ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ በፓርላማ

0
478

በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት መሰረት ከተዋቀሩት ሦስቱ የመንግሥት አካላት መካከል ሕግ አውጭው አካል ማለትም ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ የሥልጣን ባለቤት በመሆን የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። ይህንም ተከትሎ የሕግ አስፈፃሚው የበላይ አካል የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የበጀት ዓመቱ መገባደጃ ላይ ወደ ሕዝብ እንደራሴው ብቅ ብለው የበጀት ዓመቱን የመንግሥት የሥራ አፈፃፀም ሪፖርትን ያቀርባሉ። በዘንድሮው ማለትም የ2011 በጀት ዓመትን የመንግሥት የሥራ አፈፃፀምን ሪፖርት ሰኞ፣ ሰኔ 24/2011 ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በርካታ ርዕሰ ጉዳዮችን በመዳሰስ በተለይም ደግሞ ቀድሞ ይታይባቸው የነበረውን እርጋታ እና ፈገግታ አፅልመው ስለ ሕግ መከበር መረር ያሉ ቃላቶችን በመጠቀም ለምክር ቤቱ ሪፖርታቸውን አቅርበዋል፤ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄም ምላሽ ሰጥተዋል።

በአገሪቱ እዚህም እዛም የተበራከተውን የሕግ አለመከበር፤ ግለሰቦች ባስ ሲልም ደግሞ ቡድኖች ከሕግ በላይ እስከመሆን ደርሰው የዜጎች እና የአገር ደኅንነት ጥያቄ ውስጥ የገባበትን ሁኔታ በማንሳት ከባድ ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግሮችን አሰምተዋል። የመጀመሪያውን ጉዳይ ከምክር ቤት አባሉ አሰፋ ጫቅሌ ሕገ መንግሥቱን በተለመከተ በኹለት ጎራ ተከፍሎ ስለሚቀነቀነው “ሕገ መንግሥቱ ከተነካ አገር ትፈርሳለች እና ሕገ መንግሥቱ ጥቅሜን ስላላስከበረልኝ ሊሻሻል ይገባል” የሚሉትን ወገኖች ለጠቅላይ ሚንስትሩ አቅርበዋል። ዐብይ ምላሻቸውን “ከሕገ መንግሥቱ በላይ ለሕገ መንግሥቱ የቆመ የለም” ሲሉ በመጀመር በሕገ መንግሥቱ ላይ ማሻሻል እንደሚቻል የተቀመጠበትን አግባብ መኖሩን ጠቅሰው ኹለቱም ወገኖች ግን “ዋልታ ረገጥ” ሐሳቦችን ማስተጋባት በመንግስት በኩል ተቀባይነት የሌለው እና መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ ሊወስድ እንደሚገደድ አስረግጠዋል።

በሕገ መንግሥቱ ውስጥ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት እንዳላቸው እና ይህም በሕገ መንግሥቱ ላይ በአንቀጽ 47(2) ላይ መጠቀሱ ተገልፆ፤ አሁን የመጣውን አገራዊ ለውጥ ተከትሎ ዐሥር የሚሆኑ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል አደረጃጀት ጥያቄ ማቅረባቸውን ተጠይቀዋል። እዚህ ላይ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርጋታቸው በቅፅበት ተለውጦ ቁጣቸው ገነነ ዓይኖቻቸው እሳት እየተፉ “ክልል የመሆን ጥያቄን ማቅረብ ሕገ መንግሥታዊ መብት ነው። ነገር ግን ሕጋዊ ጥያቄን በግርግር ለማስፈፀም መሞከር አይቻልም” በማለት ይህ የማይሆን ከሆነ ግን “በቀደመው እና በተለመደው መንገድ እንፈታዋለን” ሲሉም በቁጣ አስጠንቅቀዋል።

በቅርቡ ሰኔ 15/2011 በባሕር ዳር እና አዲስ አበባ የተሰነዘረውን “መፈንቅለ መንግሥት” በተመለከትም ከቁጣቸው ጋር የተቀላቀለ የሐዘን ድምፀት ነበረበት። “የመፈንቅለ መንግሥት አድራጊዎች የሚሰጡትን የዳቦ ሥም እኛ አናውቅም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አያይዘውም ኢፌዴሪ የሚለው ሥያሜ እና ሕገ መንግሥት ሙሉ ሆኖ የሚቀጥለው የኹሉም ክልሎች ሰላም እስከተከበረ ድረስ መሆኑን ጠቁመው መፈንቅለ መንግሥት በክልሎች አይደረግም ማለት እንደማይቻል ጠቅሰዋል። “ከዚህ በኋላ ግን መፈንቅለ መንግሥት መሞከር በአንድ አዳር 100 ሺዎች የሚታረዱበትን ግጭት መፍጠር ነው፤ እንተላለቃለን!” በሚል ገንፍሎ የወጣውን ስሜታቸውን መቆጣጠር እስኪሳናቸው ብስጭታቸው በግልፅ ይነበብ ነበር።

