻም ከዚህ የሚመነጭ ነው። ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሉዓላዊ የሥልጣን ባለቤት በሆኑበት ሕገ መንግሥት ላይ አማራ ይሆነኛል ብሎ የላከው ተወካይ አልነበረውም። የአማራ ብሔርተኝነት በአንድ በኩል የታሪክ ጓዝ የተጫነውን የመንግሥት አስተዳደር ውክልና ጥያቄ የያዘ ሲሆን በሌላ በኩል ምጣኔ ሀብታዊ ተጠቃሚነቱም በድኅረ 1983 ፖለቲካ ውስጥ በውሉ የተመለሰ አይደለም። ኢሕአዴግ መራሹ አስተዳደር ዓለማቀፍ ዕውቅና በተቸረበት ፈጣን ዕድገት ከድኅነት ወለል በታች የሚኖሩ ዜጎቹን ቁጥር በእጥፍ በመቀነስ ወደ 24 በመቶ እንዲያሽቆለቁል አድርጓል። ከዚህ አሃዛዊ መራጃ አንጻር የአማራ ክልል ነበራዊ ሁኔታ ከተመለከትነው የድኅነት መጠኑ ከአማካይ አገራዊ መጠኑ በኹለት በመቶ ከፍ ያለ መሆኑን እንረዳለን። አማራ ክልል 26 በመቶ የሚሆነው ነዋሪው ከድኅነት ወለል በታች የሚገኝ ከመሆኑም በላይ በዓለማችን ላይ በምግብ ጥረት ምክንያት በሚፈጠረው የመቀንጨር ችግርም ቀዳሚነቱን የያዘ ነው።

አዴፓ መራሹ ክልል ከ500 ሺሕ በላይ የሚሆን ሕዝብ በቀላሉ ሊድን በሚችል የዓይን ሕመም የዓይን ብርሃኑን አጥቷል። ኢሕአዴግ ስኬታማ በሆነበት የመንገድ ዘርፍ ትስስርም ወደ ኋላ ቀርቷል። እነዚህ ማሳያዎች አማራ ከፖለቲካ ውክልናም ባለፈ ፍትሐዊ የኢኮኖሚ ተጣቃሚነትን እንዳላረጋገጠ ያሳያል። ይህ ደግሞ ዛሬ ላይ እንደ ሰደድ እየተዛመተ ለሚገኘው የክልሉ ብሔርተኝነት ምቹ መደላድልን ፈጥሯል። አማኑኤል ተስፋዬ “The Birth of Amhara Nationalism፡ Causes, Aspiration and Potential” በተሰኘ ጽሁፋቸው የዘገየ የመሰለውን የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ በአምስት ምክንያቶች በኹለት ዕግሩ ለመቆም እንደሞከረ ያብራራሉ።

እነሱንም ሲያትተቱ ኢሕአዴጋዊ የሆነ ፀረ አማራ ትርክት፣ የአማራ ተወላጆች ላይ የሚደርስ ጥቃት፣ ምጣኔ ሀብታዊ ንቅዘት፣ የብሔርተኝነት ወዝ የለመደ ትውልድ መምጣትና የአዲስ አመራር መተካትን ያነሳሉ። የአማኑኤል መከራከሪያዎች መጨረሻ ላይ ከጠቀሱት ውጭ ተለምዷዊ የሚባሉ ናቸው። ይሁን እንጅ የአማራን ብሔርተኝነት ከክልላዊ መንግሥቱ የአመራር ለውጥ ጋር አያይዞ መመልከት ብዙም የተለመደ አይደለም። ይህን ሐሳብ በውሉ ለመረዳት አንድ መሰረታዊ ጥያቄ ማንሳቱ ተገቢ ይመስላል። የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴን በርግጥ በክልሉ የተደረገው የአመራር ለውጥ ረድቶታል? ከረዳውስ እንዴት?

