የቀውስ አስተዳደር፡ በኀይል ወይስ በሕግ?

0
663

የኢትዮጵያ መንግሥት የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙን ጨምሮ ሦስት ጀኔራሎች፣ የአማራ ርዕሰ መስተዳድርን ጨምሮ ሦስት የሲቪል ባለሥልጣናት ሕይወት ያጠፋውን እርምጃ “የመፈንቅለ መንግሥት” ሙከራ ብሎታል። የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከሩቅም ከቅርብም የሚከታተሉ ብዙ ታዛቢዎች ግን እርምጃው የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ መሆኑ ላይ ጥያቄ ያነሳሉ። ይሁንና ከድርጊቱ “መፈንቅለ መንግሥት” መሆን አለመሆኑ ይልቅ የብዙዎችን ቀልብ የሳበው ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክረሲያዊ ስርዓት ግንባታ በለውጥ ሒደት ላይ ባለችበት ሁኔታ እንዴት እንደዚህ ዓይነት ቀውስ ውስጥ ገባች? ከእንግዲህስ እንዴት እና ወዴት ትጓዛለች? መንግሥት የሚያጋጥሙትን ቀውሶች ለመፍታት ምን ዓይነት መንገዶችን ይጠቀም ይሆን ? የሚሉት ናቸው።
የአዲስ ማለዳው ኤፍሬም ተፈራ በጉዳዩ ዙሪያ ባለሙያዎችን አነጋግሮ ጉዳዩን የሐተታ ዘ ማለዳ ርዕስ አድርጎታል።

ሰኞ፣ ሰኔ 24 ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የዓመቱን የሥራ ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ከማቅረብ በተጨማሪ ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ በምክር ቤቱ አባላት ለቀረበላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ በሰጡበት ወቅት፣ የኢትዮጵያን ኅልውናና አንድነት በሚመለከት፣ መንግሥት ከሰላማዊው መንገድ ባሻገር አስፈላጊ ከሆነ የጦር መሣሪያን በማንሳት የሚፈጸሙ አፍራሽ ድርጊቶችን ለመከላከል አስፈላጊውን ሁሉ ከማድረግ ወደ ኋላ እንደማይሉ አሳስበዋል።

በንግግራቸውም “ለኢትዮጵያ አንድነት ግንባራችንን እንሰጣለን፤ በኢትዮጵያ ኅልውና የሚመጣ ካለ በእስክሪቢቶ ሳይሆን ክላሽ ተሸክመን ለመዋጋት ዝግጁ መሆናችንን የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲገነዘብ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ታዲያ የመንግሥትን አካሔድ አገሪቷ ያጋጠማትን ችግር በማባባስ ወደ ቀውስ እንዳያመራ የሰጉ በርካቶች ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር “ገና ኹለት ወራት እንኳን ሳይሆነን የጀመርነውን ለውጥ ለማጨናገፍ በአደባባይ የምታቁት ሙከራ ተደረገ” ያሉ ሲሆን፤ ከዚህ ኹለት ወር በኋላ “በሶማሌ ክልል የኢትዮጵያን አንድነት የሚፈታተን ገንዘብ እና ትጥቅ ያለው የተደራጀ በሺዎች የሚቆጠር አባላት ያለው ኀይል ችግር ፈጠረ። . . . እሱን ተሻግረን ሳንጨርስ የተደራጀ ወታደር ቤተ መንግሥት መጣ። በምታውቁት ሁኔታ እነሱን ከመለስን በኋላ በምዕራብ ኦሮሚያ በሦስት ወር መንግሥት እሆናለሁ ብሎ ምዕራብ ኦሮሚያን የሚያተራምስ ኀይል ተፈጠረ” ብለዋል።

