በአምስት ክልሎች የአንበጣ መንጋ ተከሰተ

0
605
  • በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በ8 ሺሕ ሔክታር የበቆሎ ሰብል ላይ በስፋት ታይቷል

በአምስት ክልሎች የአንበጣ መንጋ በስፋት መከሰቱ ታወቀ። በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በሚገኙ ሰባት ወረዳዎች በ8 ሺሕ ሔክታር የበቆሎና ማሽላ ቡቃያ ላይ የአንበጣ መንጋው በስፋት መታየቱን ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በመምሪያው የሰብል ልማት ቡድን መሪ ተሾመ ገለቱ ለአዲስ ማለዳ እንደገለጹት በዞኑ ከሰኔ 16/ 2011 ጀምሮ የአንበጣ መንጋው ተከስቷል። መንጋው ከበቆሎና ማሽላ ሰብሎች በተጨማሪ በግጦሽ ሳርና ቅጠላ ቅጠሎች ላይ መከሰቱንም ተናግረዋል።በብሔረሰብ አስተዳደር ዞኑ በመኸር እየለማ ካለው 60 ሺሕ ሔክታር መሬት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ ታውቋል።

በግብርና ሚኒስቴር የዕጽዋት ጥበቃ ዳይሬክተር ዘብዲዮስ ስላቶ ለአዲስ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ አሁን በሁሉም ክልሎች የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ሙሉ ለሙሉ ዕድገቱን የጨረሰ በመሆኑና ብዙ ስለማይመገብ በሰብል ላይ ብዙም ጉዳት አያደርስም። ነገር ግን እንቁላል የሚጥሉ ከሆነ፣ የሚፈለፈሉት አንበጣዎች የምግብ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ስለሚሆን በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊያደርሱ ይችላሉ።

እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ከየመን ተነስቶ በሶማሌ ላንድ አድርጎ ኢትዮጵያ የገባው የአንበጣ መንጋ፣ አሁን በአገሪቱ ያለው የአየር ጸባይ ለመራባት ምቹ ስለሚሆንላቸው በቀላሉ ሊራቡ ይችላሉ። ሴቶቹ አንበጦች ተስማሚ የመራቢያ ቦታቸውን የሚያውቁት በሽታ በመሆኑ፣ በቀላሉ ተጠራርተው በአጭር ጊዜ ውስጥ መራባት ይችላሉ።
በሶማሌ ክልል አይሻ በተባለ ቦታ፣ በአፋር፣ በሐረር፣ በድሬዳዋ፣ በምሥራቅ ኦሮሚያ፣ በምሥራቅ አማራና በትግራይ አዋሳኝ ቦታዎች መንጋው የተከሰተ ሲሆን፣ ይህንን ለመከላከልና ለማጥፋት ከዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ጋር በመተባበር ሰፊ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ዘብዲዎስ ተናግረዋል።

አንበጣውን በዘመናዊና በባሕላዊ ዘዴ የመቆጣጠር ሥራ እየተካሔደ መሆኑን ገልጸው፣ ከክልልና ከፌደራል የቀረበ ከ2 ሺሕ ሊትር በላይ ፀረ ተባይ ኬሚካል ርጭት መጀመሩንም ጠቅሰዋል። መንጋው ወደ ሌሎች አካባቢ እንዳይስፋፋ አርሶ አደሩ ግንዛቤ እንዲኖረው በማድረግ የመከላከል ሥራ እየተካሔደ መሆኑንም ገልጸዋል።

መንጋውን በጅራፍና በብረት ጩኸት እንደሚያጠፉ ያወሱት ተሾመ፣ በአሁኑ ሰዓት እንቁላል መጣያ ቦታቸውን ተከታትሎ በመያዝ ገና ሳይፈለፈሉ እንዲጠፉ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል። ኅብረተሰቡ የአንበጣ መንጋውን ሲመለከት ሊሸበር ስለሚችል፣ በየክልሎቹ ሕዝቡን የማረጋጋት ሥራ እየተሠራ ነው ያሉት ዘብዲዎስ፣ በቀጣይም ከሚዲያዎች ጋር በመተባበር የተከሰተው የአንበጣ መንጋ የከፋ ጉዳት እንደማያደርስ በስፋት እናስታውቃለን ብለዋል።

ቅጽ 1 ቁጥር 35 ሰኔ 29 2011

መልስ አስቀምጡ

Please enter your comment!
Please enter your name here