ዐብይ በሕግ ማስከበር ዙሪያ ከዚህ በኋላ መንግሥታቸው የሚታገሰው ነገር አንደማይኖረው አስረግጠው የተናገሩ ሲሆን “ትዕግስታችን የአገር አንድነት ነው፤ በአገር አንድነት ለሚመጣ ግን እስክርቢቶ ሳይሆን ክላሽ ይዘን እንዋጋለን” ሲሉም ተደምጠዋል። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተጠናከረ መልኩ የሚታየውን የሕግ የበላይነት አለመከበርን እና ከዚህም ጋር ተያይዞ በሴቶች እና ሕፃናት የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር የሚደርሰውን ችግርም ዋቢ ተደርጎ በተነሳው እና መንግሥታቸው በምን ሁኔታ ሊፈታውና ሕግን ሊያስከብር እንዳሰበ ተጠይቀዋል። “የቤንሻንጉል ክልል ከአናቱ የተበላሸ የፖለቲካ ችግር ስላለበት በቅርቡ ይስተካከላል” ብለው ሲናገሩ እልህ፣ ንዴትና ቁጣ ይነበብባቸው ነበር፤ የፊት ገጽታቸውም በግልጽ በሚታይ ሁኔታ ወዝ ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ያስላለፉትን መልዕክት በተለይም ደግሞ በሕግ ማስከበር ረገድ ያሳዩትን ቁጣ እና የትዕግስት መሟጠጥ ጋር በተያያዘ አዲስ ማለዳ በኢትዮጵያ ፖለቲካው ውስጥ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል አንዳንዶቹን አነጋጋራለች።

“ሕግን ማስከበር አይሆንለትም” ብለው ንግግራቸውን የጀመሩት የቀድሞው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኢዴፓ) በመመሥራትና በመምራት የሚታወቁት ልደቱ አያሌው የሕግ ልዕልና ያልተከበረው በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ባሉ ግለሰቦች በመሆኑ ጠቅላይ ሚንስትሩ የፈለጉትን ያህል ቢጥሩም ለውጥ ለማምጣት መጀመሪያ በመንግሥታቸው ውስጥ ያሉት ሰዎች ማጥራት መጀመር ይገባቸዋል ብለዋል። ወደ ውጭ መመልከት የሚኖርባቸው ይህን ሥራ በሚገባ ካጠናቀቁ በኋላ መሆን ይገባቸዋል ሲሉም ሐሳባቸውን አጋርተዋል።

መንግሥት ተቀናጅቶ የመሥራት ትልቅ ክፍተት እንዳለው የገለፁት ልደቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚሾሟቸው ግለሰቦች ብቃት ላይ ከፍተኛ የሆነ ጥርጣሬ እንዳላቸውም ገልጸዋል።

በመጨረሻም “ክላሽ ይዞ መንቀሳቀስን በመንቀፍ ወደ ሥልጣን የመጣ ሰው ወደ ኋላ ተመልሶ የክላሽ ዘመንን ማንሳት አሳፋሪ ጉዳይ ነው” ሲሉ ትዝብታቸውን ያጋሩት ልደቱ ድሮ ወደነበረው የአስተዳደር ዘመን ግን መመለስ በጭራሽ እንደማይቻልም አስገንዝበዋል።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያስተላለፉት ሕግን የማስከበር ሒደት ተግባራዊ ይሆናል ብለው እንደማያስቡ ለአዲስ ማለዳ የተናገሩት የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ ገመቹ፣ በተለያዩ ክልሎች ውስጥ የተለያዩ መንግሥታት እየተፈጠሩ ባሉበት በአሁኑ ወቅት ሕግን አስከብራለሁ ብሎ መነሳት አዳጋች እንደሆነ ይገልፃሉ።

“ልዩ ኀይሉም ያስራል፤ በክልሎች የሚገኘው የመከላካያ ኀይል ያስራል፤ ዞን መስተዳደርም ያስራል” የሚሉት ሙላቱ ይህ የሚያሳየው በሕግ ያለመመራት ትልቁ ማሳያ እንደሆነ ያስረዳሉ። በዚህ ምንም ዓይነት የሕግ አግባብ በሌለው ሁኔታ በመቶዎች የሚቆጠሩ አባላቶቻቸውን በወታደራዊ ካምፖች፣ በልዩ ኀይል እስር ቤቶች እና በዞን ደረጃ በተለያዩ አካባቢዎች በእስር ላይ እንደሚገኙ አክለው ገልጸዋል። ይህም ፍትሕ እና ሕግ ማከበር ጭራሽ መዳከሙን የሚያሳይ ነው ሲሉ ደምድመዋል።

ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ ፓርቲ (ኢዜማ) የሕዝብ ግንኙነት ሰብሳቢ ናትናኤል መኮንን መንግሥት ሕግ የማስከበር ኀላፊነት እንዳለበት በመጠቆም በተጨማሪ ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊትም የቅድመ ጥንቃቄ ሥራዎችን በመሥራት ሕግ የማስከበር ሒደቱን ቀላል እንደሚሆን ማድረግ አለበት ሲሉ ለአዲስ ማለዳ ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል። አያይዘውም የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ሕግን የማስከበር ተስፋ እንዳሳደረባቸው የገለጹት ናትናኤል፣ ከዚህ በፊት የነበሩት ተቋማት ሕግን ከማስከበር ይልቅ አንድን ፓርቲ ወግነው የፓርቲ አጀንዳ አስፈፃሚዎች የነበሩ ናቸው ሲሉ ወርፈዋቸዋል። በዚህም ኢዜማ የለውጡ ኀይል በቀጣይ በሕግ መከበር ረገድ ትልቅ እመርታ ያስመዘግባል ብሎ ተስፋ እንደሚያደርግ የጠቀሱት ናትናኤል “እስካሁን የነበሩት ስርዓት አልበኝነቶች ከሽግግር ጋር የሚመጡ መንገራገጮች ናቸው” ሲሉ በመግለጽ ኢዜማ እንደ ፓርቲም ከመንግሥት ጎን በመቆም ለሕግ መከበር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

በዕለቱ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ላይና በታዛቢነት በተሳተፉት ላይ ጉራማይሌ ስሜቶች ተንጸባርቀዋል፤ ግማሽ ሐዘን – ግማሽ ቁጭት።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here