የአዴፓ ከትናንት የማምለጥ ሩጫ!
ከሰሞኑን የውዝግብ መነሻ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ በአማራ ክልል የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራን አድርገዋል የተባሉት ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ፅጌ ለአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ሥራ አስኪያጅ አስተላለፉ የተባሉት መልዕክት ነው። በዚህ የስልክ ምልልስ ብርጋዴር ጄነራሉ የአዴፓ አመራሮች የክልሉን ሕዝብ ጥቅም ሊያስከብሩ ስላልቻሉ እርምጃ ተወስዶባቸዋል ብለዋል። ይህ ንግግር “የአማራን ጥቅም ማስከበር ምን ማለት ነው?” የሚል ጥያቄን እንድናነሳ ዕድል ይፈጥራል። ከዛ ቀጥለንም “አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) በአማራ ሕዝብ ጥቅም ሲደራደር ነበር እንዴ?” ያስብለናል። ከመጨረሻው ጥያቄ እንነሳ።

የአማራ ፖለቲካ ልኂቃን ባለፉት ዓመታት የክልሉን ሕዝብ ጥቅም ከማስከበር አንጻር አዴፓ የአምባቸውን ያህል ሰው እንደሌለው ደጋግመው ጽፈዋል። እሱን የተጠማው የአማራ ብሔርተኝነት በዚህ ሳይወሰን አምባቸው የኢፌዴሪ ፕሬዘዳንት የመሆን ዕድል እንደተፈጠረለት ሲያውቅ ከፊል ዛቻ ከፊል ተማፅኖን አዝንቧል። ይህ ገፊ ምክንያትም አዲስ አበባ የከተሙትን ሰው ወደ ባሕር ዳር እንዲያመሩና የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር እንዲሆኑ አድርጓል። በዚህም አዴፓን ዓይንህን ለአፈር ያሉት የክልሉ ብሔርተኞች ሳይቀሩ ደስታቸውን ገልጸዋል። እንዲህ ያለው አጋጣሚ አምባቸውን አማራጭ በማጣት ብቻ የመደገፍ ሰው ሳይሆን ለክልሉ ሕዝብ እውነተኛ ተወካይ ይሆናል ከሚል የመነጨ መሆኑ አያከራክርም። ይህ ደግሞ አንድም ከላይ ያነሳነውን የውክልና ጉዳይ ለመፍታት የሚረዳ ሲሆን አንድም ወደ ኋላ የቀረውን የክልሉን ልማት ያሳድገዋል ከሚል ተስፋ የሚቀዳ ነው። በዚህ የሐሳብ ሐዲድ ከአማራ ብሔርተኝነት ጋር የተሰናሰለው የርዕስ መስተዳደሩ ሹመት ሌላም ጉዳይ ያዘለ ነበር። አምባቸው መኮንን በተለያዩ ወቅቶች ባደረጓቸው ንግግሮች የክልሉን ሕዝብ ሥነ ልቦና ታላቅነት የሚያሳዩ ኮርኳሪ ሐሳቦችን በማንሳት ከአማራ ብሔርተኞች ሰፊ አድናቆት ትረፋዋል።

ርዕስ መስተዳደሩ በዚህ ዓይነት መንገድ ጥቂት ቢያዘግሙም የሥልጣን የስበት ኀይል ግን በዚያው እንዲቀጥሉ አልፈቀደላቸውም። በመሆኑም ክልሉን የፖለቲካም ሆነ የምጣኔ ሀብት ተጠቃሚ እንዲሆን ለማድረግ ከክልሎች ጋር ለመሥራት እንቅስቃሴን ጀመሩ። ‘ኦሮማራ’ን የማደስ ሐሳብም ይዘው አንቦ ላይ ተገኙ። ኦሮሞ ሕገ መንገሥታዊ መብቱ እንዲከበርለትም እታገላለሁ ሲሉ ተናገሩ። ይህ ንግግራቸው የአማራ ብሔርተኝነት አዕማድ ከሆነው የውክልና ትግል ጋር በቀጥታ የሚላተም ነው። አምባቸው የአማራ ፖለቲካ ልኂቃን አልተወከልንም የሚሉበትን ሕገ መንግሥት ዕውቅና ከመሰጠጥ አልፎ እንዲተገብር እኔም እታገላለሁ ማለታቸው የማኅበራዊ ሚዲያ ተቃውሞ እንዲቀጣጠልበቸው በር ከፍቷል። ነገሩ ግን በዚህ የሚየቆም አልነበርም ትግራይ ክልል ጋርም ሰላም ለማውረድ የሚከፈለውን መስዕዋትነት እንከፍላለን ሲሉ ተደመጡ። እነዚህ ኹለት ሐሳቦች ከእሳቸው ጎን ነኝ ያለውን አክራሪ የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ እንዲያፈገፍግ አደረጉት።