እነዚህ ተደጋጋሚ ሙከራዎችና ፈተናዎች መንግሥትን ወደ ኀይል እርምጃዎች መውሰድ እንዳያመራው ከሚሰጉት ምሁራኖች አንዱ የሆኑት፣ የሕግ መምህሩና በወንጀል ሕግ ላይ ተመራማሪ የሆኑት ሥሜነህ ኪሮስ ለአዲስ ማለዳ ሲገልጹ፣ አገሪቱ በሽግግር ሒደት ላይ ነች፤ ከላይ ያለው አስተዳደር እንጂ፣ አጠቃላይ ቢሮክራሲው ባለመለወጡ ችግሮች መኖራቸው አይቀሬ ነው ይላሉ።

የባለሥልጣኖቹን ግድያ አስመልክቶ የተፈጸመው የግድያ ወንጀል ተራ አለመሆኑን የሚያወሱት ሥሜነህ፣ በወረዱት የቀድሞ አመራሮችና አሁን በመጡት አመራሮች መካከል የሚካሔድ ፍልሚያ መኖሩን ጠቅሰው፣ የቀድሞዎቹ አመራሮች የአገሪቱን መውጫና መግቢያ ጠንቅቀው ስለሚያውቁት ያሻቸውን እያደረጉ ነው ባይ ናቸው፤ እነዚህ ነገሮች መንግሥትን ትዕግስት ሊያሳጡት እንደሚችሉ በመጠቆም።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት ደረጀ ዘለቀ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ መንግሥት አምባገነን ሆኗል ሲሉ ይሞግታሉ። ወደ ቀደመው አምባገነናዊ ሥርዓት እየተመለስን ነው የሚሉት ደረጀ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ ለዚህ ጥሩ ማሳያ መሆኑንና በኢትዮጵያም ታሪክ ራሱን መድገሙን ያስታውሳሉ።

በኢትዮጵያ ፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ረዘም ያለ ጊዜ በመሳተፍ የሚታወቁት ልደቱ አያሌው፣ አዲሱ አስተዳደር የመጣው የክላሽ አገዛዝን ለማስወገድ እንጂ፣ ለማስቀጠል አይደለም ሲሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ይቃወማሉ። ችግር የሚፈጥሩት በራሱ በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች መሆናቸውን በመጥቀስ፣ ችግሮቹን ከመዋቅሩ ጀምሮ ማስተካከልና መፍታት ሲገባው፣ እንዲህ ዓይነት አስጸያፊ ተግባር እስኪፈጸም መጠበቁ ስህተት ነው ብለዋል።

እንደልደቱ ገለጻ፣ ከሰኔ 16ቱ ጥቃት በኋላ ተደጋጋሚ ሙከራዎች መደረጋቸውንና መታሰባቸውን መንግሥት ያውቃል። ነገር ግን እሳት ማጥፋት ላይ ብቻ በማተኮሩ፣ እንዲህ ዓይነት ችግሮች ሲመጡ መደናገጥ ውስጥ ገብቷል። ባለፉት አንድ ዓመታት በነበረው የተዝረከረከ አሰራር የመጣ ችግር መሆኑንም አውስተዋል።

መንግሥት መደናበሩን የሚያሳብቅበት ብዙ ስህተት ሰርቷል የሚሉት ልደቱ፣ ከነዚህም መካከል ነገሮች ባልተረጋገጡበት ሁኔታ መግለጫ መስጠት፣ ያለፍረድ ቤት ትዕዛዝ ማሰርና እርስ በእርሱ የሚጋጭ ተደጋጋሚ መግለጫዎቹ ናቸው ሲሉ ይገልጻሉ። ከእነዚህ ሒደቶች መረዳት የሚቻለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተለመደው አሰራራቸው በመውጣት አምባገነናዊ ሒደትን የሚከተሉ መምሰላቸው ነው ሲሉም ያክላሉ።

የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት ናትናኤል መኮንን በዚህ ሃሳብ አይስማሙም፣ መንግስት ወደሃይል እርምጃ ሊገባ ይችላል በሚለው አሳብ አይስማሙም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሃገር አንድነት ላይ አደጋ ሊፈጥሩ በሚችሉት ላይ የምወስደው የመጨረሻ እርምጃዬ ነው አሉ እንጂ መጀመሪያዬ ይሆናል አላሉም ሲሉ፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር ተገቢ መሆኑን ያብራራሉ።

