በአዲስ አበባ ከተማ የታሸገ ውሃ እጥረት አጋጥሟል

0
727

በአዲስ አበባ ከተማ በስፋት በመከፋፈል ለኅብረተሰቡ በሽያጭ የሚቀርቡ የታሸጉ ውሃዎች የምርት እጥረት እንደገጠማቸው ታወቀ። የተለያዩ የውሃ አምራች ድርጅቶች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት በአገር ዐቀፍ ደረጃ ከተጀመረው የመብራት ፈረቃ ጋር በተያያዘ ከአቅም በታች ስለሚያመርቱ በከተማዋ ውስጥ ያለውን የውሃ ፍላጎት ማርካት እንዳልቻሉ ተናግረዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የተለያዩ ውሃ አምራች ፋብሪካዎች ዋና ሥራ አስኪያጆችና የሽያጭና ግብይት ኀላፊዎች እንደገለፁት በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ የቧንቧ ውሃን መሠረት አድረጎ መንግሥት በጥንቃቄ አፍልቶ ኅብረተሰቡ መጠቀም እንዳለበት መግለጫ ካወጣ በኋላ ፍጆታው መጨመሩን ገልፀው፤ በተቃራኒው ደግሞ ፋብሪካዎች ከተፈጠረው የመብራት ፈረቃ ጋር ተያይዞ የማምረት አቅማቸው መዳከሙ ለእጥረቱ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነ አስረድተዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ የአርኪ ውሃ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጌታነህ አስፋው ለአዲስ ማለዳ ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ቀድሞ ከምናመርተው በግማሽ ቀንሰናል” በማለት በኹሉም መጠን አሽገን ለሽያጭ የምናቀርባቸው ውሃ ላይ እጥረቱ እንዳጋጠመ እንጂ የተወሰኑ መጠኖች ብቻ ተለይቶ እጥረቱ እንዳልታየ ተናግረዋል። ከዚሁ ጋር ተያይዞ አርኪ ውሃ የመብራት ፈረቃ ከመጀመሩ በፊት ያመርተው የነበረው 18 ሺሕ ኮዳ ውሃ ነው ሲሉም አክለዋል።

በተመሳሳይ ‘ፍቅር’ የታሸገ ውሃ ፋብሪካ ውስጥ በሽያጭ እና በግብይት ዘርፍ በኀላፊነት የሚያገለግሉት ዳግማዊ ጌታቸው በአዲስ አበባ ከተማ ስላጋጠመው እጥረት ሲናገሩ በኢንደስትሪው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የምርት መቀዛቀዝ እየታየ እንደሆነና ይህም ከመብራት ፈረቃው በተጨማሪም ለምርት ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎችን ለማስገባት የውጭ ምንዛሪ ችግር እንደሆነ ጠቁመዋል። ይሁን እንጂ ድርጅቱ የሚያመርተው ውሃ በስፋት እየተከፋፈለ እንደሚገኝ እና በአንዳንድ ቦታዎች ምርታቸው የማይገኝበት እንዲሁም እጥረት የሚታይበት ምክንያት ግለሰቦች ወይም ባለሱቆች ሆነ ብለው አናወርድም ስለሚሉ ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል።

አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው የውሃ ፋብሪካዎች በአንድነት የሚስማሙበት ከኀይል እጥረት ጋር ባለፈ ምርቶቻቸው የማይደርሱባቸው አካባቢዎች ሊኖሩ ስለሚችሉ አንዱ የውሃ ፋብሪካ መድረስ የሚችልባቸው አካባቢዎች ሌሎች ላይደርሱ ይችላሉ በዚህም ምክንያት ኹሉም ቦታ ኹሉንም የውሃ ዓይነቶች ላይገኙ እንደሚችሉ ያስረዳሉ።

በግንቦት ወር መጀመሪያ በአገር ዐቀፍ ደረጃ እስከ ሰኔ 30/ 2011 የሚቆይ መብራትን በፈረቃ ማከፋፈልን ተከትሎ በርካታ አምራች ድርጅቶች ሠራተኞችን እስከመቀነስ እና ሥራ እስከማቆም መድረሳቸው የሚታወቅ ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞም ተመርቆ ከተከፈተ በወጉ ዓመት ያልሞላው ‘ኬር’ የተሰኘ ውሃን በተለያየ መጠን አሽጎ ለገበያ የሚያቀርብ ድርጅት የመብራት ፈረቃ መጀመሩን ተከትሎ በመጀመሪያ ደረጃ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ የገጠመውን ችግር ለመወጣት ሞክሮ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን መቀጠል ግን ባለመቻሉ ሠራተኞቹን በትኖ ሊዘጋ እንደቻለ የአዲስ ማለዳ ምንጮች አስታውቀዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here