የቀድሞ አመራሮቹን ወደ ማረሚያ ከላከ በኋላ አንድነቱን አጠናከረ የተባለው አዴፓም በዚህ ማኅበራዊ ግፊት የተነሳ ወደ መሰነጣጠቅ አመራ። ውክልናን የተጠማው የአማራ ብሔርተኝነት እንቅስቃሴ አሳምነው ፅጌን እንደራሴ አደረገ። ብርጋዴር ጄነራሉም በዲፋክቶ የክልሉ መሪ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ንግግሮች እዚህም እዛም ማሰማት ተያያዙ። አፍሪካ አገራት ላይ የሚስተዋለው ሲቪሉን የይስሙላ አስተዳደር ያደረገ ወታደራዊ ሥልጣን (deep state) አማራ ክልልን ወደ መቆጣጠር አመራ። አፍቃሪ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ናቸው የሚባሉት የሰላምና ደኅነነት ቢሮ ኀላፊው ብርጋዴር ጄነራል አሳምነው በጥቂት ጊዜ ውስጥ ከፍ ያለ የብሔርተኞች ድጋፍ ተቸራቸው። ይህ ደግሞ ተወካዬ ናቸው የሚለው ሕዝብ አስተያየት እራሳቸውን እንደ ተወካይ እንዲመለከቱ ሳይገፋፋቸው የቀረ አይመስልም። አሳምነው ፅጌ ከላይ ባነሳሁት የስልክ ምልልሳቸው የእነአምባቸው ቡድን የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ የሚመልስ ባለመሆኑ እርምጃ ተወስዶበታል ማለታቸውም ትክክለኛው ተወካይ እኔ ነኝ ወደ ማለት ያደላል።

ለአፍታ ገታ ያደረግነውን ጥያቄ እዚህ ቦታ ላይ እናንሳ። አሳምነው የአማራን ሕዝብ ጥቅም ማስከበር የሚሉት ሐሳብ ምንድን ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ከጥቅሉ የአማራ ብሔርተኝነት አብራክ የሚወለድ ነው። በአጭር ቋንቋም ተገቢ ውልክልናን መሻት ልንለው እንችላለን። ይህ ውክልና በፌደራል መንግሥት ላይ ያለን ወሰኝ የሚኒስትርነት ቦታ የማግኘት ብቻ ሳይሆን ከዛም የላቀ ነው። የአማራ ብሔርተኝነት አራማጆች አማራው በቁጥር በሚበዛባቸው ከክልሉ ውጭ ባሉ አካባቢዎች ውክልናን ይሻሉ። እንዲህ ያለው ውክልና ወደ ራስ በማጠቃለል አልያም ባሉበት ክልል ተገቢ ተሳትፎ እንዲኖራቸው በማድረግ የሚገለፅ ነው። ተሸመ ቦሬጎ “What is the point in Amhara Nationalism?” በተሰኘ ጽሁፋቸው የአማራ ብሔርተኝነትን ወቅታዊ ጥያቄ በሌሎች ክልሎች ውስጥ ያለን ውክልና ከፊት ማስቀደሙን ይጠቅሳሉ።