የቀድሞው ኤታ ማዦር ሹም ቴፍተናንት ጀኔራል ፃድቃን ወልደ ተንሳዒ በበኩላቸው ጀኔራል ሰዓረ መኮንን፣ ሜጀር ጀኔራል ገዛኢ አበራና አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ሌሎቹምና ኹለት ባለሥልጣናት በሥራ ቦታቸው ላይ እያሉ መገደል በጣም ከፍተኛ የሆነ የፀጥታ ችግር እንዳለ አመላካች መሆኑን ባሳለፍነው ሳምንት ከቢቢሲ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። ጀነራሉ አክለውም፣ ‘ኢንተለጀንስ’ (የስለላ መረጃ) አሰባሰብ ላይ ከፍተኛ ችግር እንዳለ ነው የሚያሳየው ብለዋል፤ ከዚህ ቀደም እንኳን ይሄን ያህል ሴራ እየተሸረበ አይደለም፣ በግለሰብ ደረጃ የሚደረጉ ትንንሽ ነገሮች ፈጥኖ ይታወቁ እንደነበር ገልጸው፣ ቀላል ያልሆነ የፀጥታ ችግር መኖሩን፣ በፀጥታ መዋቅሩ ውስጥ መታየት ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ ነው የሚያሳየው ብለዋል።

ጄኔራል ሰዓረን የገደለው የራሱ የጥበቃ ኀይል አባል መሆኑን ያስታወሱት ፃድቃን፣ መከላከያ ውስጥ የመከላከያን ተቋም የሚጠብቅ ፀረ መረጃ የሚሉት ኀይል አለ። ለእንደነዚህ ዓይነት ትልልቅ ባለሥልጣናት የሚመደብ ሰው በዚህ አካል ከተጣራ በኋላ ነው በሥራ ላይ የሚሰማራው። ይህ አለመሆኑ ቀላል ያልሆነ የፀጥታ ችግር እንዳለ እንደሚያሳይና የፀጥታ ችግሩ ከፖለቲካዊ ሁኔታም ጋር የተያያዘ መሆኑን ይናገራሉ። ጄነራሉ አሁን ያለውን ሁኔታ በትኩረትና ከስሜታዊነት በራቀ መልኩ መታየት ያለባቸው ናቸው ሲሉ ይመክራሉ።

ኢትዮ ቴሌኮም በአገሪቱ ተዘግቶ የሰነበተው የፊክስድ ብሮድ ባንድ እና የሞባይል ኢንተርኔት የተቋረጠው ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነ የድርጅቱ ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ጨረር አክሊሉ ለአዲስ ማለዳ አስታውቀዋል። ለተፈጠረው መጉላላት እና ለደረሰው የኢኮኖሚ ኪሳራ ይቅርታ ጠይቀዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም ባልተለመደ ሁኔታ እንዲህ አይነት መግለጫ መስጠቱ ብዙዎችን ያነጋገረ ቢሆንም፣ ዳይሬክተሯ ግን ለአገር ደህንነት ሲባል የተወሰደ አማራጭ የሌለው እርምጃ ነው ብለውታል። በርካታ ተቋማትን ለኪሳራ የዳረግው የኢንተርኔት መቋረጥ ሌላው የቀውስ አስተዳደሩ ማሳያ ነው የሚሉም በርካቶች ናቸው።

የተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር መዋል
ዓለም ዓቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት፣ ሰኞ፣ ሰኔ 24 ባወጣው መግለጫው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተለይም በአማራ ክልልና በአዲስ አበባ ወጣቶችን እያፈኑ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ በእስር ቤት ማጎር በአስችካይ እንዲቆም ለኢትዮጵያ መንግሥት ጥሪ አስተላልፏል።

