ንግድ ባንክ በ28 ሺሕ ሠራተኞቹ ለተመሰረተበት ክስ መልስ ሳያቀርብ ቀረ

0
528

የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ከ28ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰራተዮች በአሰሪና ሰረተኛ ጉዳይ ቦርድ ከኹለት ሳምንት በፊት ክስ የመሰረቱ ሲሆን ቦርዱ በሰጠው ትእዛዝ መሰረት ለቀረበበት ክስ መልስ ይዞ መምጣት ባለመቻሉ ተለዋጭ ቀጠሮ የሰጠ ሲሆን ባንኩ መልሱን ይዞ ካልቀረበም መብቱ ሊታለፍ እንደሚቸል ቦርዱ አስጠንቅቋል።

በሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ውስጥ ያሉ ምንጮች ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት ሐሙስ፣ ሰኔ 27/2011 ከሰዓት በኋላ በዋለው ችሎት ጠበቃ ያሬድ ስዩም የሠራተኛ ማኅበሩን ወክለው የተገኙ ሲሆን የባንኩ ተወካዮች ግን መልስ ሳያመጡ ቀርተዋል። የሠራተኛ ማኅበሩ ከባንኩ ጋር ባለው የኅብረት ውል ስምምነት መሰረት የድርጅቱ ሠራተኞች የሥራ ሰዓት በሳምንትት 41 ሰዓት እንዲሆን የሚደነግግ ቢሆንም ባንኩ ግን በሳምንት 48 ሰዓት እንዲሠሩ ማድረጉ የኅብረት ውል ስምምነቱን የጣሰ ነው የሚለው የመጀመሪያው ክስ እንደሆነ ምንጮቹ ተናግዋል።

በተጨማሪም ዕድገት የሚሰጥበት መስፈርትም እንዲሁ እየተተገበረ አይደለም የሚለው የሠራተኛ ማኅበሩ ክስ ኹለቱም ድርጊቶች እንዲቆሙ እግድ ይሰጥልን ሲል አመልክቷል። የባንኩ የቅርብ ምንጮች እንደገለጹት ከዚህ ቀደም ተደጋጋሚ ድርድሮች የተደረጉ ቢሆንም ምንም ዓይነት ፍሬ ማፍራት እንዳልቻሉ ታውቋል።

የሠራተኛ ማኅበሩን ሰብሳቢ ሃይማኖት ለማ በጉዳዩ ላይ መረጀ ለመስጠት እንደማይቸሉ እና የፍርድ ቤት ሒደቶቹም ሲጠናቀቁ ለመገናኛ ብዙኀን እንደሚያሳውቁ ገልፀዋል። የማኅበሩ ጠበቃ ያሬድም በገቡት ውል መሰረት ማንኛውንም አስተያየት ከሠራተኛ ማኅበሩ ፈቃድ ውጪ እንደማይሰጡ ተናግረዋል። አዲስ ማለዳ የባንኩን የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑትን በልሁ ታከለ በሥልክ ለማግኘት ያደረገችው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

በ1960 የሠራተኞችን መብት ለማስከበር የተቋቋመው ማኅበሩ 30 ሺሕ ገደማ የሚጠጉ አባላት ያሉት ሲሆን በአጠቃለይ ለተከታታይ ዓመታት በሠራተኞቹ የደመወዝ እና የጥቅማ ጥቅም ጥያቄዎች ሲቀርብበት እንደነበር ይታወሳል። ይህንን የደመወዝ እና የሥራ እርከን ዕድገት ጥያቄዎች ከማንሳት ባለፈም በያዝነው ዓመት የሥራ የማቆም አድማ ለማድረግ ታስቦ በሒደት መሰረዙም ይታወቃል።

በተለይም በፍራንክፈርት ስኩል ኦፍ ፋይናስ አማካኝነት ለረጅም ዓመታት ሲጠና የነበረው እና ባለፈው ዓመት የተተገበረው የመሥሪያ ቤቱ መዋቅር በድርጅቱ ውስጥ ለተፈጠሩ ቅሬታዎች መባባስ ምክንያት እንደነበር ይታወቃል፡፡ ስርዓቱም በከፍተኛ የሥራ እርከን ላይ የሚገኙ ሠራተኞችን ከመጥቀም ባለፈ ለብዙኀኑ ሠራተኛ ምንም ለውጥ አላመጣም ብለው ይሞግታሉ።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here