ይህ ሐሳብ በአኀዝ ሲተነትኑም 2007 በተደረገው የሕዝብና ቤት ቆጠራ በአዳማ ልዩ ዞን የሚኖረው ሕዝብ 60 በመቶው አማርኛ ተናጋሪ መሆኑን እንዲሁም በቢሸፍቱና አካባቢዋ ያለው አማርኛ ተናጋሪም 72 በመቶ መሆኑን ይጠቅሳሉ። የአማራ ብሔርተኝነት አራማጆች ከግዛት ይገባኛል ባልተናነሰ ከክልሉ ውጭ የሚኖረው አማራ ተገቢ የፖለቲካ ውክልና እንዲኖረው ያነሳሉ። ለዚህ ደግሞ አማራ ክልል ለሌሎች ብሔረሰቦች የሰጠውን በክልል ውስጥ በዞን መደራጀትን መፍትሔ ያደርጋሉ።እንደዚህ ያለው አማራጭ ግን በአሁናዊው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አሰላለፍ ውስጥ ሊተገበር የሚችል አይመስልም። ለአብነት ያህል በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የአማራ ልዩ ዞንና ወረዳን የማደራጀት እንቅስቃሴ ቢደረገ በክልሉ ያሉ የሌላ ብሔር ተወላጆች ጥያቄውን የሚዋሱት ከመሆኑም በላይ ክልሉንም እንደ ደቡብ ክልል እንዲፈረከረክ የማድረግ ዕድል ይኖረዋል። ይህ ደግሞ ኹለቱንም ሕዝቦች ተጠቃሚ ከማድረግ ይልቅ ወደማያባራ ግጭት ያስገባዋል።

ይህ ደግሞ የትናንቱን ብቻ ሳይሆን የነገውንም አዴፓ መገዳደሩ የሚቀር አይደልም። የአማራ ብሔርተኝነት ሌላ ውክልና ፍለጋ ማጠንጠኛ ሐሳብ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የተሳሰረ ነው። የአማራ ፖለቲካ ልኂቃን ሕገ መንግሥቱ በፍጥነት ካልተስተካለ እኛ አናውቀውም ወደ ሚል ፅንፍ እየተሸጋገሩ ይመስላል፤ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ አሁን ባለው የመገፋፋት ፖለቲካዊ ውስጥ በቅርብ ዓመታት ሊስተካከል ይችላል ብሎ ማሰብ ያዳግታል። የሕዝብና ቤቶች ቆጠራን ለመፈፀም ዐቅም ያጣ አስተዳደር የዜጎችን ዕጣ ፋንታ የሚወስንን ሰነድ በሐሳብ የበላይነት ያፀድቃል ተብሎ አይጠበቃም።

ከሳምንታት በፊት “የእኔ ትክክለኛ ተወካይ አሳምነው ፅጌ ነው” ይል የነበረው የክልሉ ብሔረተኛም ዛሬ ላይ ተተኪ ተወካይን የሚፈልግ ይመስላል። እንዲህ ያለው ውክልና መንግሥታዊ በሆነ መልኩ መከሰት አለበት ብሎ የሚያስበው ኀይልም ቁጥሩ ቀላል አይደለም። በዘመነ ድኅረ እውናዊ ፖለቲካ (post truth politics) ይህንን ሕዝብ አሳምኖ ወደ አዴፓ ድጋፊነት ለመመለስ መሞከርም በጣም ከባድ የሆነ የቤት ሥራ ነው። በርግጥ ፈጣን የሆነ የምጣኔ ሀብታዊ ዕደገትና መዋቅራዊ ሽግግርን እውን ለሚያደርግ አመራር የቤት ሥራው የሰማይ ያህል የራቀ የሚባል አይደለም። ይሁን እንጅ እዚህ ቦታ ላይ አማራ ክልልም ሆነ ኢትዮጵያ ለዚያ ብቁ የሆነ አመራር አላቸው ወይ የሚለው ጥያቄ ከፊት ይደቀናል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here