ተቋሙ፣ ላለፉት 27 ዓመታት በኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞችና የመብት ተማጋቾች በነጻነት ሐሳባቸውን ስለገለጹ ብቻ ያለምንም የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሲታስሩ፤ ሲገረፉ፤ ሲገደሉ እና ሲሰቃዩ ያሳለፉት ዘመን ገና ሳይረሳ፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ውስጥ ለውጥ መጥቷል በሚባልበት ጊዜ፣ እና አገሪቱን የሚመሩት ጠቅላይ ሚንስትር “በኢትዮጵያ ውስጥ ማንም ይሁን ማን፣ አስቀድሞ ማጣራት ሳይደረግና የፍርድ ቤት ትእዛዝ ሳይወጣ፣ አንድም ሰው እንዲታስር አንፈቅድም” በማለታችው ምክንያት ከዓለም ዐቀፍ ተቋማት፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናልና የመሳስሉት ድርጅቶች ሳይቀር ዕውቅና በሰጧቸው አንድ ወር በማይሞላ ጊዜ ውስጥ፣ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ሰዎች በጅምላ እየተያዙ መታሰራቸው ስህተት ነው ሲል ገልጿል።

እንደተቋሙ መግለጫ፣ በተለይ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ ከኹለት መቶ ሰባ በላይ የሚሆኑ የአዲስ አበባና የሌሎች ነዋሪዎች ታፍነው ወደ እስር ቤት ተወርው እየተገረፉ ነው ሲል ያትታል። በሽብርተኛነት እየተከሰሱ ነው ሲል ጨምሯል። ይህ የሕወሓት መራሹን አፋኝና ጨቋኝ መንግሥት ሥራ የሚያስታውሰንና የሚመስል አድራጎት በአገሪቷ ውስጥ መጥቷል የሚባለውን ለውጥ ተስፋ ሰጪ መሆኑ ቀርቶ፣ ኢትዮጵያዊያኖች መጪውን ጊዜ በጭንቀትና በፍርሃት እንዲመለከቱት ከማድረጉም ባሻገር፣ ያለፈው የመከራና የአፈና ዘመን መልሶ መምጣቱን ከወዲሁ አመላካች እንደሆነ ያሳያል።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለው የብሔር ልዩነቶች ከጊዜ ወደ ጊዜ መጠኑ ሥር እየሰደደ መሆኑ ይታወቃል የሚለው ተቋሙ፣ መንግሥት ለዚህ ትኩረት መስጠት እንዳለበት አሳስቧል። በተለይ በአማራውና ኦሮሞ ባልሆነው ሕዝብ ላይ በቡራዩ፤ በሰሜን ሸዋ፤ በቤኒ ሻንጉል ጉሙዝ፤ በልዩ ልዩ የኦሮሞ ክልል ስፍራዎች ላይ እጅግ የሚዘገንን ብሔር ተኮር እልቂትና አፈና እየተካሔደ ነውም ሲል ከሷል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በበኩላቸው ታስረዋል ስለተባሉት ሰዎች ሲገልጹ፥ በተለያዩ የወንጀል ተግባራት ላይ ተሳትፈዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦችና ቡድኖች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አመልክተው፤ በዚህም መሰረት ከሽብር ቡድን ጋር በተያያዘ 48፣ በተለያዩ ስፍራዎች ከተፈጸሙ ብሔርን መሰረት ባደረጉ ጥቃቶች የተጠረጠሩ 799 አመራሮችና የጸጥታ ኀይል አባላት እንዲሁም፣ በምጣኔ ሀብታዊ ወንጀሎች የተጠረጠሩ 34 ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪ በሕገ ወጥ የገንዘብ ዝውውር ውስጥ ተሳታፊ ሆነዋል የተባሉ 64 ተጠርጣሪዎችና በሕገወጥ የሰዎች ዝውውር ደግሞ 51 ሰዎች በሕግ አስከባሪዎች መያዛቸውን ጠቁመዋል።

