ተጓዦች በወረፋና በጉዞ መስተጓጎል አየር መንገዱን አማረሩ

0
858

በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም ዐቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በኩል ወደ ተለያዩ ዓለም ዐቀፍ መዳረሻዎች የሚጓዙ መንገደኞች በአየር መንገዱ ሠራተኞች ክፍተት ከጉዟቸው እየተስተጓጎሉ መሆናቸውን ጠቅሰው ቅሬታቸውን አሰሙ። ችግሩ የሚስተዋለው በተለይም የኢትዮጵያ አየር መንገድን ምርጫቸው አድርገው በሚጓዙ የአገር ውስጥና የተለያዩ አገራት ዜግነት ባላቸው መንገደኞች መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በመገባደድ ላይ ያለው ሰኔ ወር ከገባ ጀምሮ በሰዎች መጨናነቅ የጀመረው አየር መንገዱ በተለይ ደግሞ በኢምግሬሽን አካባቢ የሚታየው ሰልፍ እጅግ አሰልቺ እና በረራዎች እንዲያመልጧቸው ከሚያደርጉ ምክንያተች አንዱ እንደሆነ አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ቅሬታ አቅራቢዎች ይናገራሉ። በተለይ ደግሞ በተደጋጋሚ ለንግድ ወደ ውጭ አገራት የሚመላለሱት ግደይ በላይ ለአዲስ ማለዳ እንደገለፁት ከዚህ ቀደም ከበረራ ሰዓት አስቀድሞ የጉዞ ቅድመ ሁኔታዎችን በማሟላትና ሻንጣዎችን ጭኖ መመለስ ይቻል የነበረው አሰራር መከልከሉ ሌላኛው ለተፈጠረው መጨናነቅ አሉታዊ ግብዓት እንደሆነ ጠቁመዋል።

ሌሎች ቅሬታ አቅራቢዎች ለአዲስ ማለዳ እንደተናገሩት ወደ ሰሜን አሜሪካ እና ካናዳ የሚደረጉ በረራዎች ብቻ ከበረራ ሰዓት እጅግ አስቀድሞ በመገኘት የጉዞ ቅድመ ሁኔታዎችን አሟልተው እና ዕቃዎቻቸውን አስመዝነው በመጫን ወደ ቤት የሚመለሱበት አሰራር አሁንም መኖሩን ጠቅሰዋል። ይሁን እንጂ በርካታ መንገደኛ የሚስተናገድባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ እና ሩቅ ምሥራቅ በረራዎች በሚፈጠረው መጨናነቅ የችግሩ ገፈት ቀማሽ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

አየር መንገዱ የበረራዎችን የመቀመጫ ብዛት ሳያገናዝብ በርካታ ትኬቶችን በአንድ የበረራ ቁጥር ወይም አውሮፕላን ለመንገደኞች በመሸጥ ቀድሞ የደረሰው ተጓዥ የሚስተናገድበት አግባብ እንዳለ እና በሚፈጠረው ረጅም ሰልፍ ምክንያት ዘግይተው የሚደርሱ መንገደኞች ደግሞ ቦታ ሞልቷል ተብለው እንደሚመለሱ ተናግረዋል።

ከአንድ ሳምንት በፊት የተከሰተውን የፀጥታ ችግር ተከትሎ ወደ አየር መንገዱ ቅጥር ጊቢ ተጓዦችን ይዘው የሚገቡ መኪኖች ጥብቅ ፍተሻ ስለሚደረግባቸው ለተፈጠረው መጨናነቅ መንስኤ እንደሆነም አዲስ ማለዳ ታዝባለች። በቦታው ላይ ቅኝት ባደረገችበት ሰኔ 22/2011 ገና ወደ አውሮፕላን ማረፊያው የሚያስገባው መንገድ በመኪኖች በመጨናነቁ መንገደኞች ከረጅም ርቀት ሻንጣዎቻቸውን እየጎተቱ በእግራቸው ወደ ውስጠኛው ክፍል ሲያዘግሙ ተመልክታለች።

“ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ችግሮች እየተባባሱ መምጣታቸው ሁኔታውን የከፋ እንዲሆን አደረገው እንጂ ከዚህ ቀደም ባሉት ጊዜያትም ይህን ዓይነት ችግር ይስተዋል ነበር” ሲሉ አስተያየት ሰጪዎች ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

የተጠቀሰውን ችግር በተመለከተ አዲስ ማለዳ የሚመለከታቸውን የኢትዮጵያ አየር መንገዱ ሥራ ኀላፊዎች ለማናገር ያደረገችው ጥረት ባይሳካም ሥማቸው እንዳይጠቀስ የማይፈልጉት ምንጮቻችን እንደተናገሩት፤ አዲሱን የአውሮፕላን ማስፋፊያ ታሳቢ ተደርጎ የመንገደኞችን ቁጥር ለመጨመር ጥረት በመደረጉ ይህ መጨናነቅ ተከስቷል ያሉ ሲሆን፤ የደንበኞችን ቁጥር ለመጨመር በተደረገው እንቅስቃሴ ላይም የሠራተኞችን ቁጥር ለማሳደግ ምንም ጥረት ባለመደረጉ የተጨመረው መንገደኛ ቀድሞ ያስተናግዱ በነበሩ ሠራተኞች ሥራውን ለመከወን በመሞከሩ ከአቅም በላይ እንዲሆን ማደረጉን አስረድተዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here