ሥሜነህ ዓለም ዐቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ያወጣውን መግለጫ በተወሰነ ደረጃ አይቀበሉትም፣ መንግሥት እስካሁን ለዘብ ብሎ እየሔደ መሆኑን አስታውሰው፣ በየቦታው አስጨናቂ ወሬዎችና ድርጊቶች እየተካሔዱ ባሉበት ወቅት እንኳን፣ መንግሥት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ላውጅ ሳይል፣ በመደበኛው የሕግ ሥርዓት መመራቱ የሰብኣዊ መብት መጣሱን አመላካች አይደለም ይላሉ። የመንግሥት አካሔድ እንከን ያለበት ቢሆንም፣ ለሰብኣዊ መብት ተከሳሽነት የሚያበቃው ግን አይደለም በማለት አክለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገራችን ባልተለመደ ሁኔታ የተያዙትን ሰዎች ብዛትና የተያዙበትን ምክንያት ለምክር ቤቱ ግልጽ ማድረጋቸውም መዘንጋት አይኖርበትም ሲሉም ይሞግታሉ።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ምክትል ሊቀመንበር ሙላቱ ገመቹ በዚህ አይስማሙም። የፌደራል መንግሥቱ እራሱ ያሰራቸውን ሊያውቅ ቢችልም፣ በተለያዩ አካባቢዎች በመከላከያ፣ በልዩ ኀይልና በሹመኞች እየታፈሱ በወታደር ካምፕ ስለሚታሰሩት ግን መረጃ የለውም፤ ካለውም ግልጽ አላደገውም ሲሉ ይከሳሉ። እንደ ምሳሌም የፓርቲው አባላቶች በተለያዩ የኦሮሚያ ዞኖች መታሰራቸውን በመጥቀስ።

ደረጀ፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ አምባገነንነት እየታየ ነው ይላሉ። እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችም አምባገነናዊ የጅምላ እስርና ሕጉን መሰረት ያላደረጉ ክሶች ናቸው ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሁኔታዎች አምባገነን አድርገዋቸው ሊሆን ይችላል የሚሉት ደረጀ፣ የባለሥልጣናቱ ግድያ በተፈጸመ ምሽት ጥቁር ልብስ ለብሰው መግለጫ መስጠት ሲገባቸው፣ ወታደራዊ የደንብ ልብስ ለብሰው መታየታቸው አስተዳደሩ ቀውስ ውስጥ የመግባቱ ማሳያ ነው ሲሉም ያክላሉ።

የጅምላ እስሩ የአገሪቱን ገጽታ እንዳያበላሸው ሥጋታቸውን የገለጹት ልደቱ፥ መጀመሪያውኑም ግድያው የተፈጠረው በመንግሥት እንዝህላልነት ነው በመሆኑ መጠየቅ ያለበት ራሱ መንግሥት እንጂ ሰላማዊው ሰው አይደለም ይላሉ። አሁንም መንግሥት ውስጥ አለመረጋጋት መኖሩን አውስተው፣ ከእከሌ ጋር ግንኙነት አለህ፣ ከእከሌ ጋር ተደዋውለሀል፣ እዚህ ቦታ ሔደህ ነበር እያሉ በጅምላ ማሰርና ማንገላታት አንዱ ማሳያ ነውም ይላሉ።

“ተጠርጥራችኋል” ተብለው ከሌሎች የአብን አመራሮች ጋር ሰኔ 21/ 2011 በአማራ ክልል በምዕራብ ጎጃም ዞን ሰከላ ወረዳ በክልሉ የፀጥታ ኀይሎች በቁጥጥር ሥር ውለው፣ አንድ ቀን ታስረው ካደሩ በኋላ በማግሥቱ የተለቀቁት የአብን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልና የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ ክርስቲያን ታደለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀሩ የፈረሙት የቃል ኪዳን ሰነዱ እንደተጣሰ ገልጸዋል።

ክርስቲያን በሪፖርተር ጋዜጣ ረቡዕ፣ ሰኔ 26 ዕትም ላይ እንደገለጹት፣ አብን በምርጫ ቦርድ የተመዘገበና ዕውቅና የተሰጠው ሕጋዊ ፓርቲ ነው። በመሆኑም ፓርቲውም ሆነ የፓርቲው አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች ሕገወጥ ተግባር ከፈጠሩ እንዴት መጠየቅ እንዳለባቸው በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ ተቀምጧል። በተለይ አመራሮች ሕገወጥ ተግባራት ላይ ተሰማርተው ወይም ፈጽመው ከተገኙ ድርጊቱ የተፈጸመበት ክልል፣ ዞን ወይም ወረዳ በሚመለከተው አካል በኩል ለምርጫ ቦርድ ማሳወቅ አለበት ብለዋል። ችግሩ የከፋና ሕግን የተላለፈ ከሆነ፣ ድርጅቱን (ፓርቲውን) በአግባቡ ሕግን ተከትሎ ተጠያቂ ማድረግ ሲገባ፣ በተለይ ኦዴፓ በሚያስተዳድራቸው አካባቢዎች ያለ በቂ ምክንያት የአብን አመራሮች፣ አባላትና ደጋፊዎች እየታፈሱና እየታሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

ክርስቲያን አብን ሕጋዊ ፓርቲ መሆኑንና መከሰስም ሆነ መክሰስ እንደሚችል እየታወቀ፣ አመራሮቹን እያፈሱ ማሰር ተገቢ አለመሆኑን አስረድተዋል። የዘር ጥቃት በሚመስል ሁኔታ የነቁና የሚንቀሳቀሱ የፓርቲውን አመራሮችና ደጋፊዎች ማሰር ተገቢ አለመሆኑንም በድጋሚ አክለዋል። ድርጊቱ የፖለቲካ እስር መሆኑን፣ በተለይ በተለያዩ ቦታዎች የታሰሩ ከ300 በላይ አባላትና ደጋፊዎች ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውንና ቤተሰቦቻቸው እንደማይጠይቋቸው ተናግረው፣ ይኼ የመብት ጥሰትም ጭምር መሆኑን ገልጸዋል።

ሁሉንም ሁኔታ ለኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ማሳወቃቸውንና መንግሥት ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ችግሮቹን ያስተካክላል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸው፣ መንግሥት ይኼንን ድርጊት የማያስተካክል ከሆነ በሰላማዊና በሕጋዊ መንገዶች ፓርቲያቸው የሚወስናቸው እርምጃዎች እንደሚኖሩም አስታውቀዋል። ይህ የሚያሳየው አምባገነናዊ መንግሥት እየተፈጠረ መሆኑን ነው በማለት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ሰኞ፣ ሰኔ 24/2011 ላይ በድኅረ ገጹ ላይ “ዛሬ ላይ ነገን ስፈልጋት” በሚል ርዕስ ባስነበበው ጽሑፍ ላይ እንዳብራራው፣ ኢትዮጵያ በዘመኗ ውስጥ ያሳለፈችው ፈተና እጅግ ብዙ ነው። አዋቂዎቿን፣ ችግሮችን ያሻገሯትን በገዛ ልጆቿ አጥታለች። በ1953 በታኅሣሥ ግርግር ንጉሡን ለማውረድ በማሰብ እርሳቸው ወደ ውጭ አገር በሔዱበት ወቅት በተፈጸመው ድርጊት በርካታ ዜጎች አልቀዋል።

በ1966 የተፈጸመው መፈንቅለ መንግስት በፖለቲካው፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚው ዘርፍ ያመጣው መዘዝ በቀላሉ የሚገመት አይደለም፤ በርካታ ጥናቶችና ታሪካዊ ትንተናዎች ይፈልጋል። በቁንጽል ካየነው ግን የንጉሡ ሚኒስትሮች፣ መኳንንት፣ ባለሀብት መገደል በቀላሉ የሚታይ ችግር አልነበረም። አገር ዋጋ ከፍላ በውስጥና በውጪ ያስተማረቻቸው ልጆቿ ሲገደሉ የምታነባው ለእነርሱ ብቻ አይደለም፤ አሻግራ ነገን እያየች እንጂ። የእነርሱ ዕውቀት አገራቸው በወቅቱ የደረሰችበት ደረጃ ላይ እንድትሆን ዘመኑን በተረዱትና በተገነዘቡት መጠን ሚናቸውን ተጫውተዋል። ከእነርሱ እልቂት በኋላ ወታደሩ ሥልጣን ሲጨብጥ መሣሪያ የያዘ ኀይልና በዕውቀት ላይ መሣሪያ የጨበጠ ፋኖ እርስ በርስ መዋጋት መተላለቅም ሆነ። ኢትዮጵያ የእውቀት ማኅደር የሆኑ ልጆቿን ከዚህም ከዚያም አጣች።

በደርግ ዘመን ከጭንቅና ስጋት የተላቀቀ ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ አልነበረም። አባቶች ለወንድ ልጆቻቸው ‘እያማጡ’ እናቶች መቀነታቸውን አስረው ‘እዬዬ” እያሉ ዘመናቸውን በእንባ አሳለፉ። በ1981 በመንፍቅለ መንግሥት ሙከራም የተሳተፉ ጄኔራሎችና ወታደሮች ሕይወታቸው ተቀጠፈ። አሁንም ኢትዮጵያ ተስፋ የምታደርግባቸው ልጆቿን አጣች።

ከ1983 በኋላም በተለያዩ ጊዜያት የሽብር ጥቃቶች ተፈጽመው ውድ ዜጎች ተሰውተዋል። በተለያየ ጊዜ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ፍትሐዊነት ለማግኘት ሰዎች በየአካባቢው ጥያቄ አንስተው እንደወጡ ቀርተዋል። አሊያም አንዱ ሌላውን ትደግፋለህ ተብለው በሕይወታቸው ዋጋ ከፍለዋል፤ የዜጎች ሕይወት ጠፍቷል፤ንብረት ወድሟል። ሁሉም የሚሆነው በዴሞክራሲ፣ በፍትሀዊ ተጠቀሚነት ሥም እንጂ ኢትዮጵያን ወደ ቀጣይ ዘመን ለማሻገር አቅም አጥሯቸዋል ሲል ያብራል።
የ“መፈንቅለ መንግሥቱ” አነጋጋሪነት

ሰሞኑን መንግሥት በብርጋዴር ጄነራል አሳምነው ጽጌ የተሞከረው “መፈንቅለ መንግሥት” ነው ማለቱን ተከትሎ በርካቶች ከመቼ ጀምሮ ነው በክልል ደረጃ መፈንቅለ መንግሥት መካሔድ የተጀመረው ሲሉ ሞግተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትሩም በሰኞው የፓርላማ ውሏቸው የተፈጸመው ጥቃት “በኢፌዴሪ መንግሥት ላይ የተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት ነው” ብለዋል። “በየትኛውም የፌደራል ሥርዓቱ ላይ የሚቃጣ ጥቃት የኢፌዴሪ ጥቃት ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትሩ፤ “አመራር ገድሎ እና አግቶ ሲያበቃ፤ የመንግሥት ተቋማትን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ ለምን የመፈንቅለ መንግሥት ትሉታላችሁ” መባሉ ትክክል አይደለም ሲሉ በአጽንዖት ገልጸዋል።

የሰሞኑ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ አድራጊዎች ከባሕር ዳርና ከአዲስ አበባ ውጪ በቤኒሻንጉል ጉሙዝም ኀይል አሰማርተው እንደነበረና ከኦሮሚያ የተመለመሉ “ገዳዮችን” ያካተት እንደነበረ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ተናግረዋል።

ደረጀ ግን በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ አይስማሙም፤ የተካሔደው ተራ ግድያ እንጂ መፈንቅለ መንግሥት አለመሆኑን ለአዲስ ማለዳ የሚናገሩት የሕግ ባለሙያው፣ ከዛ ይልቅ ግድያውን ያወሳሰበው ከፌደራል መንግሥቱ ይሰጡ የነበሩት እርስ በርሳቸው የሚጋጩና ሕዝቡን ግራ ያጋቡ መግለጫዎች ናቸው ሲሉ ገልጸዋል።
ድርጊቱ ግን መንግሥት ሁሉም ነገር ዴሞክራሲያዊና ነጻነት የተሞላበት እንዲሆን በመፍቀዱ በተፈጠሩ ክፍተቶች ሳቢያ የተከሰተ ነው የሚሉት ሥሜነህ፥ ይህ ሁኔታ ለአንዳንዶች በነጻነት መደራጀትና ማሴር ምቹ ሁኔታ ፈጥሮላቸዋል ብለዋል። ይሁንና ድርጊቱ ተራ ወንጀል አይደለም በማለት መፈንቅለ መንግሥት ነው አይደለም የሚለው ለመወሰን ግን ጥናት ያስፈልጋል ብለዋል።

ጀነራል ፃድቃን በበኩላቸው በክልል ደረጃ ሥልጣን ለመያዝ ታስቦ የተደረገ እንቅስቃሴ ነው በማለት የመከላከያ ሠራዊት ባለሥልጣናት ላይ የተወሰደው እርምጃ በክልላቸው ለሚደረግ ሥራ እንቅፋት እንዳይፈጥሩባቸውና ነገሮችን ለማዛባት አስበው የሠሩት በማለት ሐሳባቸውን ገልጸዋል። ይሁንና የአማራው ክልል ሙከራ ቢሳካላቸው ኖሮ የሚሔዱት ርቀት አነስተኛ በመሆኑ ፃድቃን መፈንቅለ መንግስት ነው ብሎ ለመደምደም ግን ከባድ ነው ሲሉ ቢቢሲ አማርኛ ላቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።

እንደ መፍትሔ
ማንም ሰው ሕግ የማክበር ግዴታ እንዳለበት አጽንዖት የሰጡት ሥሜነህ፥ ሕግ አስከባሪውም በበለጠ ሕግ የማክበር ኀላፊነትና ግዴታ እንዳለበት ጠቁመዋል። ሕግ ለማክበርም ሆነ ለማስከበር የሚያስፈልገው፣ በሕግ የበላይነት በማመንና ሰዎች ሁሉ በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውን በመቀበል ነው ሲሉም አክለዋል።
ሐኪም፣ መምህር፣ ነጋዴ፣ መሐንዲስ፣ አርሶ አደር፣ ጋዜጠኛ ወይም በሌሎች ሙያዎች ተሰማርቶ መሥራት የተለየ አስተያየት ወይም አድልዖ ሳይኖር፣ በሕግ ፊት እኩል ናቸው ተብሎ ይታሰባል የሚሉት ደረጀ በበኩላቸው፥ ሲያጠፉም የሚጠየቁት በሕግ አግባብ ብቻ ነው። “[ተጠርጣሪዎች] ፍርድ ቤት ሲቀርቡም ሆነ ለምርመራ ሲፈለጉ ሕጉ በሚያዘው መንገድ ብቻ መሆን አለበት። ሕግ ለማስከበር ሲባል ሕግ መጣስ የለበትም” ብለዋል።

ልደቱ የሥሜነህን እና የደረጄን ሐሳብ ይደግፋሉ። “መንግሥት በሥሩ ያሉ ተቋማት ሕግን በሚገባ ተረድተው [ሕግን] በማስከበር ሥም መጣስ የለባቸውም” በማለት በሕግ የሚጠየቅ ሰው ክብሩና መብቱ የፍርድ ሒደቱ እስከሚያልቅ ድረስ እንደ ንፁሕ ይቆጠራል የሚለው ሕግ ተግባራዊ መደረግ አለበት ሲሉም አጽንዖት ሰጥተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here